ኢትዮጵያ፤ የትምህርት ሥርዓቱን ችግሮች በጋራ መፍታት ይገባል
በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን በግልፅ ተነጋግሮ በጋራ መፍታት ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። ፕሮፌሰሩ ይህን የተናገሩት ለመምህራን ማህበር አባላት በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ነዉ። ችግሩ መቅረፍ ግዴታ ነዉ ያሉት ብርሃኑ ነጋ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በ12ኛ ክፍል ፈተና ያገኘነው ውጤት ምን ያህል የትምህርት ሥርዓቱ ችግር ያለበት መሆኑን ያሳየ ነው፤ ለዚህም ችግሩን ሊፈታ የሚችል መፍትሄ ማስቀመጥና መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል። የአገር ዉስጥ መገናኛ ዘዴዎች የትምህርት ሚኒስትሩን ጠቅሰዉ እንደዘገቡት፤ በኢትዮጵያ በተለይም ጥራት ያለው ትምህርት አለማቅረብ፣ የፖለቲካና ትምህርት መጋባት፤ የትምህርት አመራሩ የሚመደበው በብቃቱ ሳይሆን ለፖለቲካው ባለው ወገንተኝነት መሆኑ፣ ትምህርቱ በክልላዊነት መታጠሩ እና አጠቃላይ በሀገር ውስጥ የተፈጠረው የሞራል ውድቀት የትምህርት ስርዓቱ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸውን አንስተዋል። ብርሃኑ የትምህርት ሥርዓቱን በትክክል ለመቀየር እነዚህን ስብራቶች ከመሠረቱ ማስተካከል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የ12ኛ ክፍል መልቀቅያ ከተፈተኑት መካከል 3.2 በመቶዉ ብቻ አለፈ አልያም ከ 800 ሺህ በላይ ተማሪ ወደቀ መባሉ፤ ብዙዎችን አስደንግጧል። አንዳንድ አስተያየት ሰጭ ኢትዮጵያዉያን መንግሥት ተማሪዎችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላለመቀበል ያደረገዉ እርምጃ ነዉ ሲሉ አስተያየታቸዉን ይሰጣሉ። አንዳንዶች በበኩላቸዉ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጠዉ በጀት ለማቋረጥ የተደረገ ርምጃ ነዉ ሲሉ መንግሥትን ይኮንናሉ።
ኬንያ፤ የብሪታንያዉ ንጉስ የኬንያ ጉብኝት
የብሪታንያዉ ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ የንግሥናዉን መንበር ከያዙ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የኮመንዌልዝ አባል ሃገር የሆነችዉን ኬንያን ለመጎብኘት ዛሬ ከባለቤታቸዉ ከንግሥት ካሚላ ጋር ናይሮቢ ገቡ። ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ ዛሬ ለአራት ቀናት ኬንያን ለመጎብኘት ናይሮቢ ሲገቡ በፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የብሪታንያዉ ባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ይፋ ባደረገዉ ጋዜጣዊ መግለጫ መሰረት፤ ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ የኬንያ ጉብኝት በብሪታንያ እና ኬንያ መካከል በምጣኔ ሀብት ልማት፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና ደህንነትን በተመለከተ የሚያደርጉትን የጋራ የትብብር፤ ማሳያ መሆኑን ገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ ንጉስ ቻርልስ ሣልሳዊ በዚህ የኬንያ ጉብኝታቸዉ ወደ ሰባት አስርት ዓመታት ገደማ በዘለቀው የብሪታኒያ ቅኝ ግዛት ዘመን የተፈጸመዉን "አሳዛኝ ገጽታ" አምነው ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኬንያ በዚህ ዓመት ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት የተላቀቀችበትን 60ኛ ዓመት የነጻነት ቀንዋን ታከብራለች። ንጉሱ እና ባለቤታቸዉ ንግሥት ካሚላ በኬንያ አዲስ የተገነባ ብሔራዊ የታሪክ ሙዚየምን ብሎም ኬንያ በጎርጎረሳዉያኑ 1963 ዓም ከብሪታንያ ነፃ መዉጣትዋን ያወጀችበትን ቦታ ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ንጉሱ ታዋቂዋን ኬንያዊት የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ዋንጂራ ማታይን ለማግኘት ዕቅድ መያዛቸዉም ተገልጿል።
