ከመፈንቅለ መንግሥት የተረፉት አሊ ቦንጎ ማን ናቸው?
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2011አሊያን በርማርድ ቦንጎ በጎርጎሮሳዊው 1959 ዓ.ም. በብራዛቪል ተወለዱ። እናታቸው ፔሸንስ ዳባኒ ስመ-ጥር የጋቦን ድምፃዊት ነበሩ። አባታቸው ኦማር ቦንጎ የአገሪቱ የረዥም ጊዜ መሪ ናቸው።
በጎርጎሮሳዊው 1973 ዓ.ም. የቦንጎ ቤተሰብ የእስልምና ዕምነትን ተቀበለ። የዛሬው ፕሬዝዳንት ስም ከአሊያን ወደ ወደ አሊ ተቀየረ። አሊ ቦንጎ በስመ-ጥሩው የፈረንሳይ ሶርቦርን ተቋም ሕግ ተምረዋል። የእናታቸውን ፈለግ ተከትለው የሙዚቃ ባለሙያ የሆኑት ቦንጎ አንድ የሙዚቃ አልበም ሰርተዋል።
ከሙዚቃ ወደ ፖለቲካ
በአባታቸው ግፊት አሊ ቦንጎ ሙዚቀኝነታቸውን እርግፍ አርገው በመተው የፖለቲካውን ዓለም ተቀላቀሉ። አባታቸው በጎርጎሮሳዊው 1989 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ምኒስትር አድርገው ሾሟቸው። ዘግየት ብለው የአገሪቱን መከላከያ ሚኒስቴር ኃላፊነት በመቀበል እስከ አባታቸው ዕለተ-ሞት መርተውታል።
አሊ ቦንጎ ከአባታቸው የቅርብ ሰዎች አጠገብ ባለመጥፋታቸው የፕሬዝደንትነቱን መንበር መረከባቸው እምብዛም አስገራሚ አልሆነም። አገሪቱ በጎርጎሮሳዊው 2009 ዓ.ም. ያካሔደችው ምርጫ የአሊ ቦንጎን ሥልጣን አረጋገጠ። አሸንፈዋል ከተባሉ በኋላ ግን መጠነ-ሰፊ ተቃውሞ እና ኹከት ተቀሰቀሰ። በርካቶችም ለሞት ተዳረጉ። ተቃዋሚዎች የምርጫውን ውጤት ለመገዳደር ያደረጉት ጥረት ሳይሰምር ቀርቶ ቦንጎ አገራቸውን የመምራት ዕድላቸው ተሳካ።
በጎርጎሮሳዊው 2006 ዓ.ም. የተካሔደውን ምርጫ ያሸነፉት አሊ ቦንጎ ዳግም በተቃዋሚዎች ፈተና ገጠማቸው። በመላ ሐገሪቱ ኹከት ተቀሰቀሰ። ተቀናቃኛቸው ዤን ፒንግ ራሳቸውን የምርጫው አሸናፊ አድርጎ እስከ ማሳወቅ ደርሰው ነበር። ይኸ የሆነው አሊ ቦንጎ ምርጫውን ማሸነፋቸው ከተረጋገጠ በኋላ ጭምር ነበር።
አቧራው ሲሰክን አሊ ቦንጎ ራሳቸውን የለውጥ ወኪል አድርገው አቀረቡ። ከአባቶቻቸው የተረከቧቸውን የመንግሥት ባለሥልጣናት በወጣቶች ተኩ። ለውጥ እና መሻሻል የሚያቀነቅኑ ድምጾች ከፍ ብለው ተሰሙ። ተቃዋሚዎች ግን ቅንጡ ኾነው ያደጉት አሊ ቦንጎ ከሕዝቡ በመራቃቸው ሊያምኗቸው አልቻሉም። በተለይ ከ60-70 በመቶ የሚደርስ ሕዝብ ከድሕነት ወለል በታች የሚኖርባትን ጋቦን የሚመሩት አሊ ቦንጎ የተጋነነ ወጪ ጥርስ አስነከሰባቸው። ስልጣን ላይ የቆዩባቸው አመታት ገንዘብ ያሸሻሉ በሚባሉት ቤተሰቦቻቸው ላይ በፈረንሳይ ይደረግ የነበረው ምርመራ ጥላ ያጠላባቸው ነበሩ።
ለአንዳንድ ታዛቢዎች ግን አሊ ቦንጎ ባደረጓቸው ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች ከበሬታ ይቸራቸዋል። ጋዜጠኛ ሴዲክ አባ ገዢውን የጋቦን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በማዘመናቸው እና በምድር ወገብ አካባቢ የሚገኝ የእንጨት ዝርያን ለንግድ እንዳይቀርብ የሚያግድ ሕግ እንዲጸድቅ ግፊት በማድረጋቸው ዋጋ ይገባቸዋል ብሎ ያምናል።
በጥቅምት 2018 ዓ.ም. የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ለመታከም አሊ ቦንጎ ወደ ሳዑዲ አረቢያ አቀኑ። አማካሪዎቻቸውም ሆኑ የቅርብ ሰዎቻቸው ስለ ጤናቸው ተጨማሪ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ረዘም ላለ ጊዜ ቦንጎ ጥፍት ማለታቸው እያሽቆለቆለ ስለሔደ ጤናቸው ሐሜት እንዲስፋፋ አድርጓል። መንግሥታቸው ግን ምክትል ፕሬዝደንት ክላቬር ማጋንግ ሙሳዩ በጊዜያዊነት ለመሾም ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶበታል። ቦንጎ ለአዲስ አመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በቴሌቭዥን በማስተላለፍ ጭምጭምታውን ለማጥፋት ሞክረዋል። ፕሬዝደንቱ ተሽሏቸው በሞሮኮ በማገገም ላይ መሆናቸውን ተናግረው ነበር። የፕሬዝደንቱን ንግግር "አሳዛኝ" ሲሉ ያጣጣሉት የጋቦን ወታደሮች ግን ነገሩን ሁሉ በሥልጣን ለመቆየት የሚደረግ መፍጨርጨር ሲሉ ይገልጹታል።