1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተጠናከረ ነው »

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 17 2015

የኢትዮጵያ እና የጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታሪክ ወደ ጎርጎርሳውያኑ 1905 እና 1907 ይመልሰናል ። ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ በተሻገረው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ኢትዮጵያ ወደ ጀርመን ገበያ ዋነኛዋ ቡና ላኪ በመሆን እንዲሁም ጀርመን በበኩሏ ከምታደርገው ኤኮኖሚያዊ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች ።

https://p.dw.com/p/4QVLT
Botschafter in Deutschland Fekadu Beyene aus Äthiopien
ምስል privat

ከአምባሳደር ፍቃዱ በየነ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

የኢትዮጵያ እና የጀርመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታሪክ ወደ ጎርጎርሳውያኑ 1905 እና 1907 ይመልሰናል-ወደ ዳግማዊ አጼ ሚንሊክ ንጉሰ ነገስት ዘመነ መንግስት ። ከአንድ ክፍለ  ዘመን በላይ በተሻገረው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ኢትዮጵያ ወደ ጀርመን ገበያ ዋነኛዋ ቡና ላኪ በመሆን እንዲሁም ጀርመን በቀጥታ ለኢትዮጵያ ከምታደርገው ኤኮኖሚያዊ ድጋፍ ባሻገር በተለያዩ የግብረ ሰናይ ድርጅቶቿ አማካኝነት የተለያዩ ድጋፎችን ስታደርግ ቆይታለች ። በሰሜን ኢትዮጵያ ተቀስቅሶ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው እና ምናልባትም በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ህልፈት ምክንያት በነበረው ጦርነት የተነሳ ጀርመንን ጨምሮ የአውሮጳ ህብረት እና ሌሎቹም ከኢትዮጵያ ላይ ፊታቸውን ያዞሩበት እና የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲሻክር ምክንያት ሆኖ ነበር። አምባሳደር ፍቃዱ በየነ በቅርቡ በጀርመን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው በመሾም ስራ ጀምረዋል። በድህረ ሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተለይ ጀርመን በጦርነቱ ወቅት እና በኋላ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የነበራትን ዲፕሎማሲያዊ ግኙነትን በተመለከተ ሲናገሩ ።
በጀርመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጀርመን በተጨማሪ በሌሎች 8 የጎረቤት ሀገራት የዲፕሎማሲ እና የቆንስላ አገልግሎት እንደሚሰጥ የተናገሩት አምባሳደር ፍቃዱ በፖለቲካዊ ኤኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን አጠናክረው ለመቀጠል መዘጋጀታቸውን ይገልጻሉ። መሰረቱ ደግሞ ለእርሳቸው «የገጽታ ግንባታ» ነው። 
ኢትዮጵያ ከጦርነቱ በኋላ ጀርመን እና ከአውሮጳ ህብረትም ሆነ ከተቀረው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። በዚሁ ምዕራፍ ደግሞ  በጦርነቱ ምክንያት የተዳከመውን ኤኮኖሚዋን ለመጠገን ከመንግስታት  እና የገንዘብ ተቋማት ጋር ብድር እና እርዳታ ለማግኘት ብርቱ ጥረት ስታደርግ መቆየቷም እንዲሁ የመገናኛ ብዙኃንን ሽፋን አግኝቷል። አምባሳደር ፍቃዱ እንደሚሉት በፕሪቶሪያ ከተደረሰው የሰላም ስምምነት በኋላ ሀገራት እና ዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከኢትዮጵያ አንጻር ይዘውት የነበረውን አቋም በመቀየር የትብብር ግኙነት ጀምረዋል። የተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ እየተጓዙ መሆናቸውን በመጥቀስ በመሃል ሻክሮ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ስፍራው እንደሚመለስ ተስፋቸውን ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ መንግስት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የደረሰውን የሰላም ስምምነት ገቢራዊ እያደረገ ይገኛል። አሁን ደግሞ መንግስት ሸኔ ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጋር ታንዛኒያ ውስጥ የሰላም ንግግር እንደሚጀመር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን ይፋ አድርገዋል። የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲሰምር የአውሮጳ ህብረትም ሆነ ጀርመን ሲደግፉት ነበር ፤ በታንዛንያ የሰላም ንግግር ሊጀመር መሆኑ ከተሰማ በኋላ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የድጋፍ ድምጾች ቢሰሙም ፤ጸንቶ ከውጤት መድረሱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱም እንዲሁ አልጠፉም፤ እንደቀደመው ሁሉ በተለይ የአውሮጳ ህብረት ሚና ጉዳይም አብሮ ይነዳል። አምባሳደር ፍቃዱ ለታንዛኒያው የሰላም ንግግር የህብረቱም ሆነ የጀርመን ድጋፍ አብሮ እንዳለ ነው ያመለከቱት ።
የኢትዮጵያ መንግስት እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን የሚያደርጉት የሰላም ንግግር ምን ያህል ተስፋ ያጭራል ብለው የሚጠይቁ እንዳሉ ሁሉ ሁለቱም ወገኖች ለመነጋገር መፍቀዳቸው በራሱ አንድ እርምጃ እንደ,ሆነም የሚገልጹ አልጠፉም ። አምባሳደር ፍቃዱም የዚሁ ሃሳብ ተካፋይ ናቸው ።
ጎረቤት ሀገር ሱዳን በአስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፤ ጦርነቱ በአጎራባች ብሎም በቀጣናው ሀገራት ላይ ብርቱ ጥላ ሊያጠላ እንደሚችል ከወዲሁ እየተነገረ ነው፤ኢትዮጵያ  ከሁለቱ የሱዳን ተፋላሚዎች አንጻር የምትከተለው ሚና በእርግጥ በውል አልለየም። ይህንኑ በተመለከተ የተጠየቁት አምባሳደሩ ሲናገሩ የኢትዮጵያ ሚና በጦርነቱ በቀጥታ ተጎጂ ስለምትሆን ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን ማቆም በሚችሉበት አግባብ ላይ መስራት መሆኑንን አመልክተዋል።
እንግዲህ አድማጮች በወቅቱ ከጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍቃዱ በየነ ጋር የነበረንን ቆይታ ያስተናገድንበት ዝግጅት ይህን ይመስላል።

Sudan Angriffe Bombardierung
ምስል ASSOCIATED PRESS/picture alliance
Themenbild Kaffee, Kaffeebohnen
ምስል Andres Victorero/Zoonar/picture alliance
Botschafter in Deutschland Fekadu Beyene aus Äthiopien
ምስል privat
Deutschland Besuch Haile Selassie Kaiser von Äthiopien
ምስል privat

ከአምባሳደር ፍቃዱ ጋር ያደረግነውን ሙሉውን ቃለ-ምልልስ የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።   

ታምራት ዲንሳ

ነጋሽ መሐመድ