1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ2015 ዓም አቀባበል በውጪው ዓለም

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 5 2014

ጦርነት፣ ግድያና ጥቃት፣ መፈናቀል፤ ድርቅ እና የመሳሰሉ ችግሮች ከየአቅጣጫው ሲሰማበት የከረመው 2014 ዓ,ም ለስንብት ደርሷል። ለኢትዮጵያውን አስጨናቂ የነበረው ይኽ ዓመት ለመሰናበት በተቃረበበት ወቅት ዳግም በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት የአዲሱን ዓመት ድባብ አደብዝዞታል።

https://p.dw.com/p/4GeT5
Young Flower Adey Abeba Blumen Äthiopien
ምስል Yohannes Geberegziabeher

የ2015 ዓቀባበል በጀርመን

ጦርነት፣ ግድያና ጥቃት፣ መፈናቀል፤ ድርቅ እና የመሳሰሉ ችግሮች ከየአቅጣጫው ሲሰማበት የከረመው 2014 ዓ,ም ለስንብት ደርሷል። ለኢትዮጵያውን አስጨናቂ የነበረው ይኽ ዓመት ለመሰናበት በተቃረበበት ወቅት ዳግም በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት የአዲሱን ዓመት ድባብ አደብዝዞታል። እንዲያም ሆኖ በአል ያውም ተስፋ የሚሰነቅበት አዲስ ዓመት ነውና ሁሉም እንደየአቅሙና ፍላጎቱ ያከብረዋል። እንደ ሀገር ቤት ሁሉ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትውልደ ኢትዮጵያም በአሉን ማክበራቸው የተለመደ ነው። የዘንድሮው ግን ከሌሎቹ ጊዜያት ይለያል ይላል እዚህ ጀርመን ኑረንበርግ ከተማ ነዋሪ የሆነው አቶ አህመድ አሊ ሲራጅ።

በእርግጥ እንደዘመን አቆጣጠሩ አዲስ ዓመት እየመጣ ነው የሚለው አቶ አህመድ፤ በዋዜማው እየጨፈርን እንደወትሮው ልንቀበው አንችልም ነው የሚለው።  ብዙ ወገኖች በተለይ በዚህ ዓመት  በማንነታቸው በገፍ መጨፍጨፋቸውን በማስታወስም አዲሱን ዓመት በፌሽታ ከመቀበል ይልቅ እነሱን በማሰብ በሻማ ማብራት ሥርዓት እንደሚያሳልፉት ገልጸዋል።

Symbolbild I Kerzen Licht
ምስል privat

አሁንም በማንነታቸው የሚገደሉ ዜጎች መኖራቸውን በማስታወስም በአሉን በሀዘን ለማክበር መገደዳቸውን ገልጸውልናል። ባለፉት ወራት የተለያዩ በዓላትን ለማክበር የነበረው እንቅስቃሴ በዚህ በአዲሱ ዓመት አቀባበል ላይ መቀዛቀዙን እሳቸውም ማስተዋላቸውን የገለጹልን ደግሞ በዋና ከተማ በርሊን የሚኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊው የኤኮኖሚ ባለሙያ ዶክተር ፀጋዬ ደግነህ ለሚታየው የቀዘቀዘ ድባብ የተለያዩ ምክንያቶችን ያነሳሉ። እንደ ዶክተር ፀጋዬ ገለጻ በርካቶች ወደ ሀገር ቤት ሄደው በቅርቡ መመለሳቸው አንደኛው ምክንያት ሲሆን አንዳንድ ቢሆኑ ብለው የተመኟቸው ነገሮች አለመሆናቸው እንዲህ ላለው ጉዞ ያለውን መነሳሳት ሳያቀዘቅዘው እንዳልቀረም ያነሳሉ። ይኽም ብቻም አይደለም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የትኬት ዋጋም የብዙዎችን የበዓል ጉዞ ፍላጎት ማስተጓጎሉንም አንስተዋል። እንዲያም ሆኖ እሳቸውም ሆኑ ሌሎች ወደ ሀገር ቤት አሁን ባይሄዱም በርሊን የሚኖረው ማኅበረሰብ በየእምነቱም ሆነ ሌሎች ማሕበራት ተሰባስቦ አዲሱን ዓመት ለማክበር መዘጋጀቱን ገልጸዋል። የኑሮ ውድነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ፀጋዬ እዚህም ተመሳሳይ መሆኑን እና ይኽንን ተከትሎም ሊከሰቱ የሚችሉ የሥራ ቦታዎች መዘጋት ጋር የተያያዘ እርግጠኛ ያለመሆን ነገርም ሌላው ምክንያት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ከመንግሥት ውጪ ለሚኖሩ ወገኖች የቀረበውን ጥሪ መሠረት በማድረግ የገና በአልን ሌሎችን በማስተባበር ከነቤተሰቦቹ ወደ ሀገር ቤት ተጉዞ ያከበረው በኮሎኝ ከተማ የሚገኘው ፋሲካ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት ባለቤት አቶ ደጀኔ ካሣሁን ለአዲስ ዓመት እዚሁ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር መዘጋጀቱን ገልጾልናል። አብዛኞቹ በ2014 የታዩ ችግሮች ለውጥ ሳያሳዩ ወደ 2015 ለመሸጋገር ቢቃረቡም አዲሱ አመት አዲስ ነውና ይከበራል። መልካም አዲስ ዓመት።

ሸዋዬ ለገሠ