1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከፕሪቶሪያ መልስ ላቅ ያለው ተስፋ እና ትንሹ ስጋት

ሰኞ፣ ጥቅምት 28 2015

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ግጭት ያስቆማል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። በሌላ በኩል ግን የስምምነቱ ገቢራዊነት ለአፈጻጸም ያስቸግር ይሆን በማለት ስጋታቸውን የገለጹም አልጠፉም።

https://p.dw.com/p/4J9yv
Ätiopien  Tigray  Meeting Nairobi
ምስል African Union

የድርድሩ ስምምነት፤ ተስፋ እና ስጋቱ

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ግጭት ያስቆማል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል። በአፍሪቃ ኅብረት አሸማጋይነት በሁለቱ ወገኖች መካከል ግጭቱን ለማስቆም ያስችላል ያሏቸውን አንኳር ጉዳዮችን ያካተቱበትን የስምምነት ሰነድ በተወካዮቻቸው አማካኝነት በይፋ ተፈራርመዋል። የሰላም ስምምነቱ መደረስ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሃገራት እና ዓለማቀፍ ተቋማት ጭምር በደስታ ሲቀበሉት ለተግባራዊነቱ ተስፋቸውን እየገለጹ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን የስምምነቱ ተግባራዊነት ለአፈጻጸም ያስቸግር ይሆን በማለት ስጋታቸውን የገለጹም  አልጠፉም። በስምምነት ሰነዱ በግልጽ መካተት ነበረባቸው የተባሉ ጉዳዮች እንዳሉም ይነገራል። ሰላም ጤና ይስጥልን አድማጮቻችን ከፕሪቶሪያ መልስ የስምምነቱ ተስፋ እና ሊገጥመው የሚችል ተግዳሮቶች የዕለቱ ማኅደረ ዜናችን ርዕሰ ጉዳይ ነው ፤ አብራችሁን ቆዩ። 
ድፍን ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵሽ ደም አፋሳሽ ጦርነት በስተመጨረሻ ተፋላሚዎች ለሰላም እጃቸውን የሰጡ ይመስላሉ። ተደራዳሪ ወገኖች ለስምምነትም ሆነ ተግባራዊ ለማድረግ እጅግ የሚከብዱ የሚመስሉ ጉዳዮችን ጭምር ለመቀበል መስማማታቸው ጦርነቱ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ ተስፋ አጭሯል። 
ባለፈው የነሐሴ ወር በድጋሚ ያገረሸው እና አሁን በትግራይ ክልል ውስጥ በርካታ ከተሞችን በመንግስት ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንዲገባ በማድረግ የኃይል ሚዛን ያዛባው ጦርነት በፕሪቶሪያው የድርድሩ ውጤት ላይም በግልጽ ተጽዕኖ ያሳደረ ይመስላል። 
የሆነ ሆኖ በድርድሩ መቋጫ የሁለቱ ወገኖች ፊርማ ያረፈበት  ሰነድ ካካተታቸው ነጥቦች ውስጥ የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ የሚፈቱበት እና የፌደራል መንግሥት የትግራይ ክልልን የሚቆጣጠርበት ዝርዝር ሁኔታ ይገኙበታል። ሁኔታው ድጋፍ እና ተቃውሞ እንዲያስተጋባ አድርጓል። በውጭ ሃገራት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በሳምንቱ መጨረሻ ለተቃውሞ አደባባይ እንዲወጡም አስደርጓል። ባለፈው ሐሙስ አርባ ምንጭ ከተማ ስቴዲየም ለተሰበሰበ ህዝብ ስምምነት መደረሱን  በተመለከተ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው መንግስታቸው ያቀረበው ሃሳቦች ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ማግኘቱን ተናግረዋል።
