የኬንያውያን ተቃውሞና የመንግሥት ምላሽ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 15 2016ከትናንት በስተያ ሐሙስ በመላው ኬንያ የተካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎም ከመቶ የሚበልጡ ዜጎች መታሠራቸውም ነው የተነገረው። ፖሊስ የተቃውሞ ሰልፈኞቹን ለመበተን በዋና ከተማ ናይሮቢ አስለቃሽ ጭስና ውኃ መጠቀሙን አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ አምስት የመብት ተሟጋች ድርጅቶችና የኬንያ የየሀኪሞች ማህበር በጋራ ባወጡት መግለጫ ይፋ አድርገዋል። ጥይትም በዚህ ወቅት ጥቅም ላይ መዋሉን የጠቆሙ ሲሆን በተተኮሰ ጥይት የተመታ ሰው ሕይወቱ ማለፉን የኬንያው ዘ ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል።
በመላ ኬንያ ተቃውሞ የቀሰቀሰው የሀገሪቱ መንግሥት ያጸደቀው የተለያዩ ንብረቶች ላይና የገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ የሚጣል ቀረጥ እንዲሁም ዳቦ እና የምግብ ዘይት ላይ የተደረገ የዋጋ ጭማሪ ነው። ከትናንት በስተያ ሐሙስ ዕለት ናይሮቢ ጎዳናዎች ላይ ለተቃውሞ የወጡት አብዛኞቹ ኬንያውያን ወጣቶች የመንግሥት እርምጃ ያለውን የኑሮ ውድነት እንደሚያባብስ በመግለጽ ባስቸኳይ ሕጎቹን እንዲሰረዙ ጠይቀዋል።
«ግብር እየከፈልን ነው፤ በከፈልነው ልክ ግን የሠሩት እዚህ ግባ የሚባል ነገር የለም እየተዘረፈ ነው፤ እና እንዴት ነው ተጨማሪ ገንዘብ ለመክፈል የምናምናቸው?»
የሚለው በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ኪነጥበብ ላይ የሚያተኩሩ ይዘቶችን የሚፈጥረው ማኬና ካሁሃ ነው። የሕዝቡን ቅሬታና ብሶት ባደባባይ ለመግለጽ ከወጡት የተቃውሞ ሰልፈኞች አንዱ የሆነው ካሁሃ ጀነሬሽን Z የተሰኘው ንቁ የኬንያ ወጣቶች የተሰባሰቡበት ቡድን አካል ነው።
ጄነሬሽን Z
ደፋር ወጣት ተቃዋሚዎችን ያቀፈው ጀነሬሽን Z ወይም በአጭሩ ጄን Z የተሰኘው ቡድን ከጎርጎሪዮሳዊው 1990 እስከ 2000 ዓም የመጀመሪያ ወራት ውስጥ የተወለዱ ወጣቶች የተሰባሰቡበት ቡድን ነው። ወጣቶቹየኬንያ መንግሥት ችግሮቹን በዜጎች ላይ የሚጭንበት አካሄድ እንዳስቆጣቸው ይናገራሉ። ሌላኛዋ የዚህ ስብስብ አባል ፓሜላ ሙሪውኪም በሀገሪቱ መንግሥት እርምጃዎች አለመደሰቷን ነው የምትገልጸው።
«መርጦ ሥልጣን ላይ ላስቀመጣቸው ሕዝብ ከማሰብ ይልቅ ለሌሎች መንግሥታት ታማኝነታቸውን ለማሳየት ይመርጣሉ።»
ኬንያ ውስጥ ከዚህ ቀደም ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባደረጉት ቅስቀሳ ከተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ጋር ሲነጻጸርም አደባባይ የወጣው ሕዝብ በወጣቶቹ እየተመራ ፀረ መንግሥት መፈክሮችን እና እንዲሰረዝ የጠየቃቸውን ሕጎች በማመልከት ደማቅ ሰልፍ አካሂዷል።
የመንግሥት ምላሽ
የተጣለውን ግብርና የዋጋ ንረት ያስከትላል በሚል ሕዝቡ የሰጋበትን ሕግ ለመቃወም የተካሄደው ሰልፍ ከዚህ በፊት ኬንያ ውስጥ ከተደረጉ ሰልፎች የተለየ ነው። በአሁኑ ሰልፍ ወጣት የተቃሞ ሰልፉ ተሳታፊዎች ከፖሊሶች ጋር የተረጉ ግጭቶችን በስልኮቻቸው እየቀረጹ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ አውጥተዋል። የተቃውሞው መሪ ቃል «ፓርላማውን መቆጣጠር» የሚል ሲሆን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት በመላ ሀገሪቱ ተዳርሷል። ከሀገሪቱ 47 ግዛቶች በ19ኙ ተቃውሞ ተካሂዷል። እናም ስኬታማ ተቃውሞ ነው የሆነው። ሐሙስ ዕለት የተጠናከረውን ተቃውሞ ያስተዋለው የፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ መንግሥት ከሕጉ ውስጥ በዳቦም ሆነ የመኪና ባለቤትነትን አስመልክቶ የወጡ ግብሮችን ጨምሮ አብዛኞቹን ደንቦች እንደሚሰርዝ ይፋ አደረገ።
