1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሠረተ ልማት ጉድለትና ኮሌራ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2015

የድህነት በሽታ የሚባለው ኮሌራ በንጽሕና ጉድለት የሚከሰት እንደመሆኑ በተለይ የንጹሕ ውኃ አቅርቦት እና የመጸዳጃ አገልግሎት እጥረት የተንሰራፋባቸው ሃገራት ዋነኛ ችግር ነው። የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ከሰሞኑ በስምንት ዓመታት ውስጥ ኮሌራን የማጥፋት ዕቅድ እንደያዘ አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4LgTu
Mikroskopaufnahme von Cholera Bakterien
ምስል Callista Images/IMAGO

ኮሌራን ለማጥፋት ትኩረት

የዓለም የጤና ድርጅት የኢፍትኃዊነት እና የማኅበራዊ ልማት እጥረት ማሳያ ከሆኑት አንዱ ነው የሚለው ኮሌራ የዓለም የማኅበራዊ ጤና ስጋት እንደሆነ መቀጠሉን ያመለክታል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በየዓመቱ ከ1,3 እስከ 4 ሚሊየን የሆኑ ሰዎች በመላው ዓለም ለኮሌራ ይጋለጣሉ። በዚህም ከመቶ ሺህ በላይ ሰው ያልቃል። የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር ከሰሞኑ ይፋ ብሔራዊ ኮሌራን የማጥፋት ዕቅድ ዋና ትኩረቱ በኮሌራ ምክንያት የሚሞተውን የሰው ቁጥር 90 በመቶ ለመቀነስ ነው።  ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሌራ ተይዘው የነበረበትን አጋጣሚ ያስታወሱት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ከዚያ ወዲህ በተደረገ የመከላከል ጥረት በበሽታው ሕይወቱ የሚያልፈውን ሕዝብ ቁጥር መቀነስ እንደተቻለም ተናግረዋል። የጤና ሚኒስቴር ኮሌራን በስምንት ዓመት ውስጥ ለማጥፋት ያዘጋጀውን ዕቅድ በተለይ በተደጋጋሚ በሽታው በሚከሰትባቸው 118 ወረዳዎች ተግባራዊ ለማድረግ ነው ያለመው። የጤና ሚኒስትሯ እንደተናገሩት በእነዚህ ወረዳዎች ወደ 18 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ ይኖራል። እናም ከዕቅዱ አንዱ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ለ15 ሚሊየን ሕዝብ የኮሌራ ክትባት ለመስጠት መሆኑንም ገልጸዋል።

Libanon | Cholera
የንጹሕ ውኃ አቅርቦት ችግር ምስል Mohamed Azakir /REUTERS

በነገራችን ላይ ክትባቱ የሚረዳው ለሦስት ዓመታት ብቻ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሌራ ምክንያት የሚሞተውን ሰው ቁጥር ለመቀነስ ከክትባቱ በተጓዳኝ የንጹሕ ውኃ አቅርቦትን ማሻሻል ዋነኛ መፍትሄ መሆኑን ጥናቶች አጽንኦት ይሰጣሉ። ቫይብሪዮ ኮሌራ በተባለ ጀርም አማካኝነት በተለይም ንጹሕ ያልሆነ ውኃን በመጠቀም የሚስፋፋው ኮሌራ በሽታ መጠነኛ ወይም ምን አይነት የህመም ምልክት ሳያሳይ አፋጣኝ ተቅማጥ፣ ማስመለስ እንዲሁም የሆድ ቁርጠትን እንደሚያስከትል የጤና መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የኮሌራ ወረርሽኝ ከሚከሰትባቸው ሃገራት አንዷ ናት። የጤና ሚኒስቴር ከሰሞኑ በጉዳዩ ላይ በሰጠው ማብራሪያ ይህንኑ አረጋግጧል። ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥd በሽታውን በስሙ ያለመጥራት ዋነኛ ችግር እንደነበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዚህ ጋር በተያያዘ ትችት የሚሰነዝሩ አካላት ያነሱታል። አሁን ኮሌራ መከሰቱን በግልጽ መናገር መጀመሩን እንደ ትልቅ እርምጃ የሚወስዱት ጥቂት አይደሉም። ችግሩን ማወቅና ኅብረተሰቡም እንዲጠነቀቅ ማሳወቅ ወደ መፍትሄ የሚያደርስ እንደሆነ ይታመናል።  በሌላ በኩል ኮሌራን በአጭር ዓመታት ውስጥ ከኢትዮጵያ ለማጥፋት መታሰቡ አዎንታዊነቱ ቢታመንም መሠረተ ልማትን በማስፋፋት ካልታገዝ ከሚታሰበው ውጤት ለመድረስ እንደሚያዳግት ነው የህክምና ባለሙያዎች የሚናገሩት።

Symbolbild Hände waschen
እጅን መታጠብ ተሐዋስያንን የመከላከያው አንዱ መንገድምስል Imago Images/M. Westermann

