1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ የሳህል አስቸጋሪ ተልዕኮ

ቅዳሜ፣ ግንቦት 13 2014

የጀርመኑ መራሔ-መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ሲያቀኑ በሳሕል ቀጠና እየታየ ስላለው የኃይል አሰላለፍ ለውጥ መምከር ይጠበቅባቸዋል። ተንታኞች ፈረንሳይን ለመተካት ግልጽ ቃል ኪዳኖች እና የመሪነት ሚና ይጠብቃሉ። ሾልዝ ከሴኔጋል እና ከኒጀር ጉብኝታቸው በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪካ ጎራ ይላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/4Bg2T
Vorbericht Afrika-Reise Kanzler Scholz | Regierungsflieger in Accra
ምስል Bernd von Jutrczenka/dpa/picture alliance

የመራሔ-መንግሥት ኦልፍ ሾልዝ የሳህል አስቸጋሪ ተልዕኮ

የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታየን ማየር ባለፈው የካቲት ወር በሴኔጋልና ሌሎችም የአፍሪቃ ሃገራት የሚያደርጉትን ጉዞ ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ድንገተኛ ወረራ ምክንያት አቋርጠው መመለሳቸው አይዘነጋም::የአሁኑ የቻንስለር ሾልስ የመጀመሪያው የአፍሪቃ ጉብኝትም በቀጠናው እየተስፋፋ የመጣውን ቀውስና የሰላም እጦት ለመፍታት ተስፋ የሚሰጥ ተደርጎ ተቆጥሯል:: በተለይም ሾልስ ማሊን ጨምሮ በኒጀርና በደቡብ አፍሪቃ የሚያደርጉት ይኸው ጉዞ ከአፍሪቃ አገራት ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነትን በማረጋገጥና ትብብርን በማጠናከር የጀርመን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በዋናነት ትኩረት የሰጠውን ሩሲያ በአፍሪቃ የሚኖራትን የተገዳዳሪነት ስጋት ሊቀንሰው ይችላል የሚል ዕምነት እንዳላቸው ተንትኞች ያስረዳሉ:: የቡድን 7 ሃገራት አጋርና የወቅቱ የአፍሪቃ ህብረት ሊቀመንበር የሆነችው ሴኔጋል እንዲሁም የአፍሪቃ ስደተኞች ወደ አውሮጳ ለመጓዝ እንደ ስትራቴጂክ የሚጠቀሙባት ማሊ ከጀርመን ጋር በጸረ ሽብር ዘመቻው ለዓመታት የዘለቀ ወታደራዊ ትብብርን በመመስረቷ ሁለቱ ሃገራት ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ይገለጻል:: እስከ ቅርብ ጊዜ በፈረንሳይ የሚመራው የአውሮጳ ሰላም አስከባሪ ጦር በማሊ የፈጸመው ተልዕኮም ዳግም የቀደመውን ግንኙነት ለማደስ እንደሚረዳ ይታመናል:: የባርካኑ የፈረንሳይ ወታደራዊ ዘመቻ እንዲሁም የታኩባው ዓለማቀፍ ተልዕኮ በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣው የወታደራዊው አገዛዝ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ጋር ቅራኔ ከተፈጠረ በኋላ በድንገት እንዲያበቃ ተደርጓል:: ማሊ አምስቱ የሳህል ቀጣና ሃገራት ከመሰረቱት የቡድን-5 የጸረ ሽብር መከላከል ወታደራዊ ጥምረት ራሷን ማግለሏን ባለፈው ዕሁድ ካሳወቀች በኋላ የአውሮጳ ህብረት ለማሊ መንግሥት ጦር ይሰጥ የነበረውና የተቋረጠው ወታደራዊ ሥልጠና አሁንም ሊዘገይ እንደሚችል የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ጆሴፍ ቦሬል አስጠንቅቀዋል:: ወትሮውንም ቢሆን የበርካታ ምዕራባውያን ሀገራት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች መናኸሪያ የሆነችው ኒጀር ግን ለቀጣይ አዳዲስ ተልዕኮዎች እስካሁን አዎንታዊ ምልሾች እየሰጠች መሆኗ ታውቋል:: የደቡብ አፍሪቃው የደህንነት ጉዳዮች ጥናት ቲንክ ታንክ ተቋም ባለሙያ የሆኑት ፕሪያን ሲንግ ከዶይቼ ቨለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ጀርመን በቀጣይ ለሳህል የሰላም ተልዕኮ አዲስ ስትራቴጂ እንደምትከተል ዕምነታቸውን ገልጸዋል:: "ጀርመን እስካሁን በሳህል ቀጣና ፈረንሳይ ስትሄድበት የቆየችውን መንገድ የምትከተል አይሆንም:: ምክንያቱን የቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ ከተልዕኮዋ በተቃራኒው በምዕራብ አፍሪቃ የራሷን አጀንዳ ለማስፈጸም ሞክራለች በሚል ተደጋጋሚ ትችት ሲሰነዘርባት ቆይቷል:: ለዚህም ነበር እንደ ኒጀር ባሉ ሃገሮች ጸረ ፈረንሳይ መልዕክቶችን የያዙ ሰዎች የጎዳና ላይ ሰልፎችን ሲያካሂዱ የተስተዋለው:: እንደማስበው ጀርመን ግን በተወሰነ ደረጃ ገለልተኛ አቋም ስታራምድ በመቆየቷና በምጣኔ ሃብት ትብብር ላይ ስላተኮረች አሁንም አጋር ሆና መቀጠል ትችላለች የሚል ዕምነት አለኝ::ጀርመን ከሳህል ሌላ በመካከለኛው ምስራቅ በሰሜን አፍሪቃና በሌሎችም ሃገራት በሰላም ማሰከበር ተልዕኮ የላቀ ሚና ስትጫወት መቆየቷም አይዘነጋም" 

