ዲስ አበባ-የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2017 ተጨማሪ በጀት አፀደቀ
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገዉ 6ኛ መደበኛ ጉባኤዌ ለ2017 ዓመት ተጨማሪ የ582 ቢሊየን ብር በጀት አጸደቀ።የጭማሪዉ በጀት ጥያቄ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበዉ በሚንስትሮች ምክር ቤት ተደግፎ ነዉ።ይሁንና የምክር ቤቱ አባላት ዛሬ በጉዳዩ ላይ ባደረጉት ዉይይት ከግማሽ ትሪሊዮን በላይ ብር ጭማሪ በጀት መመደብ በሀገሪቱ የዋጋ ንረትን እንዳያባብስ እና ኢኮኖሚውን እንዳያናጋ ሥጋት መኖሩ ተደጋግሞ ተጠይቋል።
ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ "ተጨማሪ በጀት የሚቀርበው ተጨማሪ ገቢ መኖሩ ሲታመንበት" መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ይህንን እንደሚያሳካ «እርግጠኛ ሆነን ያመንበትን ገቢ ነው ይዘን የቀረብነው" ብለዋል።መንግሥት ሐምሌ 2016 ላይ ባደረገው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ እርምጃ ሕብረተሰቡ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ መደረጉንና መሰረታዊ ምርቶች ማለትም ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ የምግብ ዘይት፣ መድኃኒት እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ እንደሚደጎሙም ሚንስትሩ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ እንደዘገበዉ ምክር ቤቱ የቀረበውን ተጨማሪ በጀት በ3 ተቃውሞ እና በ5 ድምፅ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምፅ አጽድቆታል።የኢትዮጵያ አጠቃላይ የ2017 በጀት ወደ 1.55 ትሪሊዮን ብር ከፍ ብሏል።
አዲስ አበባ-የኢትዮጵያ መንግሥት 3 የመብት ተሟጋች ድርጅቶችን ማገዱን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ማዕከል ተቃወመ
የኢትዮጵያ የሲቪል ማሕበረሰብ ባለሥልጣን ባለፈዉ ሳምንት 3 የሰብአዊ መብቶችና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ማገዱን የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ማዕከል (EHRDC) ተቃወመ።ማዕከሉ ዛሬ ባወጣዉ መግለጫ በድርጅቶቹ ላይ የተወሰደዉ እርምጃ የሐገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚጥስ፣«የመንግስትን ሰብዓዊ መብቶችን የማክበርና የማስጠበቅ ግዴታን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እና ለሲቪክ ምህዳሩ መጥበብ የጎላ ተጽእኖ የሚያሳድር» ብሎታል። እገዳ የተጣለባቸዉ የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል (CARD)፣ ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች (LHR) መሆናቸዉን ማዕከሉ በመግለጫዉ ጠቅሷል፡፡በማዕከሉ መግለጫ መሠረት እነዚሕ ሶስት ድርጅቶቹ «በሰብአዊ መብቶች ሥራ ትልቅ እውቅናን ያተረፉ፣ አገርን ሊጠቅሙ የሚችሉ በርካታ ሥራዎችን ያበረከቱና እየሰሩ የሚገኙ ናቸዉ።» የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል መግለጫ እንደሚለዉ ከዚሕ ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት የሚያደርጉባቸዉን ጫና፣ ክትትልና ማስፈራራት በመሸሽ በሥም የጠቀሳቸዉ 4 የመብት ተሟጋቾች ድርጅቶች ኃላፊዎች ከሐገር ተሰድደዋል።ኢትዮጵያ ዉስጥ ከጅምሩ «ጥሩ እመርታ አሳይቶ ነበር» ያለዉ የሲቪክ ምሕዳር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ወገኖች ሁሉ እንዲጥሩ ማዕከሩ ጠይቋል።በተያያዘ ዜና የ3ቱን ድርጅቶች መታገድ ዓለም አቀፉ የምብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል አዉግዞታል።ድርጅቱ ማምሻዉን ባሠራጨዉ መግለጫ የድርጅቶቹ መታገድ ኢትዮጵያ ዉስጥ «በሲቭካ ማሕበራት ላይ የሚፈመዉ ጫና መጠናከሩን የሚያመለክት» ብሎታል።መንግሥት ድርጅቶቹን ለማገዱ የሰጠዉን ምክንያትም ዓለም አቀፉ ድርጅት «የተለመደ» በማለት ነቅፎታል።
