ኢትዮጵያ ሊቲየምን ጨምሮ በአምስት ዘርፎች የጀርመን ኩባንያዎችን መዋዕለ-ንዋይ ትፈልጋለች
ረቡዕ፣ ኅዳር 19 2016የኢትዮጵያ መንግሥት ሐይድሮጅን ለማምረት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ከታላቁ የኅዳሴ ግድብ ኃይል ለመመደብ ዝግጁ እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስትሩ ኢዮብ ተካልኝ ባለፈው ሣምንት በበርሊን ከተማ ለጀርመን ባለወረቶች ተናግረዋል። ውኃን ወደ ኦክስጅን እና ሐይድሮጅን በመቀየር የሚመረተው የኃይል አይነት ጀርመን በካይ ከሚባለው ነዳጅ ለመላቀቅ ተስፋ ያደረገችበት ነው። የጀርመን መንግሥት በካይ የሚባለውን የኃይል ምንጭ ከ20 ዓመታት ገደማ በኋላ ሙሉ በሙሉ በሐይድሮጅን የመተካት ውጥን አለው። ይሁንና ሀገሪቱ እስከ 70 በመቶ የሐይድሮጅን ፍላጎቷን ከውጭ ማስገባት ይጠበቅባታል።
በበርሊን በተካሔደው የቡድን 20 ኮምፓክት ዊዝ አፍሪካ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ ባለወረቶች ሐይድሮጅን ማምረት ቢሹ በኢትዮጵያ ለሥራው የሚያስፈልገው ታዳሽ ኃይል እንደማይቸግራቸው ቃል ገብተዋል። ዶክተር ኢዮብ “ይኸን ጥቅም ላይ ያልዋለ እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ዕድል የሚቀይር ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ካለ ከታላቁ የኅዳሴ ግድብ ለዚህ ፕሮጀክት 500 ሜጋ ዋት ኃይል ለመመደብ ዝግጁ ነን” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ የጀርመን ኩባንያዎች ወደ ታዳሽ ኃይል ለሚደረገው ሽግግር ኹነኛ ግብዓት የሆነው ሊቲየምን ጨምሮ በማዕድን ልማት ዘርፍ እንዲሳተፉ ትሻለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ተስፋ ከጣሉባቸው ማዕድናት አንዱ የሆነው ሊቲየም ለቅንጡ ስልኮች እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ባትሪ ዋንኛ ግብዓት ነው።
“እንዳለመታደል ሆኖ የማዕድን እምቅ አቅማችንን ገና መረዳት የጀመርን ይመስለኛል። ሁለተኛ ማዕድኖችን በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር አለ። ለምሣሌ ያክል ሊቲየም ጥሬውን እየተላከ አንዳንዴም ወደ ጎረቤት ሀገሮች እየሸሸ ሀገሪቱን ሳይጠቅም ቆይቷል” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው መንግሥታቸው በዘርፉ ማሻሻያ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሊቲየምን ጨምሮ በማዕድን ልማት ዘርፍ መሠማራት የሚሹ ጀርመናውያን ባለወረቶች ወደ ኢትዮጵያ ጎራ እንዲሉ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ጋብዘዋል። “ሊቲየምን ጨምሮ በማዕድን ልማት ዘርፍ የተመሰከረለት ኢንቨስተር ካለ ጥሩ ዕድል አለ” ሲሉ ለጀርመን ኩባንያዎችን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ግብዣ በኤሌክትሪክ መኪና ግንባታ ጠንካራ ኢንዱስትሪ ከመሠረቱት የዓለም ሀገራት አንዷ የሆነችው የጀርመን ባለሥልጣናት በቸልታ የሚያልፉት አይደለም።
“የጀርመን መንግሥት በወሳኝ ጥሬ ዕቃዎች ዘርፍ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለማግኘት በጣም ፍላጎት አለው” ያሉት የጀርመን የኤኮኖሚ ጉዳዮች እና የአየር ንብረት ጥበቃ ሚኒስቴር (BMWK) ምክትል ዳይሬክተር ኡርሱላ ቦራክ ዘርፉ “በጣም ስሱ እና ለወደፊቱ በጣም አስፈላጊ” እንደሆነ ገልጸዋል።