ኬንያ የኮሮና ተሐዋሲ ወረርኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከዋጋ ንረት ጋር እየታገለች ያለች ሀገር ናት። የዓለም የገንዘብ ድርጅት IMF የኬንያ መንግሥት ብድርን ለመቀነስ የዘንድሮና የመጪው ዓመት ገቢውን እንዲያሳድግ አሳስቦታል።
የበለጠ ተጠያቂነት እንደሚያስፈልግ
ኬንያ ውስጥ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የበኩሉን ተነሳሽነት ይዞ የሚሠራው የማኅበራዊ ተጠያቂነት ተቋም አስተባባሪ እንደሚሉት የሰሞኑ የተቃውሞ ሰልፍ ሰላማዊ ነው። ዋንጂሩ ጊኮንዮ እንደሚሉትም ወጣቶቹ ያስተባበሩት መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳረፍ የቻለው የግብር ጭማሪን የተቃወመው ሰልፍ በፖለቲከኞቹ ከሚደረገው የተሻለ ነበር።
«ሰልፎቹ ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ነበሩ። በጣም ፈጠራ የታከለባቸው ድምጾች ፤ በጣም ኪነጥበባዊ ነበሩ። የሚያሳዝነው ፖሊስ በዚህ ለዜጎች እጅግ ወሳኝ የሆነ የሕግ ጉዳይና፤ የግብር ድንጋጌን ለመቃወም በወጡ ወጣቶች ላይ ኃይል ተጠቅሟል።»
ኬንያውያን ሰላማዊ ናቸው የሚሉት ጊኮንዮ እስከዛሬ የሚታዩት አመጽ የተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎች በፖለቲካው መድረክ የተቀሰቀሱ እንደሆኑ እንዲረዱት እንዳደረጋቸውም አልሸሸጉም።
እንደእሳቸው ሁሉ በወጣቶች ብቃት ላይ የሚሠራው አማሊ የተሰኘው ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ዛሃን ኢንዲሙሊም እንዲሁ በሰላማዊ መንገድ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎች ላይ የሚወሰድ እርምጃ የመንግሥትን አለመብሰል ያሳያል ነው ያሉት።
«ምላሽ በሰጠህ ሕዝብ ላይ ለምንድነው አስለቃሽ ጭስ የምትወረውረው? ይህ መንግሥት ውስጥ ያለውን አስተሳሰብ እና አለመብሰል የሚያሳይ ነው፤ ዓለምን ከመዞር ይልቅ ሥልጣን ላይ ካስቀመጣቸው ሕዝብ ጋር ተቀምጠው ሀገር ውስጥ ያለውን ችግር ማስተካከል አለባቸው። መጀመሪያ ቤትህን አስተካክል ከዚያም ወደሀይቲም ሆነ ሌላ ጋ ሄደህ የተበላሸውን ማስተካከል ትችላል፤ በቅድሚያ ግን ቤትህን አስተካክል።»
እሳቸው እንደሚሉት ፕሬዝደንት ሩቶ በአካባቢውም ሆነ በዓለም ደረጃ እራሳቸውን ተፈላጊ ለማድረግ እየሞከሩ ነው። አሁን በኬንያ የታየው ዓይነት ሕዝባዊ ተቃውሞ ደግሞ ገጽታቸውን ያበላሻል። እሳቸውም ሆኑ ሌሎች በሀገሪቱ የሚታየው የፋይናንስ ቀውስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ተረድተዋል፤ የሀገሪቱ መንግሥታት የወሰዱት ኃላፊነት የጎደለው ብድር ነው። ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ የዛሬ ሁለት ዓመት ወደ ሥልጣን ሲመጡ መንግሥታቸው ትርፋማ ባልሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ብዙ ገንዘብ ማፍሰሱንም አጥብቀው ይተቻሉ። ዊልያም ሩቶ በቅርቡ ግብር ለመቀነስ ቃል ገብተው ነበር ነገር ግን ያደረጉት ተቃራኒውን ነው። ይህም ሀገራዊ ተቃውሞውን ቀሰቀሰ። አሁን ያወጡትን ሕግ እንደሚዘርዙ ተናግረዋል፤ ተግባራዊ ካላደረጉት ግን ኬንያውያን ወጣቶች «ዓርላማውን ለመቆጣጠር» የቆረጡ መሆናቸውን እየገለጹላቸው ነው።
ሸዋዬ ለገሠ/ማርቲና ሺቭኮቭስኪ