ሐዋሳ-በወርቅ ሥርቆት የተጠረጠሩ የፖሊስ አዛዥ ተያዙ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ሦስት ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ ሰርቀዋል ተብለዉ የተጠረጠሩ የጮርሶ ወረዳ የፖሊስ አዛዥ ታሠሩ፡፡የዞኑ ፖሊስ መምሪያ እንዳስታወቀዉ የጮርሶ ወረዳ የፖሊስ አዛዥ የታሰሩት በኮትሮባንድ ሲዘዋወር ከተያዘ ሰባት ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ መካከል ሦስቱን ወደ ቤታቸው ወስደዋል በሚል ጥርጣሬ ነዉ፡፡ አዛዡ ወርቁን ወደ ቤታቸው መውሰዳቸው የተጠረጠረጠረዉ ወርቁን ሲያዘዋውሩ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች የተያዘብን ወርቅ ይሄ ብቻ አይደለም በሚል በሰጡት ጥቆማ መሠረት በተደረገ ምርመራ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዣ ኮማንደር ግርማ በየነ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡
“ የጎደለ ወርቅ ሥለመኖሩ መረጃው እንደወጣ ተጠርጣሪው አዛዥ ከአካባቢው ለመሰወር ሞክረዋል ያሉት የመምሪያው አዛዥ “ ነገር ግን ፖሊስ ባለቤታቸውን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ አድርጓል ፡፡ የተጠርጣሪው አዛዥ ባለቤትም የቅርብ ዘመዶቻቸው ጋር በመደወል ወርቁን ከቤት በማስመጣት ገቢ አድርገዋል ፡፡ ተሰውረው የነበሩት አዛዥም ትናንት ሰኞ በሀዋሳ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ተችሏል “ ብለዋል ፡፡
የሐዋሳዉ ወኪላችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ የዞኑን የፖሊስ አዛዥ ጠቅሶ እንደዘገበዉ በወርቅ አዘዋዋሪዎችን እና ወርቁን ለመሰወር በሞከሩት የፖሊስ አዛዥ ላይ ተጨማሪ ምርምራ ተደርጎ ተጠርጣሪዎቹ ለሕግ ይቀርባሉ።
ዤኔቭ-አፍሪቃ ዉስጥ በርካታ ሕዝብ ከተፈናቀለባቸዉ ሐገራት እንዷ ኢትዮጵያ ናት
አፍሪቃ ዉስጥ የሚደረጉ ጦርነቶችና የዓየር ንብረት መዛባት ከቤት ንብረቱ የሚያፈናቀሉት ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት አስታወቀ።ዓለም አቀፉ የተፈናቃዮች ጉዳይ ተመልካች ማዕከል (IDMC) እንደሚለዉ አፍሪቃ ዉስጥ እስከ ግሪጎሪያኑ 2023 ማብቂያ ድረስ 35 ሚሊዮን ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።ከ35 ሚሊዮኑ ተፈናቃይ 32.5 ሚሊዮኑ የተፈናቀለዉ ጦርነት፣ ግጭትና ጥቃትን ሸሽት ነዉ።የተቀረዉ በዓየር መዛባት ምክንያት አካባቢዉን ለቅቆ የተፈናቀለ ነዉ።ርዕሠ-መንበሩን ዤኔቭ-ስዊትዘርላንድ ያደረገዉ ማዕከል የበላይ ሐላፊ አሌክሳንደር ቢላክ እንዳሉት ከ35 ሚሊዮኑ ተፈናቃይ 80 በመቶዉ የተፈናቀለዉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአምስት ሐገራት ዉስጥ ነዉ።
«አብዛኞቹ ሰዎች የተፈናቃሉት በግጭትና ጥቃት ምክንያት ነዉ።በድንገተኛና ተደጋጋሚ አደጋዎች የተፈናቀሉም አሉ።አፍሪቃ ዉስጥ ካሉት 35 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ዉስጥ አብጣኞቹ ማለትም 80 በመቶዎቹ የሚኖሩት በአምስት ሐገራት ዉስጥ ነዉ።ሱዳን፣ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያና ናጄሪያ ናቸዉ።»
