ከመቀሌ እና ራያ የተመለሱ የዮንቨርስቲ ተማሪዎች
ዓርብ፣ ሐምሌ 9 2013በትግራይ ክልል የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ በርካታ ወላጆች የቴሌኮሚኒኬሽን ግንኙነት ከተቋረጠ ጊዜ አንስቶ ከልጆቻቸው ጋር እስካሁን መገናኘት አልቻሉም። የተወሰኑ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸው ተመልሰውላቸው እፎይ ብለዋል። የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ ም ከመቀሌ ከተማ ለቆ ሲወጣ ናሆም በሚማርበት የመቀሌ ዮንቨርስቲ ካምፓስ ውስጥ ነበር። « በተማሪዎች ዘንድ ትንሽ ግራ የመጋባት ስሜት ነበር። ከዛ ውጪ ግን ብዙ የተለየ ነገር አልተፈጠረም። የደስታ ርችት እና ተኩስ እንሰማ ነበር። እኛ እንኳን መከላከያ የገባ ጊዜም ስለነበርን ሁኔታው ብዙም አላስደነቀጠንም። አዲስ ተማሪዎች ግን ትንሽ የመደናገጥ ስሜት ነበራቸው።» ይላል።
ተማሪዎቹ ከነበረው ሁኔታ ጋር ቀስ በቀስ ቢላመዱም በተለይ የቴሌኮሚኒኬሽን ግንኙነት መቋረጡ እና አንዳንድ የሚሰሙት እና የሚያዩት ነገር ከግቢ ለቀው እንዲወጡ እንደገፋፋቸው ናሆም ይናገራል። « ከኛ በፊት የሄዱ ሰዎች ነበሩ።የእነሱ መሄድ የሚገፋፋ ስሜት ነበረው። ከዛ በተጨማሪ የምግብ ሁኔታ ያጠራጥር ነበር። » ድባቡም በፊት ከነበረው ሁኔታ መቀየሩን ናሆም ይናገራል። ከዛም በተጨማሪ መሠረታዊ የሆኑ እንደ መብራት እና የባንክ አገልግቶሎች አለመኖራቸው ለተማሪዎቹ ምክንያት ነበሩ። ናሆም እና ጓደኞቹ ዮንቨርስቲውን ለቀው የወጡት መከላከያ ከመቀሌ ከወጣ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሲሆን ከግቢ የወጡትም ሚኒ ባስ ተከራይተው ነው። « መንገድ ላይ ሁለት ኬላ ላይ ፍተሻ ነበር። ተማሪ መሆናችንን መታወቂያ አሳይተን ነው ያለፍነው። የተወሰኑ ተማሪዎች ግን ኮምፒተራቸው እንደተወሰደባቸው ሰምቻለው። » ይላል ናሆም። ተማሪዎቹም የተወሰነ መንገድ በመኪና ከተጓዙ በኋላ በባጃጅ እና በእግር አቆራርጠው አላማጣ ገብተዋል።
ተማሪ ስንዱ የመከላከያ ሠራዊት ከራያ ዮንቨርስቲ የለቀቀ ምሽት ነው ከጓደኟቾ ጋር ወዲያውኑ ለመመለስ የወሰነችው። « ግቢ ውስጥ ያሉ መከላከያዎች ሲወጡ እኛም በድንገት ሌሊት ተከትለን ወጣን።» የዛን ምሽት ብቻ ዮንቨርስቲውን ለቀን የወጣነው ተማሪዎች 220 ገደማ እንሆናለን የምትለው ስንዱ በሌሊት እና በድንገት ስለነበር አብዛኞቹ ተማሪዎች እዛው መቅረታቸውን ትናገራለች። ጉዞዋቸውም አስጊ እና በእግር ነበር። « መኪናም አልነበረም፣ሌሊት ነው። መከላከያዎች ራሱ በእግር ነበር የሚጓዙት። እና ደርሰንባቸዋል። ለረዥም ሰዓት በእግራችን ነው የተጓዝነው። ትንሽ አስከፊ ነገር ነበረው።»