Belgien Brüssel | EU-Afrika-Gipfel | Olaf Scholz
መራሔ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ በብራስልስ የአውሮፓ ኅብረት እና አፍሪካ ጉባኤ ምስል Yves Herman/AFP/Getty Images

ይሁን እንጂ "የአፍሪቃ ማህበረሰብ በዓለማቀፉ ሰላም አስከባሪ ጦር የቆይታ ጊዜ መራዘም ጉዳይ በጣም እየተሰላቸ የመጣ ይመስላል" ሲሉ በጀርመን የሲቭል ማህበረሰብ የሳህል ትኩረት ኔትዎርክ ኮሚቴ አባል ኦላፍ በርናው ይገልጻሉ::"በኒጀር ከነዋሪዎች ጋር በተካሄደ ውይይት፣ ዓለማቀፉ ሰላም አስከባሪ ጦር በአካባቢርው ለረጅም ጊዜያት መቆየቱ የጀሃዲስት ቡድኖችን ጥቃት የበለጠ በሳህል ግዛት ሊያስፋፋው ይችላል የሚል ስጋት አላቸው" በማለት በርናው ተናግረዋል::

ምልከታ:- ወታደራዊ ስልጠናና ማህበራዊ መሰረቶችን ማጠናከር

ጀርመን እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ከ 2018 ዓ.ም ጀምሮ የናይጄሪያን ልዩ ኃይል "በጋዜል ተልዕኮ" እያሰለጠነች ትገኛለች:: ይህ ተልዕኮ ደግሞ አስቀድሞ በተያዘው ዕቅድ መሰረት በዓመቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል:: ባለፈው ሚያዝያ ወር በሳህል ቀጣና የሚካሄደውን ወታደራዊ ስልጠና የጎበኙት የጀርመኗ መከላከያ ሚኒስትር ክሪስቲን ላምብሬክት ስለ አዲስ ስትራቴጂካዊ የትብብር ስምምነት መጠቆማቸው ምናልባትም ይኸው የስልጠና ተልዕኮ ወደ ሌሎች ሃገራት ሊሸጋገር እንደሚችል ፍንጭ የሰጠ ሆኗል:: ኒጀር የአውሮጳ ህብረት ወታደራዊ ስልጠና ተልዕኮ ማዕከል ልትሆን ትችላለች የሚሉት በርናው ግልጽነት ያለው የሥልጠና ተልዕኮ በአካባቢው የሚደርስ ውድመትንና ጥቃትን ለመቀነስ ይረዳል ሲሉ ይገልጻሉ:: ያም ቢሆን ወታደራዊ ትብብር ብቻውን ለበርካታ ዓመታት በሳህል አካባቢ የዘለቀውን ዘርፈ ብዙ የጸጥታ ችግር እንደማይፈታ ባለሙያዎች ይስማማሉ:: የደህነት ጥናት ባለሙያ የሆኑት ሲንግ "በጀርመን መሪነት የሚወሰዱ አመክንዮአዊ እርምጃዎች ምናልባትም በቀጣይ ለአካባቢው ሰላም ግንባታ ወሳኝ እርምጃዎች ይሆናሉ:: ምክንያቱም ጀርመን በረጅም ጊዜ ቆይታዋ በአካባቢው ተጨባጭ የሆነ በቂ ልምድ ስላላት ሁሉን አቀፍ ሥልጠናና ግልጽ የሆነ የዕቅድ ትግበራ ማከናወን በማህበረሰቡ ውስጥ እምነትን ለመገንባት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና እስከታች ያለው መዋቅር እንቅስቃሴም በአዲስ መንፈስ ዳግም እንዲነቃቃ ለማድረግ ቁልፍ ሚና አለው"