የብሪታንያ መንግሥት ኬንያን በቅኝ ግዛት በያዘበት ዘመን በተለይም ከጎርጎረሳዉያኑ 1952-1960 ዓም ባለዉ ጊዜ፤ በማዕከላዊ ኬንያ በማው ማው ዓመፅ ወቅት ስለተፈፀመዉ ግፍ እንደተጸጸተ መግለፁ ተሰምቷል። የኬንያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ይፋ እንዳደረገዉ በዚህ አመጽ ወቅት 90,000 ሰዎች እንደተገደሉ እና የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እንዲሁም ወደ 160,000 ሰዎች በቅኝ ግዛት ባለ ሥልጣናት ታስረዉ፤ ነበር ሲል ግምቱን አስቀምጧል።
ታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ሽታይን ማየር ታንዛንያን እየጎበኙ ነዉ
ጀርመን እና ታንዛኒያ ግንኙነታቸውን የበለጠ በማስፋት እና በማጠናከር የቅኝ ግዛት ዘመን ታሪካቸዉን በጋራ ለማጤን እንደሚሰሩ ተነገረ። ይህ የተነገረዉ የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር ታንዛንያን ለመጎብኘት ዳሬሰላም ከገቡ በኋላ ነዉ። የታንዛኒያዋ ፕሬዝዳንት ሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን በዳሬሰላም ከጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ዋልተር ሽታይንማየር ጋር ከተገናኙ በኋላ "በአገራችን የነበረዉን የቅኝ ግዛት ዘመን እንዴት መፈተሽ ማየት እንዳለብን ይፋዊ ድርድር ለመጀመር ዝግጁ ነን" ብለዋል። ፕሬዚዳንቷ “ይህን የጨለማ ምዕራፍ ለመረዳት አብረን መስራታችን ለእኔ አስፈላጊ ነው” ሲሉ አጽንዖት ሰጥቷል። ጀርመንም የባህል ንብረቶችን እና የሰውን አስከሬን ለመመለስ ተዘጋጅታለች።
የምስራቅ አፍሪካ ታንዛኒያ እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ የጀርመን ቅኝ ግዛት አካል ነበረች። የቅኝ ግዛት ዘመኑ በጭቆና፣ በብዝበዛ እና በጭካኔ የተሞላ እንደነበርም ተመልክቷል። እንደ ታንዛኒያ ግምት ከጎርጎረሳዉያኑ 1905 እስከ 1907 ባለው ጊዜ ውስጥ የማጂ-ማጂ እየተባለ በሚጠራው ጦርነት እስከ 300,000 ሰዎች ተገድለዋል።
ጀርመን ንስለር ሾልዝ ምዕራብ አፍሪቃን ለሦስት ቀናት
ምዕራብ አፍሪቃን ለሦስት ቀናት ለመጎብኘት ባለፈዉ እሁድ ወደ ናይጀርያ ያቀኑት የጀርመኑ መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ዛሬ ጋና መዲና አክራ ጉብኝት አድርገዋል። ቻንስለር ሾልዝ በአክራ መዲና ከፕሬዝዳንት ናና አኩፎ አዶ ጋር ተገናኝተዉ ተወያይተዋል፤ ብሎም በመዲናዋ የሚገኝ የወታደሮች ማሰልጠኛ ማዕከልን ጎብኝተዋል። በዚህ ጉብኝት ሾልዝ ከጀርመን እና ከጋና የንግድ ተወካዮች ጋር በጋራ ተወያይተዋል። ከ34 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ብዛት ያላት ጋና በአፍሪቃችን ከሚገኙ ሃገራት መካከል እጅግ የተረጋጋ ዴሞክራሲ ስርዓትን የምትከትል ቀዳሚዋ ሃገር ናት። ቀደም ሲል ናይጀርያን የጎበኙት የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ መዲና ሌጎስ ላይ ከፕሬዝዳንት ቦላ ቲኑቡ ጋር ተገናኝተዉ በተለይ ስደተኞችን ከጀርመን በመመለስ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል። ሾልዝ በሃገራቱ መካከል ፍልሰትን በማስተዳደር ረገድ የጠበቀ ትብብር እንዲኖር ሐሳብ አቅርበዋል። ትናንት ሰኞ ሾልዝ 20 ሚሊዮን ነዋሪ በሚገኝባት መዲና ሌጎስ የሚገኝ አንድ የፍልሰተኞች ማዕከልን ጎብኝተዋል። የጀርመኑ ቻንስለር እና የናይጀርያዉ ፕሬዚዳንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የናይጀርያዉ ፕሬዚዳንት ዜጎች ሁሉ ሃገራቸዉ መመለሳቸዉን ተቀብለዋል።
