እስር፤ ግድያና እገታ በጉራጌ ዞን
ረቡዕ፣ ጥቅምት 20 2017በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ከፋኖ እና ሸኔ ጋር ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ነዋሪዎች እየታሰሩ መሆናቸውን ተናገሩ ። በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እገታ እና ግድያ ይፈጽማሉ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ መንግሥት ግንኙነት የሌላቸውን እያሰረ ይገኛል ሲሉም ይከሳሉ ። የሐዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛው ወጋየሁ ዝርዝር አለው ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ የዳርጌ አካባቢ ነዋሪዎች በሥጋት ውስጥ መውደቃቸውን እየገለጹ ይገኛሉ ፡፡ ነዋሪዎቹ እንዳሉት በአንድ በኩል ታጣቂዎች ግድያና እገታ ይፈጽሙባቸዋል ፤ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ከታጣቂዎቹ ጋር ግንኙነት አላችሁ ብሎ ያስራቸዋል ፡፡ የክልሉ መንግሥት በበኩሉ " ሽብርተኛ " በሚል የተፈረጁት የፋኖ እና የሸኔ ቡድኖች በክልሉ አዋሳኝ ሥፍራዎች ላይ ክልልን ለማወክ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ብሏል ፡፡
ታጣቂዎች የደቀኑት ሥጋት
ለደህንነቴ ሲባል ሥሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ በአበሽጌ ወረዳ የዳርጌ አካባቢ ነዋሪ በቀበሌው ለተፈጠረው የሰላም እጦት ታጣቂ ቡድኖችን ተጠያቂ ያደርጋሉ ፡፡ ከቅርብ ወራቶች ወዲህ በአካባቢው በታጣቂዎች እንቅስቃሴ የተነሳ ሥጋት መኖሩን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪው " ታጣቂዎች በነዋሪው ላይ በሚፈጽሙት ዘረፋ የተነሳ በሥጋት ውስጥ እንገኛለን ፡፡ ምርታችንን እንኳን ወደ ገበያ ወስድን ለመሸጥ አልቻልንም ፡፡ በዛ ላይ ሰዎችን በማገት ብር እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ ፡፡ በቅርቡ አንድ ወጣትና አንድ ሌላ የአካባቢው ባለሀብት ታግተው አራት መቶ ሺህ ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀዋል " ብለዋል ፡፡
የመንግሥት ጥርጣሬ
የቀደሙት አስተያየት ሰጪ ለሰላም እጦቱ መንስኤው በቀበሌው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ናቸው ቢሉም የዚሁ መንደር ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ የመንግሥት የፀጥታ አባላት የሚፈጽሙት የጅምላ እሥር ሥጋት ላይ እንደጣላቸው ይናገራሉ ፡፡ በአካባቢው የታጠቁ ቡድኖች መኖራቸው እርግጥ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪው " ነግር ግን ከቡድኖቹ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ሠርተው የሚኖሩ ንጽሃን ጭምር ባልዋሉበት እየታሠሩ ይገኛሉ ፡፡ ለምሳሌ የዘጠኝ ልጆች አባት የሆነ አማቼ የአማራ ተወላጅ ብቻ በመሆኑ ፋኖ ነህ ተብሎ ታስሮ ወልቂጤ ተወስዷል ፡፡ አብዛኛው የብሄሩ ተወላጅ አማራ ሥለሆነ ብቻ ፋኖ ነህ ተብዬ ልታሠር እችላለሁ በሚል ሥጋት ውስጥ እየኖረ ይገኛል " ብለዋል ፡፡
የመንግሥት ርምጃ
በአሁኑ ወቅት በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዋልጋና እና በወልቂጤ ከተሞች ታሥረው እንደሚገኙ የታሳሪ ቤተሰቦች ተናግረዋል ፡፡ በወረዳው ታጣቂዎች ፈጥረዋል በተባለው ሥጋትና ታሥረዋል በተባሉ ሰዎች ዙሪያ ዶቼ ቬለ የወረዳ፣ የዞን እና የክልል ፀጥታ ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጠው አካል ባለማግኘቱ ሊሳካ አልቻለም ፡፡ ያም ሆኖ በቅርቡ ከክልል ምክር ቤት አባላት ጋር የውይይት መድረክ ያካሄዱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው መንግሥት ሽብርተኛ ሲል በፈረጃቸውና በክልሉ አዋሳኝ ሥፍራዎች ላይ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ባሏቸው የፋኖ እና የሸኔ ቡድኖች ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ገልጸው ነበር ፡፡
ፎቶ ፡ ከክልሉ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር