1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፍልሰትጀርመን

ወጣቱ ኤርትራዊ የአውቶብስ ሾፌር በቦን

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 23 2015

ሮቤል የኑሮ ደረጃው፣ ቋንቋው፣ ባህሉና ልምዱ ከሀገሩ ከኤርትራ ፍጹም ቢለይም ከጀርመን ባህል ጋር መቀላቀሉ ብዙም አላስቸገረኝም ይላል። ለዚህም ቋንቋ ሲማር ጓደኞቹ ይሰጡት የነበረውና እስካሁን የዘለቀው ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግሯል። ከሰባት ዓመት በላይ ብሩል የሚኖረው ወጣቱ ሮቤል አሁን በቦን ከተማ በአውቶብስ ሾፌርነት ይሰራል።

https://p.dw.com/p/4Vitt
ሮቤልን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት የአውቶብስና የባቡር ሾፌሮች የደንብ ልብስ ለብሶ በከተማ ባቡር ሲሄድ ነበር። ያኔ አብረን ካገኘነው የስራ ባልደረባዬ አዜብ ጋር ስለ ስለርሱ ማንነት በመጠኑም የተረዳነው፣ ይህንንም ቃለ ምልልስ እንዲሰጠን የጠየቅነው በአማርኛ ነግሮን ነው ።
ከሰባት ዓመት በላይ ብሩል የሚኖረው ወጣቱ ሮቤል አሁን ከብሩል ብዙም በማይርቀው ራድዮ ጣቢያችን በሚገኝበት በቦን ከተማ በአውቶብስ ሾፌርነት ይሰራል።  ምስል German Embassy Tirana

ወጣቱ ኤርትራዊ የአውቶብስ ሾፌር በቦን

የ32 ዓመት ወጣት ነው። ጀርመን ከተሰደደ 8 ዓመት ሆኖታል።የወጣቱ የስደት ሕይወት የሚጀምረው ግን ከዛሬ 13 ዓመት አንስቶ ነው። ሮቤል ወልደ ሚካኤል ተወልዶ ካደገባት ከኤርትራ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰደደው በ19 ዓመቱ ነበር። በተሰደደበት ሱዳን ለአምስት ዓመታት ግድም ኖሯል። በአነስተኛ ንግድ ተሰማርቶ የቆየው ሮቤል ሱዳንን ፣እንደ ክርስቲያን በነጻነት መኖር የሚችልባት ሀገር ሆኖ ስላላገኛኃትት እንደገና መሰደድን መረጥኩ ይላል።ከዚያም በአደገኛው የየብስና የባህር ጉዞ ወደ አውሮጳ ለመሄድ ወሰነ ። ከኢትዮጵያና ሶማሊያ እንዲሁም ከሌሎች አገራት ዜጎች ጋር ፣ ከሱዳን ወደ ሊቢያ ፣ ከሊቢያ በሜዴትራንያንን ባህር አድርጎ የዛሬ 8 ዓመት አውሮጳ ደረሰ። እንዲህ በአጭሩ ጠቅለል አድርጌ የተረኩላችሁ የወጣቱ ጉዞ ግን ቀላል አልነበረም። ብዙ የተፈተነበት ሕይወቱንም ለተለያዩ አደጋዎች ያጋለጠበት ጉዞ ነበር። ሮቤል ለዶቼቬለ የአማርኛው ክፍል በጀርመንኛ በሰጠው  ቃለ ምልልስ እጅግ አስቸጋሪ በነበረው በዚህ ጉዞ እርሱና ሌሎች ስደተኞች ብዙ ስቃይ እንደደረሰባቸው ተናግሯል። በነገራችን ላይ ሮቤል በአማርኛ መግባባት ይችላል። ሆኖም ሀሳቡን ይበልጥ አብራርቶ ለመግለጽ ጀርመንኛን መርጧል።