ይሁን እንጂ ችግሩ በጀርመን የሚገኙት አብዛኞቹ ማንነትን የሚያረጋግጥ መታወቅያ የላቸዉም። በጀርመን ከሚገኙት ወደ 14,000 ከሚጠጉት ናይጀርያዉያን ተገን ጠያቂዎች መካከል ወደ 12,500 ገደማ የሚሆኑት የመለያ መታወቂያ ወረቀት የሌላቸዉ ናቸዉ። የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ዛሬ ምሽት የምዕራብ አፍሪቃ ጉብኝታቸዉን ጋና ላይ አጠናቀዉ ወደ ሃገራቸዉ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።
እስራኤል፤ የተኩስ አቁም ጥያቄን ዳግም ውድቅ አደረገች
እስራኤል በጋዛ ክልል በታጣቂዉ እና በአሸባሪነት በተፈረጀዉ ሃማስ ቡድን ላይ እያካሄደች ባለዉ ጥቃት ስኬቶችን ማግኘትዋን ገለፀች። በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ለሰብዓዊ እርዳታ ኮሪዶር የጠየቀውን የተኩስ አቁም እስራኤል ዳግም ውድቅ አድርጋለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ጦር "ደረጃ በደረጃ " እየገሰገሰ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ይሁንና ሚኒስትሩ እስራኤልን የተኩስ አቁም እንድታደርግ እና እንድትስማማ መጠየቅ ሃማስን ብሎም ሽብር እንዲቆጣጠራት ከመጠየቅ ተለይቶ አይታይም ሲሉ አጽኖት ሰጥተዋል። እንደ እስራኤል ሁሉ ዩናይትድ ስቴትስም የሰብዓዊ እርዳታን ለማቅረብ የተጠየቀዉን የተኩስ አቁም ጥሪ ተቃወማለቃለች። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ "ይህ በአሁኑ ወቅት ትክክለኛው መልስ ነው ብለን አናምንም" ማለታቸዉ ተሰምቷል።
ፍልስጤም፤ ርዳታዉ ለጋዛ ህዝብ በቂ አይደለም
የተመድ የፍልስጤም ርዳታና ሥራዎች ድርጅት ኃላፊ ፊሊፕ ላዛሪኒ ለጋዛ ተጨማሪ የሰብአዊ ርዳታ እንዲደረግ አሳሰቡ። እስካሁን በጋዛ ገባ የተባለዉ በጣት የሚቆጠር እርዳታ የጫነ ተሽከርካሪ ችግር ላይ ለወደቀዉ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ለሆነዉ የጋዛ ህዝብ በቂ አይደለም ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ላዛሪኒ ተናግረዋል። አሁን ባለው ሁኔታ የጋዛ ህዝብ ለሌሎች ሰላማዊ ሰዎች እንደሚደረገዉ እርዳታ እየተደረገት እንዳልሆነ ነዉ የሚረዳዉ ሲሉ የተናገሩት የተመድ የፍልስጤም ርዳታና ሥራዎች ድርጅት ኃላፊ፤ በፍልስጤም ግዛት የሚኖረዉን ህዝብ ሁሉ ከሃማስ ጋር ማዛመድ አደገኛ ነዉ ሲሉም አስጠንቅቀዋል። ላዛሪኒ ካልሆነ ግን መላው ሕዝብ ላይ ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት ይከናወናል ሲሉ የተመድ የፍልስጤም ርዳታና ሥራዎች ድርጅት ኃላፊ አሳስበዋል።
ኢንዶኔዥያ በሽብር የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች መያዛቸዉ ተገለፀ