የጋራ ስኬት ተጠቃሚኒት:- በኃይል አቅርቦቱ ዘርፍ ከጥገኝነት የሚወጡባቸው መንገዶች

የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ቀጣዩ የአፍሪቃ ሃገራት ጉብኝት በንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮችም ዘንድ ትልቅ ተስፋን አሳድሯል::የጀርመን የኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤቶች የውጭ ንግድ ኃላፊ የሆኑት ፎልከር ትሬየር ከዶይቼ ቨለ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ "የሾልስ ጉብኝት ወቅታዊና ትክክለኛው ጊዜ ነው" ብለዋል:: ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ እንዲሁም በሻንጋይና ሌሎችም የቻይና ክፍሎች ዳግም የተቀሰቀሰው የኮረና ወረርሽኝ ያስከተለው የዝውውር እገዳ ሀገራት በኃይሉ ዘርፍ ለአብነት የአንድ ወገን ጥገኛ ሆነው ለመቆየታቸው በግልጽ ያሳዩ ክስተቶች ናቸው:: እንደ ትሬየር ዕምነት "ከተለያዩ ሃገራት ጋር በተለያዩ ዘርፎች የልምድና የሃሳብ ልውውጥ ማካሄድ እንዲሁም በኢነርጂና በደህንነት ፖሊሲ ጉዳዮችም የማዕቀፍ ስምምነቶችን ማድረግ ይገባል":: በዚህ ረገድ አፍሪቃ ለጀርመን ለአየር ብክለት መንስኤ መሆኑ ከሚጠቀሰው የቅሪተ አካል ኃይል ይልቅ ፈሳሽ ጋዞችን ማቅረብ የምትችል ሲሆን ጀርመንም ልምዶቿንና ቴክኖሎጂዎቿን ለአፍሪቃ ማካፈል ትችላለች:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለጸሃይ ኃይል ፕሮጀክት ማስፋፊያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ያፈሰሰችው ሴኔጋል በዚህ ረገድ ቀዳሚውን ሚና ልትጫወት ትችላለች የሚል ዕምነት አለ:: ትሬየር መርሃዬ መንግስት ሾልስ በአፍሪቃው ጉብኝታቸው እነዚህን ሁሉ ዕቅዶች በግልጽ ዕውን የሚያደርጉና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ትክክለኛ አማራጮችን ይዘው እንደሚቀርቡ አምናለሁ ብለዋል::

Vorbericht Afrika-Reise Kanzler Scholz | Bundeswehr in Niger
የጀርመን ወታደሮች የኒጀር ወታደሮችን ያሰለጥናሉምስል Kay Nietfeld/dpa/picture alliance

"ወደ አፍሪቃ ሀገራት ስንመጣ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ማቅረብም አለብን" የሚሉት የደህንነት ባለሙያ የሆኑት ሲንግ ዓለም አሁን ከገጠማት የኢነርጂ ጥገነት ለመላቀቅ ብቸኛው መንገድ ዘላቂ የሆኑ ኃይሎችን ጥቅም ላይ ማዋል ነው ሲሉ ያስረዳሉ:: ለምሳሌ የረጅም ጊዜ የጀርመን አጋር የሆነችው ደቡብ አፍሪቃ ዛሬም ድረስ በድንጋይ ከሰልና በቅሪተ አካል ነዳጆች ላይ ጥገኛ በመሆኗ የኃይል ዘርፉን ለማስፋፋት ትልቅ ፍላጎት እንዳላትም ሲንግ ተናግረዋል::

"ደቡብ አፍሪቃ ቢያንስ ከ 2008 ዓ.ም ጀምሮ በሃይል ቀውስ ውስጥ ትገኛለች:: የሃገሪቱ የኃይል አቅርቦት የውጭ ኢንቨስትመንት ፍላጎትን የሚያሟላ አይደለም:: ስለሆነም በደቡብ አፍሪቃና በጀርመን መካከል በኢንቨስትመንት ወይም በቴክኒካል የዕውቀት ሽግግር ረገድ ሽርክና ለመፍጠር ሰፊና አመቺ ዕድል አለ"::

የአፍሪቃ አህጉርን በነጻ የንግድ ልውውጥ ለማስተሳሰር ገቢራዊ የሆነውና የአውሮጳ ህብረት ዓይነት ቅርጽ ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የአፍሪቃ ነጻ የንግድ ስምምነት ለአዎንታዊ እድገት ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ያሉት የጀርመን የኢንዱስትሪና ንግድ ም/ቤቶች የውጭ ንግድ ኃላፊ ፎልከር ትሬየር "የጀርመን-አፍሪቃን ትብብር ማጠናከር የጀርመን ኩባንያዎች በአፍሪቃ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱና ተጨማሪ የስራ እድልንም ለመፍጠር የተሻለ መሰረት ይጥላል። ከጥሬ ዕቃዎች በተጨማሪ የአፍሪቃ ምርቶች በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ሚናቸውን ሊጨምሩም ይችላሉ" ሲሉ አስረድተዋል።

ፊሊፕ ሳንድነር/እንዳልካቸው ፈቃደ