 
«ከባድ ነበር። ከሱዳን ሊቢያ ድንበር ለመድረስ 7 ቀናት ፈጅቶብናል። መንገዱም አስቸጋሪ ነበር። ውሀ አናገኝም። ፀሐዩ ሙቀቱ ከባድ ነበር። በአንድ የጭነት መኪና ላይ የተጫነው ብዙ ሰዎች ነበርን። 100 ያህል ሰዎች ነበርን በአንድ ላይ የታጨቅነው። ትክክለኛ ምግብ አናገኝም ነበር። በተወሰነ ሰዓታት ልዩነት ብስኩት ነበር የምንበላው። ደንበኛ የሚባል ምግብ አናገኝም ነበር።»
በዚህ ዓይነት ጉዞ ለሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች በርካታ ገንዘብ ከፍለው ከሱዳን ወደ ሊቢያ ያቀኑት ሮቤልን ጨምሮ ሦስት ኤርትራውያን እና ሁለት ኢትዮጵያውያን የሚገኙባቸው ቁጥራቸው መቶ የሚሆን ስደተኞች መጨረሻ እስርቤት ሆነ። ቤንጋዚ ሊቢያ ውስጥ ላሰሯቸው ታጣቂዎች ገንዘብ ካልሰጡ ደግሞ ከእስር ቤት መውጣት አይችሉም  ነበር። 
«የሚከፈለው ገንዘብ ብዙ ነው። ለኔ ብዙ ገንዘብ ነበር።ገንዘቡም በእጄ ላይ አልነበረም። የሆነ ቦታ ያሉ ቤተሰቦቼ ገንዘቡን ከፍለውልኝ ነው ከዚያ እስር ቤት ነጻ የወጣሁት። ያልከፈለ ግን እዚያው እንደ እስረኛ ይቆያል። እኔ ከእስር ቤት ለመውጣት ስድስት ወራት ወስዶብኛል። ሆኖም የሌሎቹ ይለያያል። ሁለት ዓመት የቆዩም አሉ።»

የወጣቱ ጉዞ ግን ቀላል አልነበረም። ብዙ የተፈተነበት ሕይወቱንም ለተለያዩ አደጋዎች ያጋለጠበት ጉዞ ነበር። ሮቤል ለዶቼቬለ የአማርኛው ክፍል በጀርመንኛ በሰጠው  ቃለ ምልልስ እጅግ አስቸጋሪ በነበረው በዚህ ጉዞ እርሱና ሌሎች ስደተኞች ብዙ ስቃይ እንደደረሰባቸው ተናግሯል።
የወጣቱ ጉዞ ግን ቀላል አልነበረም። ብዙ የተፈተነበት ሕይወቱንም ለተለያዩ አደጋዎች ያጋለጠበት ጉዞ ነበር።ምስል Fabrizio Bensch/REUTERS


ሮቤልና ሌሎች ገንዘብ የከፈሉ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ በሕገ-ወጦቹ የሰዎች አሻጋሪዎች በድብቅ በመኪና ወደ ሊቢያ ዋና ከተማ ትሪፖሊ ተወስደው ከዚያ በጀልባ ወደ ኢጣልያ ጉዞ ጀመሩ። የጀልባው ጉዞም እንደ ጭነት መኪናው በሰዎች የታጨቀ ነበር። « ከዚያ በኋላም በግምት መቶ የምንሆን ጉዞ ጀመርን። አብዛኛዎቹ ሶማሊያውያን ነበሩ። የተቀረነው ኤርትራውያንና የሌሎች ሀገራት ዜጎች ነበርን። በሁለት ቀናት ተኩል ወይም በሦስት ቀናቱ ጉዞ ብዙም የከፋ የሚባል ችግር ባይደርስብንም፣ ጀልባው መንገድ ስቶ ብዙ በመጓዙ ቤንዚኑ አልቆበት ባህር ላይ ቆሞ በነበረበት ወቅት እንደ አጋጣሚ አንድ የኢጣልያ መርከብ ላምፔዱዛ አካባቢ ደርሶ ታደገን።» በኢጣልያ መንግሥት ትዕዛዝ የታደጋቸው ይህ መርከብ ወደ ኢጣልያዋ የወደብ ከተማ ሲሲሊ ወሰዳቸው። ከትሪፖሊ ሊቢያ በተነሱ በአራተኛ ቀናቸው ኢጣልያ የገቡት ሮቤልና ሌሎች ስደተኞች ጉዟቸውን በባቡር ቀጥለው በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 2015 ዓ.ም. ደቡብ ጀርመንዋ ከተማ ሙኒክ ገቡ። ሙኒክ ሦስት ቀናት ከቆየ በኋላ ወደ ምዕራብ ጀርመንዋ ዶርትሙንድ ከተማ ሄደ ከሦስት አራት ቀናት በኋላ ሀም የተባለችው ከተማ ተወሰደ   በመጨረሻም ኮኒግስቪንተር የተባለችው አነስተኛ ከተማ እንዲኖር ከተደረገ በኋላ በርሱ ጥያቄ  የሀገሩ ልጆች ጓደኞቹ ወደሚገኙበት ብሩል በተባለችው ከተማ መኖር ጀመረ። ከሰባት ዓመት በላይ ብሩል የሚኖረው ወጣቱ ሮቤል አሁን ከብሩል ብዙም በማይርቀው ራድዮ ጣቢያችን በሚገኝበት በቦን ከተማ በአውቶብስ ሾፌርነት ይሰራል። 