«ደቡብ አፍሪካ ላይ በነበረው ድርድር ኢትዮጵያ መቶ በመቶ ያቀረበችው ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቷል።»ለሰላም ስምምነቱ የአፍሪቃ ኅብረት የተጫወተው ሚና
የስምምነቱ የፊርማ ስነ ስረዓት በይፋ ሲከናወን በእርግጥ ለብዙዎች ትንግርት መፍጠሩ አልቀረም። በትግራይ ፤ አማራ እና አፋር ክልሎች ጦርነቱ ጥሎት ያለፈው ጥቁር ጠባሳ እንዲሁ በቀላሉ የሚሽር ባይሆንም ከዚህም የከፋ ጥፋት እንዳይከሰት ባለበት መገታቱ ግን ለኢትዮጵያውያን የማይተካ አማራጭ ነው። 
ለዚህም ነው ከመቀሌ እስከ አዲስ አበባ ፤ ከባሕር ዳር እስከ ሐዋሳ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ነዋሪዎች ስምምነቱ መልካም ነገር ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ነው ተስፋቸውን የገለጹት ። 
«ትጃለም እባላለሁ ፤ መቀሌ ፤ እኔ ደስ ብሎኛል። ዝርዝሩን በኋላ የምናየው ነው የሚሆነው ። እስካሁን ባለው ሁኔታ ግን ተኩስ ይቁም ፣ የሰብአዊ እርዳታ ይግባ እና የመሳሰሉ ነገሮችን ያየዘ ነው። የትግራይ ህዝብ ብዙ ጊዜ ሲጠይቅ የነበረው እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን ነው። »
«ጉዳዩን የምመለከተው እንደሴት ነው ጦርነትን አልደግፍም ። እንደዚሁም ተከትሎ የሚመጡትን ውጤቶች ደግሞ አጥብቄ እቃወማለሁ። ስለዚህ ከዚህ አንጻር የተደረገው ስምምነት የሴቶች እና የህጻናትን ስቃይ ያስቆማል፤ ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል ብዬ አስባለሁ።»
«በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝ አስተያየት ትልቁ ነገር ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ሰላም ስለሆነ በመጀመሪያ ያንን ሰላም ማስቀደማቸው ደስ የሚል ዜና ነው።»
በእርግጥ ይህ የብዙዎች ተስፋ ፣ ምኞት እና ፍላጎት ነው። ጦርነት ገዳይ ነው፤ ጦርነት አውዳሚ ነው፤ ጦርነት የሀገር ጠር ነው። ጦርነት እና ጦረኝነት መጨረሻቸው ዕልቂት እና ውድቀት ነው። በእውነቱ ከሆነ ይህ ለኢትዮጵያውያን ሊነገር ባልተገባ ነበር። ኢትዮጵያውያን ከባዕዳን ጋር ካደረጉት ጦርነት ይልቅ እርስ በእርሳቸው የተዋጉበት  የቅርብ ጊዜ አስከፊ ታሪካቸው ነው። በዚህ የእርስ በእርስ የጦርነት ታሪክ ጥላቻ ፣ ቁርሾ እና ቂም በቀል ተዘርቷል። ዘረኝነትን አንግሷል፤  ወንድም ወንድሙን ለማሸነፍ አንዱ በሌላኛው ያልፈጸመው ግፍ አልነበረም ፤ መጨረሻው ግን አሸናፊ የሌለበት ይልቁኑ ትናንትን መለስ ብሎ በጸጸት ማስታወስ ሆኗል። የተፈረመው የሰላም ስምምነትና ተግባራዊነቱ
የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በድርድር መቋጨት በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ግጭቶች ዕልባት እንዲያገኙ መንገድ ሊጠርግ እንደሚችል የሚገልጹ አሉ። ነገር ግን አሁንም ድረስ የሰላም ስምምነቱ ሰነድ የያዛቸው ዝርዝር ጉዳዮች ግልጽ አልተደረጉም የሚሉ እና በሰነዱ ውስጥ መካተት ነበረባቸው የሚሉ ጉዳዮችን በተመለከተ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ አንድ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ እንደሚሉት የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል ስለመውጣት ጨምሮ ለአፈጻጸም ያስቸግራሉ ያሏቸውን እና በስጋት የተመከቷቸውን ጉዳዮች አንስተዋል። 