የዓለም የጤና ድርጅት  በጎርጎሪዮሳዊው 2030 ዓ,ም ኮሌራን ለማጥፋት ካለመ ሰንብቷል። ይህን ከጽዳት ጉድለት ጋር በእጅጉ የሚቆራኝ እና የበርካታ ዋና ዋና መሠረተ ልማቶች ያልተስፋፉባቸው ሃገራት ዋነኛ የጤና ችግር ለማስወገድ እንቅፋት ሆነዋል ካላቸው ቀዳሚው የንጹሕ ውኃ አቅርቦት ጉድለት ነው። ኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ካቋቋመች 80 ዓመታት እንደሆናት ያስታወሱት ከ40 ዓመታት በላይ በማኅበረሰብ ጤና ዘርፍ ያገለገሉት ዶክተር መኮንን አይችሉህም ዕቅዱ መልካም ቢሆንም በተባለው ጊዜ ውስጥ ግን እውን ለማድረግ እንደሚከብድ አመልክተዋል።

በይርጋለም አጠቃላይ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ የሆኑት ሲስተር ኂሩት ፍሰሀም እንዲሁ ዕቅዱ አስደሳች ቢሆንም ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ መሻሻሎች ሳይኖሩ ለማሳካት እንደሚከብድ ተናግረዋል። በማደግ ላይ ካሉት ሃገራት በግንባር ቀደምትነት ከሚጠሩት አንዷ በሆነችው ሕንድ የኮሌራ ወረርሽኝ ዋነኛው የጤናው ዘርፍ ችግር እንደሆነ ይነገራል። ሕንድ ኮሌራን ለማጥፋት በምታደርገው ያላሰለሰ ጥረት በተለይ የመጸዳጃ ስልት እና የንጹሕ ውኃ አቅርቦት ችግር በሆነባቸው የገጠር የሀገሪቱ ክፍሎች የታሰበውን ለማሳካት ፈተና እንደሆነባት ጥናቶች ያመለክታሉ። ጀርመን ሀገር ከ30 ዓመታት በላይ በህክምና ሙያቸው ያገለገሉት ዶክተር ውብታየ ዱሬሳ ተክሌ ተመሳሳይ የመሠረተ ልማት ችግር ባለባት ኢትዮጵያ አስቀድሞ የኅብረተሰቡን የአኗኗር ይዞታ ማሻሻል ካልተቻለ ኮሌራን በስምንት ዓመታት ውስጥ እንደታሰበው መቆጣጠር መቻሉ ትልቅ ጥያቄ እንደሆነ ነው የገለጹት።

Guinea Bissau
በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ንጹሕ ውኃ ለማግኘት ያለው ችግርምስል AP

ሲስተር ኂሩት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደታሰበው ኮሌራን ለማጥፋት ብዙ መሠራት አለበት ነው ያሉት። ዶክተር መኮንንም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሌራን በስምንት ዓመት ሳይሆን በረዥም ዓመታት ጥረት ለማጥፋት አስቀድሞ መሠረተ ልማቱን ከማስፋፋት በተጓዳኝ ኅብረተሰቡን ማስተማር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የህክምናው ዘርፍ ምሁራን ኮሌራን የድህነት በሽታ ነው የሚሉት። ዛሬም ድህነት ስር በሰደደባቸው እና ግጭት ጦርነት መሰረተ ልማቶችን ባወደሙባቸው ማኅበረሰቦች መካከል ኮሌራ እንደሚከሰት የመን ፣ እንዲሁም ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ጥሩ ማሳያዎች ተደርገው ይጠቀሳሉ።  መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ ሕዝብ ንጹሕ ውኃ አያገኝም፤ 90 በመቶው ደግሞ አግባብ ያለው የመጸዳጃ አገልግሎት ተጠቃሚ አይደለም ።

World Health Organization - WHO, Logo
ምስል AP

ሕንድ ውስጥ በየዓመቱ 675,188 ሰዎች በኮሌራ እንደሚያዙ፤ ከእነሱም ውስጥ ከ20 ሺህ በላይ እንደሚሞቱ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ 255,221 ሰዎች በኮሌራ ተይዘው፤ ከ10 ሺህ የሚበልጡት ሕይወታቸው እንደሚያልፍ፤ ናይጀሪያም እንዲሁ ከ220 ሺህ የሚበልጡት በኮሌራ እንደሚጠቁ እና ከስምንት ሺህ በላይ ሰዎች እንደሚሞቱ፤ ሃይቲ ውስጥም ከ210 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሌራ እንደሚያዙ እና ከ2,500 የሚበልጡት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

የሰሜን አውሮጳ ሃገራት እና ዩናይትድ ስቴትስ ኮሌራ ከዛሬ 150 ዓመታት በፊት ማጥፋት እንደቻሉ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። ለዚህም የመሠረተ ልማቱ መስፋፋት አይነተኛ ሚና ተጫውቷል። ከህክምናው ማደግ እና መስፋፋት በተጨማሪ የንጹሕ ውኃ አቅርቦትም ሆነ የመጸዳጃው እና ፍሳሽ ማስወገጃው ስልት በአግባቡ የሚሠራ በመሆኑ በብክለት እና ንጽሕና ጉድለት ሊመጣ የሚችለውን በሽታ ማስቀረት አስችሏቸዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ህክምናውን ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ የንጹሕ ውኃ አቅርቦትና የመጸደጃ አጠቃቀም ትልቁን ሚና እንደሚጫወት ነው አስተያየታቸውን የሰጡን የህክምና ባለሙያዎቹ ያሳሰቡት። ሃሳባቸውን ያካፈሉንን የህክምና ባለሙያዎች እናመሰግናለን።

 ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