በድርጅቱ ዘገባ መሠረት በዓለም ላይ ባለፉት 15 ዓመታት ከየቤት ንብረቱ የሚፈናቀለዉ ሕዝብ ቁጥር በሶስት እጥፍ ጨምሯል።በመላዉ ዓለም ካለዉ ተፈናቃይ ግማሽ ያክሉ አፍሪቃዊ ነዉ።
እየሩሳሌም/ቤይሩት-የእስራኤልና ሒዝቡላሕ ተኩስ ሊያቆሙ ነዉ
እስራኤልና የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቡላሕ ዩናይትድ ስቴትስ ያቀረበችዉን የተኩስ አቁም ሐሳብ እንደሚቀበሉት የእስራኤልና የሊባኖስ ባለሥልጣናት አስታወቁ።የሊባኖስ ምክር ቤት ትናንት የተኩስ አቁሙን ዕቅድ አፅድቆታል።የእስራኤል ባለሥልጣናት እንዳሉት ደግሞ ዛሬ የሚሰበሰበዉ የእስራኤል የፀጥታ ካቢኔ ዕቅዱን ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል።የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የፀጥታ አማካሪ ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢም የመንግሥታቸዉ የተኩስ አቁም ዕቅድ ተቀባይነት ለማግኘት ተቃርቧል ብለዋል።ስምምነቱን ሁሉም ወገኖች መቀበላቸዉን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደንና የፈረንሳዩ አቻቸዉ ኢማንኤል ማክሮ ዛሬ ማታ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እየሩሳሌም/ቤይሩት-የተኩስ አቁም ይዘትና የጦርነቱ ጉዳት
በዕቅዱ መሠረት የእስራኤል ጦር ከደቡባዊ ሊባኖስ ለቅቆ ይወጣል።የሒዝቡላሕ ታጣቂ ኃይልም ከሊታኒ ወንዝ በስተደቡብ የሚገኘዉን ሥፍራ ይለቅቃል።ባካባቢዉ የሊባኖስ ጦር ኃይል በ60 ቀናት ዉስጥ ይሠፍራል።እስራኤልና ሒዝቡላሕ ከአምና መስከረም ጀምሮ በገጠሙት ዉጊያ ከ3 ሺሕ 700 በላይ የሊባኖስ ዜጎች መገደላቸዉን የሊባኖስ የጤና ሚንስቴር አስታዉቋል።ሮይተርስ ዜና አገልግሎት እንደዘገበዉ የሊባኖስ የጤና ሚንስቴር ዘገባ የሟች ታጣቂዎችንና የሰላማዊ ሰዎችን ቁጥር አልየም።የእስራኤል ጦር ከሚደድባቸዉ አካባቢዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሊባኖሳዊ ተፈናቅሏል።ሒዝቡባላሕ ሰሜናዊ እስራኤልና እስራኤል በኃይል በያዘችዉ የሶሪያ ግዛት ጎላን ኮረብታ ላይ በከፈተዉ ጥቃት 45 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።በሮይተርስ ዘገባ መሠረት ሰሜናዊ እስራኤል፣ ጎላን ኮረብታና ደቡባዊ ሊባኖስ ዉስጥ በተደረገዉ ዉጊያ ደግሞ በትንሽ ግምት 73 የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል።የእስራኤል ጦር ዛሬም የሊባኖስን ርዕሠ ከተማ ቤይሩት መደብደቡን አስታዉቋል።የቤይሩት የ20 ቀበሌ ነዋሪዎች ከየአካባቢያቸዉ እንዲሸሹ አስጠንቅቋልም።
ፊዉጂ-የቤርቦክ መልዕክት ለቡድን 7 ሚንስትሮች ስብሰባ
የዩናይትድ ስቴትስ ተመራጭ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የሚያራምዱትን «አሜሪካ ትቅደም» መርሕ ለመቋቋም አዉሮጳ በአንድነት መቆም እንደሚገባት የጀርመንዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አሳሰቡ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ ፊዉጂ-ኢጣሊያ ለተሰበሰቡት የቡድን 7 አባል ሐገራት የዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች እንደነገሩት ከአዲስ የአሜሪካ አስተዳደር የሚመጣዉን ጫና ለመቋቋም አብነቱ የአዉሮጳ አንድነት ነዉ።ጫናዉ በዓየር ንብረት፣ በንግድ መርሕ ይሁን ወይም በሌላ ጉዳይ የአዉሮጳ አንድነት መጠናከር አለበት።የአዉሮጳ አንድነት በዉስጥ ንግዷ ላይ የተመሠረተ እንደሆነም የጀርመንዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አስታዉቀዋል።ቤርቦክ አክለዉም «አዉሮጶች በምጣኔ ሐብቱ ብቻ ሳይሆን ፀጥታን በማስከበሩ ረገድም ይበልጥ ኃላፊነት መዉሰድ ይገባል» ብለዋል
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫኔ