1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: ሁኔታዎች ከቤተሰብ እንድትርቅ ያስገደዷት ተማሪ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሰኞ፣ ጥቅምት 18 2017

የ18 ዓመቷ ናይጎኣ ታይካላ በምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ባለው የፀጥታ ሥጋት የተነሳ ኑሯቸውን በሀዋሳ ካደረጉ ወጣቶች መካከል ናት ፡፡ ወደ ሀዋሳ ከመጣች ሁለተኛ ዓመቷን የያዘችው ናይጎኣ አሁን ላይ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቷን በመከታተል ላይ እንደምትገኝ ትናገራለች ፡፡

https://p.dw.com/p/4mJCe

ሀዋሳ የመጣችው በጋምቤላ ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ የተነሳ እንደሆነ የገለጸችው ናይጎኣ “ እዚህ እንደመጣሁ በመጀመሪያ አካባቢ ሁሉም ነገር አዲስ ነበር የሆነብኝ ፡፡ አካባቢው ፣ ቋንቋ እና ባህሉ ለእኔ አዲስ ነው ፡፡ በሂደት ግን ሁሉን ነገር እየለመድኩ መጣው ፡፡ አሁን ላይ የትምህርት ቤት ጓደኞችን ማፍራት ችያለሁ “ ብላለች ፡፡
ናይጎኣ ከቤተሰቧና ከትውልድ አካባቢዋ ብትለይም አንዳንድ በሩቅ ያሉ ዘመዶቿ በገንዘብ እንደሚደግፏት ትናገራለች ፡፡ ሁኔታዎች ከቤተሰብ እንድትርቅ ቢያስገድዷትም ከትምህርት ሰዓት ውጭ ያለውን ጊዜ በተለያዩ ሁኔታዎች እንደምታሳልፍ የጠቀሰችው ናይጎኣ “ ከትምህርት ቤት ውጭ ባለኝ ጊዜ መጸሀፍትን አነባለሁ ፡፡ የቤት ሥራዎችን እሠራለሁ ፡፡ እንዲሁም መንፈሳዊ መዝሙሮችን ማዳመጥና የቴሌቪዥን ዝግጅቶችን በመከታተል አሳልፋለሁ “ ብላለች፡፡
የመጣችበት የምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢ ግጭቶችና ወባን የመሳሰሉ በሽታዎች እንደሚስተዋልበት የጠቀሰችው ናይጎኣ ወደፊት ወደ አካባቢዋ የመመለስ ዕቅድ እንዳላት ተናግራለች “  ወደፊት ነርስ የመሆን ዓላማ አለኝ ፡፡ በዚህም ማህበረሰቡን መርዳት እፈልጋለሁ ፡፡ እዛ ብዙ ሰዎች በበሽታ ይሞታሉ ፡፡ ወደዚያው ተመልሼ ነገሮችን ማስተካከል አለብኝ “ ስትል የወደፊት ዕቅዷን ገልጻለች፡፡ 
“ እንደእኔ ከቤተሰብ ርቀው ለሚገኙ ወጣቶች መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ “ የምትለው ናይጎኣ“ የማስተላልፈው ምክር በጣም መጎበዝ እንዳለባቸው ነው፡፡ ጠንክረው ትምህርታቸውን በመቀጠል የተሻለ ቦታ መድረስና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ማሸነፍ ይኖርባቸዋል “ ብላለች፡፡

#ዝምታሰባሪአዳጊሴቶች #GirlzOffMute
ዘገባ: ሊሻን ዳኜ 
ቪዲዮ:ሸዋንግዛው ወጋየሁ