አፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዕይታ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 23 2016ሶማሊያ የሠፈረዉ የአፍሪቃ ሕብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ሠራዊት የሚኖረው አዲስ የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር በአፍሪቃ ቀንድ "አዲስ ሥጋት" ይዞ መምጣቱን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ነሐሴ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በሶማሊያ የሚኖረው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ኃይል አወቃቀር ኢትዮጵያን "የሚያሳስብ ሆኗል" ብሎታል፡፡የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "ለአጭር ጊዜ ፍላጎታቸው እና ከንቱ አላማቸው ሲሉ በከልሉ ውጥረትን ለማቀጣጠል የሚሞክሩ" ያላቸው እና በስም ያልጠቀሳቸው ኃይሎች "ዕኩይ ተግባራቸው የሚያስከትሏቸዉን መዘዞች መሸከም ይኖርባቸዋል" ሲልም አስጠንቅቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያወጣው መግለጫ ዝርርዝር
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው ጠንከር ያለ መልዕክት የያዘው መግለጫ "ቀደም ሲል አሕጉራዊ እና አለምአቀፋዊ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን አበረታች ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉና የሚቀለብሱ ድርጊቶችን ኢትዮጵያ አትታገስም" በማለት ያስጠነቅቃል።
የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት በሶማሊያ ለሚደረገው የሰላም አስከባሪ አዲስ ሽግግር እየተዘጋጁ ባሉበት ወቅት "ቀጣናው ሊተነበይ ወደማይቻል ፈተና ውስጥ እየገባ ይገኛል" ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በሁኔታው ላይ ቀደም ሲል ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ውስጥ ወታደር ያዋጡ አገሮች ተደጋጋሚ ጥሪዎችና አስተያየቶች ትኩረት አልተሰጣቸውም ብሏል።
ሚኒስቴሩ "ሌሎች ተዋናዮች" በሚል በስም ያልጠቀሳቸው አካላት የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ እርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም ብሏል።የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ያለውን ወቅታዊ አለመግባባት ለመፍታት እንዲያስችል በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይም ተሳትፎ እያደረገች ቢሆንም፣ የሶማሊያ መንግሥት እነዚህን ጥረቶች ከማጠናከር ይልቅ "ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሠራ ይገኛል"፡፡ ሲል ወቅሷል።
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የሚኒስቴሩ ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ ተጨማሪ መብራሪያ በነገው ዕለት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አፅቀ ሥላሴ ይሰጣል ሲሉ መልሰዋል። ቃል ዐቀባዩ ባለፈው ሳምንት መግለጫቸው ተከታዩን ብለው ነበር።
"ከአትሚስ በኋላ የሚዋቀረው ኃይል አወቃቀሩ በውስጡ ሌላ ሠራዊት የሚያዋጡ ሀገራት ተሳትፎ እና የኃይሉ አወቃቀር ጭምር በቀጣናው ውስጥ አዲስ ውጥረትን በመፍጠር ለቀጣናው ያልታሰበ የሰላም እና የመረጋጋት ችግር እንደዚሁም ክልሉን አደጋ ውስጥ ሊጥል በማይችል መልኩ በጥንቃቄ ሊዋቀር እንደሚገባ ኢትዮጵያ ታምናለች"።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሶማሊያ ለማሰማራት የታቀደውን አዲስ የሰላም ተልዕኮ የማዘጋጀት እና የመፍቀድ ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ሁሉ "በቀጣናው የሚገኙና ቀደም ሲል ወታደር አዋጭ የሆኑ ሀገራትን ተገቢ የሆኑ ሥጋቶች ሁሉ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል"፡፡ ሲል በመግለጫው አሳስቧል።
ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ነቢዩም ይህንኑ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ በአፅንዖት አንስተውት ነበር።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ "ለሶማሊያ ደኅንነት እና መረጋጋት መስዋዕትነት የከፈሉትን የኢትዮጵያን እና የሌሎችን ሕጋዊ ብሔራዊ ጥቅም ችላ ማለት አይቻልም።" ሲሉ በኤክስ ጽፈዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ተልእኮ አወቃቀሩ የሚታደስበት ምክንያት
የአፍሪካ ሕብረት የሽግግር ተልእኮ(ATMIS) በሶማሊያ የተሰጠውን የሰላም ማስከበር ኃላፊነት ታኅሳስ ወር ላይ ለሶማሊያ መንግሥት አስረክቦ ይወጣል የሚል እቅድ የነበረ ቢሆንም፣ የአልሸባብ ከጊዜ ወደ ጉዜ እየተጠናከረ መምጣት፣ ቡድኑ ሰው አልባ የጦር አውሮፕላን - ድሮኖችን ጭምር ስመታጠቁ መረጃዎች መውጣታቸው እና የጥቃት ስልቱ ውስብስብ እየሆነ በመምጣቱ እንዲሁም የሶማሊያ የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት ታስቦ የነበረውን ኃላፊነት በራሰቸው ለመወጣት በሚችሉበት አቅም ላይ አለመገኘታቸው እቅዱ እንዲከለስ እና አዲስ አወቃቀር እንዲኖር አስፈላጊ ሆኗል። ይህም ከጅምሩ ውዝግቦችን አስነስቷል።
ትናንት የጦር መሳሪያ ስለመጫናቸው የተነገረላቸው ሁለት የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች በሶማሊያ ዋና ከተመ ሞቃዲሾ አየር ማረፊያ መታየታቸው ደግሞ ውጥረቱን አባብሶታል።
ኢትዮጵያ ሶማሊያ የሉዓላዊ ግዛቴ አንድ አካል ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት በጎርጎረሲያኑ ጥር 1 ላይ ከፈረመች ጀምሮ ከሶማሊያ ጋር ያላት ግንኙነት ክፉኛ የሻከረ ሲሆን ጉዳዩም በሶማሊያ በኩል እስከ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ድረስ ሄዷል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