«አሁን ስምምነቱ ላይ እንደሰማነው ፤ ስለኤርትራ ጉዳይ የሚጠቅስ ነገር የለም ። ኤርትራ እንዴት ነው የሚሆነው ፤ አሁን ኤርትራ ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ፣ ትግራይ ውስጥ ገብቶ እያመሰ፣ ሰው እየገደለ በጣም ብዙ ዘግናኝ ግፍ እያደረሰ ነበር። ነገር ግን ስምምነቱ ላይ አልተጠቀሰም። ስለዚህ ዝርዝሩ እንዴት ነው የሚሆነው ፤ አፈጻጸሙ እንዴት ነው የሚሆነው የሚለው ጥርጣሬ አለን።»የሰላም ስምምነቱ ተስፋና ጥርጣሬ
በእርግጥ ነው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተሳታፊ መሆኗ በተደጋጋሚ ስሟ የሚነሳው የኤርትራ ወታደሮች ጉዳይ በስምምነቱ ውስጥ አልተጠቀሰም። ይህ ምናልባትም በስምምነቱ ሰነድ ውስጥ የሰፈሩ ጉዳዮች በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ ከሚጠቀሱ ተግዳሮቶች አንደኛው እንደሆነ ሲገለጽ ይሰማል።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ባለፈው ዓርብ በትዊተር የማኅበራዊ የመገናኛ አውታራቸው ባሰራጩት መልዕክት ከፕሪቶሪያው ስምምነት ያፈነገጡ ይዘቶችን የያዙ ረቂቅ ሰነዶች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል። ይህ በመንግስት የመገናኛ ብዙኃን ጭምር ተዘግቧል። አምባሳደር ሬድዋን በዚሁ የትዊተር መልዕክታቸው ለዘጠኝ ቀናት ያህል ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ሲደረግ ቆይቶ በፊርማ የተቋጨው ስምምነት «የተፈረመው ከበርካታ እልህ አስጨራሽ እና ውጣ ውረድ የበዛበት የቡድን ክርክሮች እና ንግግሮች በኋላ መሆኑን መገንዘብ ይገባል» ብለዋል። 
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን  ሁለቱ ወገኖች ተስማምተው ከተፈራረሟቸው የስምምነት ሰነድ የተለየ ሃሳብ የሰፈረባቸው ረቂቆች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መሰራጨታቸውን ባመለከቱበት በዚሁ የትዊተር መልዕክታቸው «ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ ሊሰጥ ይችላል» ብለዋል። ትክክለኛ ያሉትን የስምምነት ሰነድም በትዊተር ገጻቸው አጋርተዋል።  በስምምነት ሰነዱ ውስጥ ያልተካተቱ ጉዳዮችን ሳይዝ ተሰራጨ የተባለው ሰነድ ውስጥ የተካተቱን ጉዳዮችን በተመለከተ ግን በዝርዝር ያሉት ነገር የለም። ከህወሃት ባለስልጣናት በኩል ስለጉዳዩ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልተሰጠበትም። 
 ይህ በእርግጥ አንድ ግልጽ መሆን ሲገባ ያልተደረገ ነገር እንዳለ ያጠይቃል። ከጦርነት ጉሰማ እስከ «ለሰላም» እጅ መጨባበጥ
ኔዘርላንድስ ዘሄግ በሚገኘው የዓለማቀፍ የዴሞክራሲ እና የምርጫ ድጋፍ ተቋም ውስጥ የሰላም እና የሕገ መንግስት ግንባታ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶ/ር አደም ካሴ ይህንኑ የሚያጠናክር ሃሳብ ነው ለዶይቼ ቬለ የሰጡት። ስምምነቱ በአጭር እና በረዥም ጊዜ ውስጥ የሚገጥሙት ተግዳሮቶች አሉ ባይ ናቸው ።
«እንግዲህ አሁን ከፍተኛ ችግር ሊሆን የሚችለው በተለይ በህወሃት ላይ ካለበት ጫና ከዚህ በፊትም ደግሞ በትግራይ ህዝብ ላይም ተፈጽመዋል ተብለው ከሚነገሩ አንዳንድ ነገሮች  አንጻር የኤርትራ ወታደሮች ወደ ድንበሩ ካልተመለሱ በህወሓት በኩልም ትጥቅ የመፍታት ሂደቱ ላይ ሊያስተጓጉል ይችላል።»
የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ወይም ካርድን በኃላፊነት የሚመሩት አቶ  በፍቃዱ ኃይሉ በበኩላቸው ተግዳሮት ያሉትን እንዲህ ያብራራሉ።
«መስማማታቸው በራሱ ራሱ አንድ ርምጃ ስለሆነ ነው እንጂ ብዙዎች በደስታ የተቀበሉት እና ያበረታቱት ወደ ተግባር መቀየሩ ቀላል ነገር አይደለም። ምክንያቱም ብዙ ደረጃዎች አሉት፤ ለምሳሌ ትጥቅ የማስፈታት እና ከህብረተሰቡ ጋር መልሶ እንዲዋሃዱ ማድረግ እና ሌሎቹም፤ በዚህ ጉዳይ ብዙ ያለመተማመን አለ ፤ ጦርነት ከሚያስከትላቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ያለመተማመን ጉዳይ አለ።»
ይህ ብቻ አይደለም የስምምነቱን ተፈጻሚነት በጊዜ ሂደት ሊያስተጓጉል የሚችል ሌላ ተግዳሮትም አለ።  እንደ ዶ/ር አደም ካሴ በሰሜን ኢትዮጵያ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ አንዱ እና ውስብስብ ነገር ግን መፍትሄ የሚሻ ጉዳይ ነው። 
«በረዥሙ ሲታይ ከፍተኛ እና ውስብስብ ሆኖ የሚታየው የመሬት ጉዳይ ነው። የመሬቱ ጉዳይ እንግዲህ አሁን ባለው ሁኔታ ግልጽነት ያንሰዋል። በተለይ  በሕገ መንግስቱ መሰረት ይፈታል ሲባል ምን ማለት ነው? ይሄ ማለት ወደ ትግራይ ተመልሶ ከዚያ በኋላ ነው ንግግሩ የሚጀመረው ወይስ ምናምን የሚሉ እሳቤዎች አሉ።»
ለስምምነቱ ተግባራዊነት ተግዳሮቶች ሊገጥሙ ይችሉ ይሆን በሚል በህዝቡም ሆነ በባለሞያዎች አስተያየት ቢሰጥበት ጦርነቱ ካስከተለው ጥፋት አንጻር አይበዛበትም። 
የስምምነቱን መደረስ ሃገራት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት በደስታ መቀበላቸውን ዐስታውቀዋል። በዚያው ልክ ጦርነቱ ባደረሰው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠያቂነት እንዲኖር እና ስምምነቱ በአስቸኳይ ተፈጻሚ እንዲሆን የሚጠይቁ ድምፆችም እየተበራከቱ ነው። 
በኢንዱስትሪ የበለጸጉት የቡድን ሰባት አባል አገራት የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ሕወሓት ባለፈው ረቡዕ በደቡብ አፍሪካ የተፈራረሙትን ሥምምነት «ሙሉ በሙሉ አክብረው እንዲተገብሩ» ጥሪ አቅርበዋል። በጦርነቱ ውስጥ ሰብአዊ በደል የፈጸሙ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ያሳሰቡት ሃገራቱ «ከጥቃት የተረፉ ሰዎች እና ተጎጂዎች ፍትኅ ማግኘት እንዳለባቸው» ገልጸዋል።
የሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ግጭት የማቆም ሥምምነት «ተጨማሪ የጭካኔ ተግባራት እና ሰብአዊ ቀውስን ለማስወገድ ለአፋጣኝ እና ጥብቅ ዓለም አቀፍ ክትትል ዕድል» እንደሚፈጥር ያስታወቀው ደግሞ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሒውማን ራይትስ ዎች ነው። የተቋሙ የአፍሪካ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር ካሪን ካኔዛ ናንቱልያ ባለፈው ሐሙስ በሰጡት መግለጫ ቀጣዩን ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ጽፏል።  
«ከሁለት ዓመት ግድም የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ የግጭት ማቆም ውሳኔው የጭካኔ ተግባራትን እና የሚሊዮኖችን ጥልቅ መከራ ለማቆም ወሳኝ ጊዜ» 