«ፍላጎቱ ካለ ይሳካል።ለአራት ዓመታት ጀርመንኛ ቋንቋ ተምሬያለሁ። የተማርኩትም በጀርመን የተገን ጥያቄዬ ይመስለኛል በጎርጎሮሳዊው 2017 ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው።የጀርመንኛውን ቋንቋ ትምህርት ቤ ስቫይ እስከሚባለው ደረጃ ድረስ ተማርኩ። ለአውቶብስ ሾፌርነት የሚያበቃውን መንጃ ፈቃድ ከመያዜ በፊት አንዳንድ ስራዎችን እሰራ ነበር። SWB በሚባለው የቦን የአውቶብስና የባቡር ድርጅት  የአውቶብስ ሾፌር ከሆንኩ አሁን ሁለት ዓመት ተኩል ሆኖኛል።»ወጣቱ ሮቤል የኑሮ ደረጃው፣ ቋንቋው፣ ባህሉና ልምዱ ከተወለደበትና ካደገባት ከኤርትራ ፍጹም ቢለይም ከጀርመን ባህል ጋር መቀላቀሉ ብዙም አላስቸገረኝም ይላል። ለዚህም ቋንቋ ሲማር ጓደኞቹ ይሰጡት የነበረውና እስካሁን የዘለቀው ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግሯል።« አዎ ባህሉ የተለየ መሆኑ ግልጽ ነው። ቋንቋ ስማር ጀርመናውያን ጓደኞቼ ይደግፉን ነበር።በአጠቃላይ አሁንም እየረዱኝ ነው። » ያም ሆኖ ሮቤል በጀርመን የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥመውታል።« ጀርመንኛ ሁለተኛ ቋንቋ መሆኑ ጉዳት አለው። እኔ ብዙ ነገር ተሳክቶልኛል። ሆኖም እዚህ መድረሱ  ቀላል አልነበረም። ቋንቋውን በአንዴ በትክክል መናገር አይቻልም። የአውቶብስ ሾፌር ለመሆን የወሰድኩት ፈተና ለምሳሌ በቋንቋው ምክንያት ከባድ ነበር። ሆኖም በየጊዜው ፣ዓመት ባለፈ ቁጥር ንግግሩም መግባባቱም ይሻሻላል።ሆኖም ተግዳሮቶቹ እንደተባለው ብዙ ናቸው።»
ይሁንና ሮቤል እንደሚለው በስራ ቦታ ግን ብዙም ችግር አልገጠመውም። በስራውም ደስተኛ ነው። «በምሰራበት ቦታ ወጣቶችም ሆነ በእድሜ ትላልቅ የሆኑ ሰዎች አሉ። ያንንም ብዙውን ጊዜ አዎንታዊ ነው የምለው። ሆኖም እንደሚጠበቁት ሆነው የማይገኙ የስራ ባልደረቦች አሉ። ሆኖም በአጠቃላይ ሲታይ መጥፎ አይደለም። ሰው ጥሩ የስራ ባልደረባ ሳይሆን ጥሩ ስራ ነው የሚፈልገው። እኔን  ችግሮች ያጋጠሙኝ በስራ ቦታ አይደለም ይልቁንም ከሰነዶች ጋር በተያያዘ ከስምንት ዓመት አንስቶ ከጀርመን ባለስልጣናት በኩል ችግሮች አጋጥመውኛል።»