ለምርጫ ዝግጅት ላይ ባለችዉ በኢንዶኔዥያ በሽብር የተጠረጠሩ በርካታ ሰዎች መያዛቸዉ ተገለፀ። የሀገሪቱ የሽብር መከላከያ ፖሊስ እንዳስታወቀዉ የጦር መሳሪያ፣ የፕሮፓጋንዳ ቁሳቁስ፣ የፈንጂ መስርያ ኬሚካል፤ የተገኘባቸዉ ወደ 59 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዉለዋል። የሃገሪቱ ፖሊስ ይፋ እንዳደረገዉ በቁጥጥር ከዋሉት 59 ተጠርጣሪዎች መካከል 40 የሚሆኑት በመጭዉ የካቲት ወር በሃገሪቱ ሊካሄድ በታቀደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ ጥቃት ለማድረስ ያሴሩ እና አይ ሲስ ተብሎ ከሚጠራዉ የሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸዉ ናቸዉ። በዓለማችን በርካታ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሚገኙባት ሀገረ ኢንዶኔዥያ በዩናይትድ ስቴትስ በጎርጎረሳዉያኑ 1999 መስከረም 11 የሽብር ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ፤ በነበሩት ዓመታት ተከታታይ የሽብር ጥቃቶች የደረሱባት ሃገር መሆንዋ ይታወቃል።
ደቡብ አሜሪካ፤ በርካታ ስደተኞች የእግር ጉዞ ወደ አሜሪካ ጀምረዋል
በደቡባዊ ሜክሲኮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ከ3,000 ኪሎ ሜትር በላይ በእግር በመጓዝ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ እየተመሙ ነዉ። አብዛኞቹ ከመካከለኛው አሜሪካ እና ከቬኔዙዌላ መምጣታቸዉ የተነገረዉ እንዚህ ስደተኞች ጓቲማላ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው በታፓቹላ ከተማ ውስጥ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመግባት ቪዛ መጠየቂያዉ ጊዜ በጣም ረጅም እና ጥብቅ መሆኑን በመግለጽ መቃወም እንደሚፈልጉ ተነግሯል። ወደ አሜሪካ የእግር ጉዞ የጀመሩት እነዚህን በሽዎች የሚቆጠሩትን ስደተኞች ፖሊስ እና የመጀመርያ የህክምና እርዳታ ተሽከርካሪዎች እንዳጀቧቸዉ ተመልክቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ የበርካታ የደቡብ አሜሪካ ሃገራት መንግሥታት እና የመንግሥታት ተጠሪዎች ዩናይትድ ስቴትስ የኢሚግሬሽን ፖሊሲዋን እንድታላላ በተደጋጋሚ ጥሪ እያቀረቡ መሆኑ ይታወቃል።
እግር ኳስ፤ ሜሲ ለስምንተኛ ጊዜ የወንዶች ባለን ደ ኦር አሸናፊ ሆነ
አርጀንቲናዊው የኢንተር ማያሚ አጥቂ ሊዮኔል ሜሲ በወንዶች እግር ኳስ የባለን ደ ኦር ሽልማትን ዘንድሮ ለስምንተኛ ጊዜ አሸነፈ። የ36 ዓመቱ ሜሲ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የኳታር ዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ሃገሩን ለክብር ማብቃቱ፤ በፓሪስ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ዕውቅናን ለማግኘት አብቅቶታል። ሊዮኔል ሜሲ በፓሪስ በተካሄደው ምርጫ "የፈረንሳይ እግር ኳስ" በተሰኘው የንግድ መጽሔት ኖርዌያዊዉን የማንቸስተር ሲቲ አጥቂ ኧርሊንግ ኦላንድን በሁለተኛነት ፤ ብሎም ፈረንሳዊውን የፓሪ ሳን ጃርሞ ምርጥ ተጨዋች ኪሊያን ምባፔን በሦስተኛነት አስከትሎ ነዉ፤ የዓመቱ ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋች ተብሎ ሽልማቱን የወሰደዉ። የቀድሞው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ የ62 ዓመቱ ሎታር ማቲያስ በባሎን ደ ኦር የሜሲን መሸለም «ቧልት» ሲል በብርቱ ተችቷል። ይልቁንስ በዘንድሮ ብቃቱ መሸለም የሚገባው ሁለተኛ ደረጃ ያገኘው ኧርሊንግ ኦላንድ ነበር ብሏል ። ትውልደ ቱርክ ቤተሰብ ያለው ጀርመናዊዉ ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋች ኢልካይ ጉንዶዋን በፓሪሱ ሥነ-ስርአት 14ኛ ወጥቷል። በሴቶች ምድብ የስፔኗ የዓለም እግር ኳስ ባለድል እና አይታና ቦንማቲ አንደኝነቱን ይዛ አሸንፋለች። የጀርመን የሴቶች ብሔራዊ ቡድን አንበል አሌክሳንድራ ፖፕ በበኩልዋ በዉድድሩ ሰባተኛ ደረጃን አግኝታለች።