“ለዚህ የሚሆን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ጥሩ የሆነ የማዕቀፍ ሁኔታ ያስፈልጋል” ያሉት ኡርሱላ ቦራክ “ጥሩ ፕሮጀክት እና ኢንቨስተር ካለ” የጀርመን መንግሥት “ፖለቲካዊ ድጋፍ ያደርጋል” ሲሉ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የካበተ ሐብት እና እውቀት ካላቸው ኩባንያዎች ባሻገር ለጀርመን ግዙፍ ኤኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሚባሉት አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት ላይ ቀልቡ አርፏል። ከጀርመን ተቋማት 99 በመቶው በዚሁ ምድብ የሚጠቃለሉ ናቸው።
የጀርመን ገበያ ከሚፈጥረው የሥራ ዕድል 58.8 በመቶው የአነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት ድርሻ እንደሆነ የጀርመን የኤኮኖሚ ጉዳዮች እና የአየር ንብረት ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በሀገሪቱ ገበያ ሽያጭ እነዚህ ተቋማት ከ35 በመቶ በላይ ድርሻ አላቸው።
ዶክተር ኢዮብ እና መንግሥታቸው የኢትዮጵያ አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት የጀርመኖቹን ፈለግ እንዲከተሉ ይሻሉ። ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ “የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ አቅም አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት ናቸው ብለን እናምናለን” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው የጀርመን “ተሞክሮ በጣም ሳቢ” እንደሆነ ገልጸዋል። መንግሥታቸው “ኢትዮጵያን የሥራ ፈጣሪዎች ሀገር ለማድረግ ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ምቹ ከባቢ ለመፍጠር” እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የገንዘብ አቅርቦት አነስተኛ እና መካከለኛ ተቋማት እንዲነሱ ያግዛል የሚል ተስፋ ዶክተር ኢዮብ አላቸው።
ኢዮብ ከጀርመን ባለወረቶች የተገናኙበት መድረክ የኢትዮጵያ ጀርመን የንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ ፎረም ነው። ሕዳር 12 ቀን 2016 በተካሔደው በዚህ መርሐ-ግብር 50 ገደማ የጀርመን 24 የኢትዮጵያ ኩባንያዎች መሳተፋቸውን በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈቃዱ በየነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ግብርና እና የትምህርት ግብዓቶች አቅርቦትን ጨምሮ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ 154 የጀርመን ኩባንያዎች በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ገበያ ይገኛሉ። አምባሳደር ፈቃዱ በየነ ግን “ጀርመን ካላት አቅም እና እምቅ ሀብት አኳያ 154 ማለት በጣም ትንሽ ነው” የሚል አቋም አላቸው።
በበርሊን የተካሔደው የኢትዮጵያ ጀርመን የንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ ፎረም “በግብርና፣ በማምረቻ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፎች የበለጠ የጀርመን ኩባንያዎችን ለመሳብ” ያቀደ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። አምባሳደር ፈቃዱ የጀርመን ኩባንያዎች “መረጃ ካገኙ፣ ኢትዮጵያ ወዴት እንደሔደች ካወቁ የበለጠ ኢንቨስት ያደርጋሉ” የሚል እምነት አላቸው።
በኢትዮጵያ ጀርመን የንግድ እና መዋዕለ-ንዋይ ፎረም የተሳተፉት ዲየትሪሽ ሮገ የአዲስ አበባ ቅንጡ፣ መካከለኛ እና ማኅበራዊ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ታዝበዋል። የዲየትሪሽ ሮገ ሮክስቶን የተባለ ኩባንያ በአዲስ አበባ ቀነኒሳ ጎዳና “ከፍታ” የተባለ ግዙፍ የመኖሪያ ሕንጻ በመገንባት ላይ ይገኛል። ኩባንያቸው ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ብቅ ሲል ከመንግሥት “አስደናቂ ድጋፍ” እንዳገኘ የሚናገሩት ዲየትሪሽ ሮገ ሌሎች የጀርመን ኩባንያዎች የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ በልበ ሙሉነት የሚናገሩ ናቸው። ጀርመናዊው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ግን ዋናው ፈተና እንደሆነ አላጡትም።
