1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከባድ ዝናብ እና የዝናብ እጥረት ያስከተለዉ አደጋ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 12 2015

በኢትዮጵያ በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የተከሰተውን ከባድ ድርቅ ተከትሎ በተለያዩ ዞኖች በተስተዋለው የኮሌራ ወረርሽኝ እስካሁን 44 ሰዎች ሕይወት አልፏል። አዲስ አበባ ላይ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ደግሞ መኖሪያ ቤቶችን ሰብሮ አራት ሰዎችን ገድሏል፣ በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን ከባድ ዝናብ የጎርፍ የ13 ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል።

https://p.dw.com/p/4P0Qe
[No title]
ምስል Shewangizaw Wegayehu

በኢትዮጵያ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተከሰተውን ከባድ ድርቅ ተከትሎ በተለያዩ ዞኖች በተስተዋለው የኮሌራ ወረርሽኝ ምክንያት እስካሁን 44 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተነገረ። ባለፈው ቅዳሜ አዲስ አበባ ላይ የጣለው ከባድ ዝናብ  ያስከተለው ጎርፍ ደግሞ በወንዝ ዳርቻዎች የተሠሩ መኖሪያ ቤቶችን ሰብሮ በመግባት አራት ሰዎችን ሲገድል ፣ በተመሳሳይ ከሳምንት በፊት በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን የተስተዋለ ከባድ ዝናብ ያስከተለው የጎርፍ አደጋ የ13 ሰዎችን ሕይወት ማጥፋቱ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሜትሪዮሎጂ ኢንስቲቲዩት አሁን ላይ እየጣለ ያለው ዝናብ እነዚህን ችግሮች ቢያስከትልም በልግ ዋነኛ እና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ አካባቢዎች ላይ እየጣለ ያለው ዝናብ ወቅታዊ እና የሚጠበቅ ነው ፣ ቀጣይነት ያለውም ነው ብሏል።

ከየካቲት እስከ ግንቦት እንደሚጠበቅ የተነገረለት የበልግ ዝናቡ በተለይም የበልግ አዝርእትን ለማልማት እና ሌሎች የግብርና ሥራዎችን ለማከናወን አሥፈላጊ ከመሆኑም በላይ በድርቅ እየተጠቁ ለሚገኙት አካባቢዎች የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም የሜትሪዮሎጂ ኢንስቲቲዩት አስታውቋል።

የካቲት ፣ መጋቢት፣ ሚያዝያ እና ግንቦት ወራቶችን የሚሸፍነው የኢትዮጵያ የበልግ ወቅት በተለይ ለደቡብ አጋማሽ የኢትዮጵያ ክፍለ - አገር ዋነኛ የዝናብ ወቅት መሆኑን የሚገልፁት በኢትዮጵያ ሜትሪዮሎጂ ኢንስቲቲዩት የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ ሰሞነኛው ዝናብ የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን "ተጠናክሮ የሚቀጥል" ጭምር ነው።

"አሁን ላይ እየጣላ ያለው ዝናብ በተለይም በልግ ዋነኛ እና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑ የአገራችን አካባቢዎች ላይ ወቅቱን የጠበቀ ነው። ተጠናክሮ ይቀጥላል"። በኢትዮጵያ በ4 ክልሎች ድርቅ ተከስቶ በሰው እና በእንስሳት ላይ ከባድ ችግር ከማስከተሉ ባለፈ የምግብና ውኃ እጥረት ያስከተላቸው ተላላፊ በችታ እና ወረርሽኞችንም አምጥቷል። በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በኮሌራ 44 ሰዎች መሞታቸው ለዚህ ማሳያ ነው።

አቶ መስፍን ወሰን በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና አደጋ አስተባባሪ ናቸው ይህንን የገለፁልን። "አንደኛ በእነዚህ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የምግብ እጥረት መከሰተ፣ ሁለተኛ ወረርሽኞች ፣ በውኃ እጥረት ምክንያት ጋር ተያይዞ የኮሌራ ወርርሽኝ፣ የኩፍኝ ወረርሽኝ በሶማሌ ክልል ፣ በደቡብ ክልል መከሰቱን ያሳያ"።

ከሰሞኑ አዲስ አበባ ላይ ከባድ ዝናብ እየወረደ ነው። ባለፈው ቅዳሜ 4 ሰዎች በጎርፍ ተወስደው ሞተዋል። ትናንት ደግሞ በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ተከስቷል። አቶ ንጋቱ ማሞ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሟቾችን አስክሬን ማግኘታቸውን ገልፀው ጥንቃቄ እንዲደረግም አሳስበዋል።

"ቀለል ቀለል ያሉ ጉዳቴች ሲያደርስ ቆይቷል። ቅዳሜ እለት ግን ምሽት 12: 20 አካባቢ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የጣለውን ዝናብ ተከትሎ ጎርፍ በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ገብቶ የ 4 ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል"

ከየካቲት 17 ጀምሮ ለበልግ ዝናብ መፈጠር አመቺ የሆኑ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ከእለት ወደ እለት በመጠናከራቸው በብዙ ቦታዎች ላይ ከቀላል እስካ መካከልኛ መጠን ያለው ዝናብ አግኝተዋል ያሉት በኢትዮጵያ ሜትሪዮሎጂ ኢንስቲቲዩት የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ ዝናቡ ለግብርና ሥራም ሆነ ድርቅ ለመታቸው አካባቢዎች የሚፈለግ ነው ብለዋል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