1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮቪድ 19 አጣዳፊ የዓለም የጤና ችግርነቱ መቀነስ፤ ምን ማለት ይሆን?

ማክሰኞ፣ ግንቦት 1 2015

የዓለም የጤና ድርጅት ካለፈው ሳምንት ዓርብ ማምሻውን ጀምሮ ኮቪድ 19 አጣዳፊ የዓለም የጤና ችግር መሆኑ መቀነሱን አስታውቋል። የድርጅቱ ባለሥልጣናት ከዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት በመላው ዓለም የተሓዋሲውን ይዞታ ባለሙያዎች ሲመረምሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4R6Vm
3D Blue Virus Molecules
ምስል Zoia Fedorova/Zoonar/picture alliance

ኮቪድ 19 አጣዳፊ የዓለም የጤና ችግርነቱ መቀነስ፤ ምን ማለት ይሆን?

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ዓርብ ዕለት ነው የዓለም የጤና ድርጅት ከሦስት ዓመታት በላይ የዘለቀው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አጣዳፊ የጤና ችግርነቱ መቀነሱን ይፋ ያደረገው። የመተንፈሻ አካላት ላይ በሚያደርሰው ጉዳት የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈው የኮሮና ተሓዋሲ በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው መተላለፉ በመላው ዓለም ከፍተኛ የጤና ስጋት ሆኖ ቆይቷል። የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ ወረርሽኙ በተስፋፋበት ወቅት በሳምንት ከአንድ መቶ ሺህ ሰው በላይ ሲፈጅ የከረመው የኮሮና ተሓዋሲ ባለፉት ሳምንታት ግን በተሓዋሲው ምክንያት የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ከአራት ሺህ በታች ወርዷል። ምንም እንኳን ድርጅቱ አሁን የበሽታው አጣዳፊ ስጋትነት መቀነሱን ቢያመለክትም ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በጥንቃቄ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም ተናግረዋል።

«ትናንት የአጣዳፊ ጉዳዮች ኮሚቴ ለአ15ኛ ጊዜ ስብሰባ ካካሄደ በኋላ፤ ዓለም አቀፍ የጤና አሳሳቢነቱ ማብቃቱን ይፋ እንዳደርግ ሃሳብ አቀረበልኝ። እኔም ምክሩን ተቀብያለሁ። ስለዚህ በታላቅ ተስፋ ኮቪድ 19 የዓለም የጤና አጣዳፊ ችግር መሆኑን ይፋ አደርጋለሁ። ሆኖም ግን ኮቪድ 19 የዓለም የጤና ስጋትነቱ አበቃ ማለት አይደለም።»

የኮሮና ተሐዋሲ ተጽዕኖ እንዲቀንስ ካደረጉት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ክትባት መዘጋጀቱ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው 13 ቢሊየን ክትባት በመሰጠቱ በርካቶችን ከከፋው ህመም እና ሞት ለማትረፍ አስተዋጽኦ አድርጓል። እንዲያም ሆኖ እጅግ ብዙ ሃገራት ክትባቱ እንዳልተዳረሰ ነው የሚነገረው። ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ765 ሚሊየን በላይ ሰዎች በተሐዋሲው መያዛቸው ተረጋግጧል።

በመላው ዓለምም ወደ 20 ሚሊየን ገደማ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያትም መሆኑን ነው ድርጅቱ ያመለከተው። ምን እንኳን ኮቪድ 19 የዓለም አጣዳፊ የጤና ስጋትነቱ ቀንሷል ቢባልም፤ አሁንም ግን ተሓዋሲው አደገኛነቱ እንዳለ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አሳስበዋል።

WHO Logo
የዓለem የጤና ድርጅት አርማ

«ባለፈው ሳምንት ኮቪድ 19 በየሦስት ደቂቃው ሕይወት ቀጥፏል፤ ያ ደግሞ የምናውቀው ሞት ነው። አሁን እኛ እየተነጋገርን በመላው ዓለም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጽኑ ሕሙማን ክፍል ነፍስ ውጪ ግቢ ትግል ላይ ናቸው። እንዲሁም ሚሊየኖች በኮቪድ 19 ከተያዙ በኋላ በሚያስከትላቸው አስከፊ ተጽዕኖዎች ጋር መኖር ቀጥለዋል።»