“በውጭ ምንዛሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ካደረክ፤ ከፈለክ እንዴት እና መቼ መልሰህ ከሀገሪቱ ታወጣዋለህ? ሰዎች የግድ ገንዘባቸውን ማውጣት ይፈልጋሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ድንበር ተሻግረህ ኢንቨስት ስታደርግ ‘እንዴት ማውጣት እችላለሁ?’ የሚለው ጥያቄ እንዲመለስ ትፈልጋለህ” ሲሉ ጉዳዩ ለባለወረቶች አንገብጋቢ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ የገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለኢንቨስትመንት “እንቅፋት” እንደሆነ የገለጹት ዲየትሪሽ ሮገ ነው። “በጣም ዝግ ከነበረ ኤኮኖሚ ወደ ነጻ ገበያ የሚደረግ ሽግግር ከባድ በመሆኑ ችግሩን እረዳለሁ። ይኸ ደግሞ ለቢዝነስ ሥራ ትልቅ ፈተና ነው። [ሽግግሩ] በፍጥነት ተግባራዊ ቢደረግ የዋጋ ንረት ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን ስለሚችል ማኅበራዊ እና ከዜጎች በኩል ያለውን ጫና እረዳለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
ለረዥም ዓመታት የትምህርት ግብዓቶች ለኢትዮጵያ ገበያ ሲያቀርብ የቆየ የጀርመን ኩባንያ በኃላፊነት የሚመሩት ቶማስ ገርክማን የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ ለባለወረቶች አንገብጋቢ እንደሆነ ይስማማሉ። በብሬመን “የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ” የሆኑት ገርክማን “የጀርመን ባለወረቶች እጅግ ወግ አጥባቂ ናቸው። መረጋጋት እና ለሥራቸው ዋስትና ይፈልጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
“በኢትዮጵያ የሚኖርህ ማንኛውም ኢንቨስትመንት ወይም ወደ ኢትዮጵያ የምትልከው የትኛውም ሸቀጥ በጀርመን መንግሥት የሐመስ የመድን ዋስትና የሚሰጠው በመሆኑ ደስተኞች ነን” ሲሉ ገርክማን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የጀርመን ባለወረቶችን ሲጋብዝ ግን ሀገሪቱ ገጥሟት ከነበረው ጦርነት ዳፋ ገና በቅጡ አላገገመችም። በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የተቀሰቀሱ ግጭቶችም ኹነኛ መፍትሔ አልተበጀላቸውም።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት “የውስጥ ተግዳሮቶች” እንደገጠሟት የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታው ኢዮብ ተካልኝ “ብዙዎቹ የረዥም ጊዜ ዕይታ ያላቸው ኢንቨስተሮች ለአጭር ጊዜ በሚፈጠሩ ችግሮች አይናጠቡም” የሚል አቋም አላቸው።
“ባለፉት አምስት ዓመታት በአማካይ ኢንቨስትመንት በየዓመቱ እያደገ ነው የመጣው። 15 በመቶ ያክል እየጨመረ ነው የመጣው” የሚሉት ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ መንግሥታቸው ሀገሪቱ የገጠማትን ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት አለመጠናቀቁን የጠቀሱት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ “ሀገረ መንግሥት ምስረታ በየትኛውም ሀገር messy ነው። የእኛ ፍላጎት ይኸንን የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አሁን መጨረስ ነው። የእኔ ልጆች በዚህ እንዲቸገሩ አልፈልግም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