የሥምምነቱ ቁልፍ ደጋፊዎች የሰላማዊ ሰዎችን ደሕነት ጥበቃ እንዲያስቀድሙ፣ ለጥብቅ ክትትል ግፊት እንዲያደርጉ እና የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ባለሥልጣናት በመብቶች ጉዳይ የገቡትን ቃል ማክበራቸውን እንዲያረጋግጡ ሒውማን ራይትስ ዎች አሳስቧል።
የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና ሕወሃት መካከል የተደረደው ስምምነት በእርግጥ ተፈጻሚ መሆን ሊጀምር ይሆን የሚል ተስፋ ያስጫረው ዛሬ ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ የሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የጦር አመራሮች የሚያደርጉት ንግግር ውጤት ተጠባቂ ነው።
ሁለቱ ወገኖች የደረሱትን ስምምነት በእርግጥ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው ለሚታየው ግጭት መፍትሄ ለማበጀት መሰረት ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል። ድህነት ለተንሰራፋባት ሀገር ጦርነት እና ግጭት ሲታከልበት በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ ሆኖ ሕዝቡ በምሬት የተሞላ ኑሮ እንዲገፋ አስገድዶታል። ይህ ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሊያበቃ ይገባል። የግዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር በየትም ቦታ ያለ ጦርነትም ሆነ ግጭት መጨረሻው ንግግር ወይም ድርድር ነው። የበለጠ ሰብአዊ ቀውስ፣ የበለጠ የንብረት ውድመት ከማስቀጠል ወደማይቀረው ሰላማዊ መፍትሔ የመሻት መድረክ መምጣት ግን እርሱ አሸናፊነት ነው ። እኔ በዚሁ ላብቃ ቸር ያሰማን፤ እያልኩ የምሰናበታችሁ ታምራት ዲንሳ ነኝ፤ ጤና ይስጥልኝ።  

Logo der Organisation Amnesty International
ምስል Britta Pedersen/dpa/picture alliance
Äthiopien l Amnesty International l  eritreische Soldaten sollen in Tigray hunderte Menschen getötet haben
በትግራይ በጦርነቱ የተገደለ ልጃቸውን ምስል የያዙ ወላጆችምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images
Eritrea Äthiopien Soldaten Flash-Galerie
የኤርትራ ወታደሮች (ስፍራው በትክክል ያልተገለጸ )ምስል AP
Äthiopien Tigray-Provinz Mekele
ከጦርነቱ በፊት የነበረው የመቀሌ ከተማ ገጽታምስል EDUARDO SOTERAS/AFP
Symbolbild Tigray Konflikt
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጉዳት የደረሰበት ታንክ ምስል Tiksa Negeri /REUTERS
Ätiopien  Tigray  Meeting Nairobi
ምስል African Union
Äthiopien Ministerpräsident Abiy Ahemed im Süden
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በአርባምንጭ ከተማ ለተሰበሰበው ህዝብ ንግግር ሲያደርጉምስል Southern Ethiopian regional office
Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
የሰላም ስምምነቱ በተፈጸመበት ወቅትምስል SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

ታምራት ዲንሳ

ማንተጋፍቶት ስለሺ