የኮሮና ተሓዋሲ በበርካታ ሃገራት መዛመትን ተከትሎ ስርጭቱን ለመግታት የተለያዩ ጥረቶ ሲደርጉ ታይተዋል። በተለይም አውሮጳ ውስጥ በጣሊያን በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ላይ የታየው የሰዎች አስከፊ ሞት እና የጅምላ ቀብር በመላው ዓለም አስፍኖት የነበረው የፍርሃት ድባብ በቀላሉ የሚዘነጋ አይደለም። ወቅቱም ለወትሮ በትብብር ይጎዳኙ የነበሩ ሃገራት የየግል ድንበሮቻቸውን ያለ ይሉኝታ በሌላው ላይ ለመዝጋት ያላመነቱበትም ነበር። በዚህ ጊዜም ነበር እያንዳንዱ ሀገር ስንት ለጽኑ ሕሙማን የሚሆኑ የተሟሉ ክፍሎች እንዳሏቸውም ታይቷል።

በኤኮኖሚ አቅማቸውን የጠነከሩት እና ዘመናዊው የህክምና መሠረተ ልማት በተስፋፋቸው ሃገራት ያደረሰውን ተጽዕኖ በመመልከትም ደካማ የህክምና አቅርቦት ባለባቸው የአፍሪቃ ሃገራት ሊደርስ የሚችለው እልቂት ብዙዎችን አነጋግሯል። የተሰጋውን ያህል ግን አልሆነም። ለዚህ ደግሞ አንዳንድ የህክምና ባለሙያዎች ሰዎች ከተሓዋሲው ጋር እንዲላመዱ ዕድል እንደፈጠረ ሲናገሩ ገሚሱ ደግሞ የአየር ጠባይ ይዞታው ትልቅ ሚና እንደተጫወተ ይገምታሉ።

ያ ሁሉ ስጋት እና ጭንቅ፤ የእንቅስቃሴ ገደብ፤ የምርመራ ግዴታ፤ ውሎ አድሮም ክትባቱን ለመውሰድ የተደረገው ግፊት ሁሉ አልፎ ሦስተኛ ዓመቱን ካገባደደ በኋላ ኮቪድ 19 ከባለፈው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ የየሃገራትን አቅም ያሟጠጠው ጉልበቱ የመቀነሱ መረጃ ተሰምቷል። የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ምንም እንኳን በይፋ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መከሰቱን ባወጁበት መንገድ አሁን ኮቪድ 19 አጣዳፊ የዓለም ጤና ችግር መሆኑ አብቅቷል ቢሉም ኅብረተሰቡ እንዳይዘናጋ ግን አሳስበዋል።  

«ይኽ ተሓዋሲ እዚሁ የሚቆይ ነው፤ አሁንም እየገደለ ነው። አሁንም መለዋወጡንም ቀጥሏል። አዲስ ልውጥ ተሓዋሲ የመፈጠሩም ሆነ የታማሚዎች ቁጥር መጨመርም ሆነ የሞት ስጋትም እንዳለ ነው።»

Tedros Adhanom Ghebreyesus | WHO Generaldirektor
ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም፤ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርምስል Fabrice Coffrini/AFP/Getty Images

ይኽ በእንዲህ እንዳለም ከቀናት በፊት የኮቪድ 19 ክትባትን ስለመከተብ እንደ አዲስ መቀስቀስ በጀመረችው ኢትዮጵያም፤ የጤና ሚኒስቴር የዓለም የጤና ድርጅትን እወጃ ተንተርሶ የራሱን መግለጫ አውጥቷል። የጤና ሚኒስቴር በመግለጫው ምንም እንኳን ኮቪድ 19 አጣዳፊ የጤና ችግር አይደለም ቢባልም አሁንም በርካቶች እንደ ሳርስ እና COV 2 በተባሉት ተሐዋሲዎች እየተያዙ እንደሆነና ብዙዎችም ለሞት እየተዳረጉ እንደሆነ በመግለጽ ኅብረተሰቡ እንዳይዘናጋ አሳስቧል።