ጥቂት ውኃ እንጠጣ ብለው ወደኋላ የቀሩ ተማሪዎች መያዛቸውን መስማቷን ስንዱ ገልፃልናለች። ስንዱ በሰዓቱ የኔትወርክ ግንኙነት ስላልነበር ቤተሰቧ እሷም በጉዞ ላይ ስለመሆኗ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። « አላማጣ ከተማ እስክንገባ ድረስ ኔትዎርክ ስላልነበር። ማንም ወላጅ አያውቅም ነበር። ድንገተኛም ስለነበር ለሁሉም ሰው አስደንጋጭ ነበር።»
የራያ ዮንቨርስቲ ተማሪዋ ስንዱም ትሁን የመቀሌ ዮንቨርስቲ ተማሪው ናሆም ምሩቅ ተማሪዎች ናቸው። ይህ ዓመት እንደሌሎቹ ዓመታት ነፃነት የተሞላበት ባይሆንም በጥር ወር ትምህርታቸውን መከታተል ከጀመሩ አንስቶ ሰላማዊ በሚባል ሁኔታ እየተማሩ እንደነበር ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። ከአሁን በኋላ እንዴት እንደሚቀጥል ግን ማናቸውም አያውቁም። « ፈተና ላይ ነበርን። ሶስት ሳምንት ያህል ነበር የቀረን። ግን ሁኔታው አዳጋች ሆኖ ስለታየን ነው ትተን የመጣነው። እዚህ መጥተን ደግሞ የሚመለከታቸውን አካላት እያናገርን ነው።» ይላል ናሆም። ስንዱም ብትሆን ክልል ላይ አመልክተን ነበር ትላለች። « ተመልሳችሁ አትገቡም የሚል ውሳኔ ተወስኗል ብለው ነግረውናል። ነገር ግን የትኛው ዮንቨርስቲ ነው ገብተን መመረቅ ያለብን ፣ ቦታ ይሰጠን ብለን ስንጠይቃቸው መወሰን አልቻሉም»
ከዚህ ባሻገር ደግሞ በአሁኑ ሰዓት እዛው ዮንቨርስቲ ውስጥ ያሉት ተማሪዎች ጉዳይ ያሳስባቸዋል።ናሆም መቀሌ በነበረበት ጊዜ አንዳንድ የአካባቢው ተወላጅ ተማሪዎች ይዝቱ እና ሌሎችን ያስፈራሩ እንደነበር ገልፆልናል። « የሚሳደቡ ውስን የሆኑ ተማሪዎች ነበሩ። ግን ሁሉንም የሚወክሉ አልነበረም። በተለያየ ምክንያት ተገቢ ያልሆነ ባህሪዎች የሚያሳዩ ልጆች ነበሩ። » ሲል ራሱ መመልከቱን ይናገራል።
ስንዱ ደግሞ ራያ ዮንቨርስቲ ያሉ ጓደኞቿ በቅራቡ ኔትዎርክ ወዳለበት ቦታ ሄደው ደውለውላት እንደነበር ትናገራለች። ደህና ስለመሆናቸው ግን ጥርጣሬ አላት። « የ20 ብር ባጃጅ ትራንስፖርት በባጃጅ ተጉዘው እንደደወሉልኝ ነው የነገሩኝ። ሰላም እንደሆኑ ነግረውኛል። ግን ኔትወርክ ካለቦት ቦታ ከትግራይ ልዩ ኃይል ጋር ተከትለው መጥተው ሰላም እንደሆኑ ለቤተሰብ መልዕክት እንዲያስተላልፉ እንደሚገደዱ ነው የገባኝ።»ትላለች ።
በስጋት ትምህርታቸውን አቋርጠው የተመለሱት ተማሪዎችንም ጉዳይ ይሁን የክረምት የዲግሪ ተማሪዎች ትምህርት ስለመጀመራቸው ለመጠየቅ ዶይቸ ቬለ በተደጋጋሚ ጉዳዩ የሚመለከተው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ደውሎ ነበር። ምላሽ ግን አላገኘም።
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