1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
የምግብ ዋስትናአፍሪቃ

ከ12 ዓመት በላይ ያልተጠናቀቀው መስኖ በሶማሌ ክልል

ዓርብ፣ ግንቦት 19 2014

በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ከ12 ዓመታት በላይ ያለ አገልግሎት ሲፈሱ የነበሩ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ከዚህ ዓመት ጀምሮ ጥቅም ላይ ለማዋል ሥራ መጀመሩ ተገለጠ። የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚንስቴር በሜቴክ ድርጅት ተጀምረው ሳይጠናቀቁ ብክነት ውስጥ የቆዩትን ሃያ ስምንት ጉድጓዶች አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4Bxkj
Irrigation Project at City Zone, Somali Region
ምስል Mesay Teklu/DW

28 የውኃ ጉድጓዶች ያለአገልግሎት ለዓመታት ባክነዋል

በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ከዐሥራ ሁለት ዓመታት በላይ ያለ አገልግሎት ሲፈሱ የነበሩ የመስኖ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ሥራ መጀመሩ ተገለጠ። የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚንስቴር በሜቴክ ድርጅት ተጀምረው ሳይጠናቀቁ ብክነት ውስጥ የቆዩትን ሃያ ስምንት ጉድጓዶች አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጿል። የክልሉ መንግስት በክልሉ ባሉ የተለያዩ ዞኖች የሚኖረውን አርብቶ አደር ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለሚያደርጉ የተለያዩ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ትኩረት መስጠቱን በመጠቆም ባለሐብቶችም እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል። ረቡዕ ዕለት በተካኼደው የመስክ ጉብኝት የድሬዳዋው ወኪላችን መሳይ ተክሉ ተገኝቶ ነበር።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን በክልሉ ሲቲ ዞን ዱሬ በተባለ አካባቢ ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት ተጀምረው ባለመጠናቀቅ ብክነት ውስጥ የቆዩ የመስኖ ፕሮጀክት ስራዊችን አጠናቆ አርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ  ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

Irrigation Project at City Zone, Somali Region
ምስል Mesay Teklu/DW

ምርትና ምርታናነትን ማሳደግ ካልተቻለ አሁን በገጠርም በከተማም ያሉ ችግሮች የበለጠ አደጋ ውስጥ ይከታሉ ያሉት አቶ ኢብራሂም በክልሉ ባሉ ዞኖች ለመስኖ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው በበቂ ደረጃ ላይ አይደለም ያሉት የባለሀብቶች ተሳትፎ እንዲያድግ ጥሪ አቅርበዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚንስቴር ሚንስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ በሲቲ ዞን ለመስኖ አገልግሎት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል። የፕሮጀክቱ ስራ በእቅድ መካተቱን የጠቀሱት ሚንስትሯ ለጊዜው አራት ሺህ ሄክታር መሬት ወደ ስራ እንደሚገባ አስረድተዋል። አካባቢው በተለያዩ ጊዜያት በድርቅ የሚጠቃ ፤ ነገር ግን ትልቅ ተፈጥሯዊ ሀብት ያለበት እና ከጅቡቲ ባለው ቅርበት ለኢንቨስትመንት ምቹ አካባቢ ነው ያሉት ኢንጅነር አይሻ ማንኛውም ኢንቨስተር ወደ አካባቢው ቢመጣ ህብረተሰቡን ጠቅሞ ራሱን መጥቀም የሚችልበት ነው ብለዋል። የዶይቸ ቬለ የድሬዳዋ ወኪል ረቡዕ፤ ግንቦት 17 ቀን፣ 2014 ዓ.ም በመስክ ጉብኝቱ በአካባቢው ማኅበረሰብ እና በጥቂት ባለሐብቶች የተጀመሩ የመስኖ ዝግጅት ሥራዎችን ተመልክቷል።

መሳይ ተክሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