ኮቪድ 19 ላለፉት ሦስት ዓመታት መላውን ዓለም ያሰጋ ወረርሽኝ መሆኑ ይፋ ተደርጎ የጥንቃቄ እርምጃዎች ሲወሰዱ ከርሟል። አሁን ከዓለም የጤና ድርጅት የተላለፈው መልእክት በእርግጥ ምን ማለት ይኾን? ዶክተር አስቻለው ወርቁ የሳንባ ከፍተኛ ሀኪም ሲሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ኮቪድ 19ን በሚመለከተው ኮሚቴም አባል ናቸው።

«አሁን የስርጭቱ መጠን በንጽጽር ሲታይ በፊት ከነበረበት ቀነስ አድርጓል፤ በጽኑ ህክምና ውስጥ ታመው የተኙት ከበፊቱ ሲታይ አሁን ቀነስ አድርጓል፤ የሟቾች ቁጥር አሁንም አለ ግን ከበፊቱ ጋር ሲተያይ የተሻለ ደረጃ ላይ ነው ያለው። በቆይታው ባለው ልምድ በመደበኛው የጤና አገልግሎት ሃገራትም ሁኔታውን መከታተል መቆጣጠርና ማከም ይችላሉ ተብሎ የሚታሰብበት ደረጃ ላይ ስለደረሰ  ባለፈው ሜይ 5 የዓለም የጤና ጥበቃም እኛም ትናንት ይኽን መግለጫ አውጥተናል። ይኽ ማለት ምን ማለት ነው፤ ስርጭቱ ተቋርጧል፤ የሚሞት ሰው የለም ማለት አይደለም፤ የታመመ የለም ማለት አይደለም፤ ሁለተኛ በቀጣይም በሚኖረው ስርጭት ልውጥ ዝርያ ሊፈጠር አይችልም ማለትም አይደለም።» 

Frankreich Lyon | Coronavirus Impfstation
የኮቪድ 19 ክትባትምስል JEFF PACHOUD/AFP

የኮሮና ተሓዋሲ ስርጭትን ለመከላከል በሚል የተደነገጉ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ጀርመንን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት እየላላ ሄዶ ጭራሽ ከቀረ ሰነባበተ። በዚህ መሀል ግን በኮሮና ተሐዋሲ የሚያዙ፤ ጠንከር ባለ ጉንፋን ተይዘው የሚሰቃዩ እና የተሰቃዩ ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም። ይኽን ያስተዋሉ ታዲያ ዛሬም ሰዎች በተሰቡበት ቦታ ሲገኙ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የሚያደርጉ፤ ርቀታቸውን ለመጠበቅ የሚሞክሩም አሉ። ዶክተር አስቻለው አሁንም መዘናጋት እንደማይገባ ያሳስባሉ። ከዚህ በተጨማሪ ጊዜውን እየተጠበቀ የሚሰጠውን መግለጫ በማዳመጥ ኅብረተሰቡ እራሱን እንዲጠብቅም መክረዋል። 

የዓለም የጤና ድርጅት ኮቪድ 19 አጣዳፊ የዓለም የጤና ችግርነቱ መቀነሱን ይፋ ቢያደርግም ሁኔታው ተለውጦ ከተባባሰ ዳግም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አጽንኦት ሰጥቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን ከ44 ሚሊየን በላይ ዜጎች የኮቪድ 19 ክትባትን አንድ ጊዜ መውሰዳቸውን፤ ሁለት ጊዜ የተከተቡት ከ37 ሚሊየን እንደሚበልጡ፤ እንዲሁም ከሦስት ሚሊየን የሚልቁት ደግሞ ማጠናከሪያውን ጭምር መከተባቸውን የጤና ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። ለሰጡን ማብራሪያ ዶክተር አስቻለው ወርቁን እናመሰግናለን፤ ኮቪድን በተመለከተ ያላችሁን የግል ተሞክሮም ሆነ አስተያየት ለማስተናገድ ዝግጁነን። በፌስቡክም ሆነ ቴሌግራም ጻፉልን፤ ሃሳባችሁን አካፍሉን።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