ሮቤል ከከጀርመን ባለስልጣናት በኩል ገጥመውኛል የሚላቸውን ችግሮች ወደ ኃላ ላይ እንመለስባቸዋለን። ሮቤልን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት የአውቶብስና የባቡር ሾፌሮች የደንብ ልብስ ለብሶ በከተማ ባቡር ሲሄድ ነበር። ያኔ አብረን ካገኘነው የስራ ባልደረባዬ አዜብ ጋር ስለ ስለርሱ ማንነት በመጠኑም የተረዳነው፣ ይህንንም ቃለ ምልልስ እንዲሰጠን የጠየቅነው በአማርኛ ነግሮን ነው ። ሮቤል አማርኛ የተማረው ጀርመን ከመጣ በኋላ ነው። አማርኛ ያስተማረው ደግሞ የዛሬ ስምምነት ዓመት እንደርሱው ጀርመን የተሰደደው ኤርትራዊው አማኑኤል ይስሀቅ የሚባል ጓደኛው ነው። ወዳቆየነው የሮቤል ቅሬታ እንመለስ ። ከዛሬ 8 ዓመት አንስቶ ጀርመን የሚኖረው ሮቤል ለጀርመን ባለስልጣናት ያስገባው አንድ ማመልከቻ እንደጠበቀውና እንደሚፈልገው መልስ አለማግኘቱ ቅር አሰኝቶታል።
«በጀርመን ብዙው ነገር ጥሩ ቢሆንም ግን ኤርትራውያን በሀገሪቱ ባለሥልጣናት ይበደላሉ።ለምሳሌ እኔ 8 ዓመት ጀርመን ኖሬያለሁ ባለስልጣናት አድርጉ እንደሚሉት ቋንቋ ተምሬያለሁ። ቋሚ ስራ አለኝ ስለጀርመን ፖለቲካ ተምሬያለሁ። ሆኖም የጀርመን ዜግነት የማግኘት መብት ቢኖረኝም ባለስልጣናት እስካሁን ጥያቄውን አልተቀበሉም።ለዚህ ያቀረቡት ምክንያት የተለያዩ ሰነዶችን አላሟላህም የሚል ነው። ከኤርታራ ሁሉንም ሰነድ ማግኘት እንደማይቻል ያውቃሉ። ሌላ መንገድ መፈለግ ይገባቸው ነበር። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ እንቅፋት እንዳለ ነው ።»
ሮቤል በተሰጠው ምክንያት ማመልከቻው መልስ አላገኘም ። ይህ ለጊዜው ባይሳካካም  በጀርመን ሁኔታዎች ከተመቻቹለት ስልጠናዎችን በመውሰድ ራሱን ከፍ ወዳለ ደረጃ የማሳደግ ምኞት አለው።  « ምን ሌሎች እድሎች እንዳሉ መመልከት ይኖራል። አሁን የአውቶብስ ሾፌር ነኝ። እስከ ዛሬ   5  ዓመት ውስጥ ምን ሌሎች እድሎች እንዳሉ አያለሁ።ከዚያ በኋላ ተጨማሪ ትምህርቶችን ለመማር ስልጠናዎችን ለመውሰድ እፈልጋለሁ።»

ከዛሬ 8 ዓመት አንስቶ ጀርመን የሚኖረው ሮቤል ለጀርመን ባለስልጣናት ያስገባው አንድ ማመልከቻ እንደጠበቀውና እንደሚፈልገው መልስ አለማግኘቱ ቅር አሰኝቶታል።
ሮቤል አማርኛ የተማረው ጀርመን ከመጣ በኋላ ነው። አማርኛ ያስተማረው ደግሞ የዛሬ ስምምነት ዓመት እንደርሱው ጀርመን የተሰደደው ኤርትራዊው አማኑኤል ይስሀቅ የሚባል ጓደኛው ነው። ምስል cc by-sa Max S.

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