አስከፊ ረሃብ በሶማልያ
ሐሙስ፣ መስከረም 5 2015በሶማልያ በረሃብ የቱጎዱ ዜጎች ጉዳይ አሳሳቢ ሆንዋል ሲሉ የሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልእክተኛ ገለፁ። መልክተኛዉ ይህን የገለፁት ለሶማልያ ተጨማሪ ርዳታን ለማግኘት ከሳምንቱ መጀመሪያ ጀምሮ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶችና አባል ሀገራት ጋር በሚደረገው ስብሰባ ላይ ነዉ። በአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ሃገራት ከአራት ጊዜ በላይ የዝናብ ወራት በመቅረቱ ከብቶች እና ሰብልን አዉድሟል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለረሃብ አጋልጧል። የተመ የሶማልያ ልዩ መልክተኛ አብዲራህማን አብዲሻኩር በስብሰባዉ ላይ እንደገለፁት "እኛ የመጣነው በሶማልያ ስለሚታየዉ ቀዉስ ስፋት እና፣ ሊደርስ ለሚችለዉ ሰብዓዊ ጉዳት ትኩረታችሁን እንድትሰጡ ነው" ብለዋል። አብዲሻኩር ለሶማልያ ቃል የተገባው ርዳታ እና በሶማሊያ ወቅታዊ ፍላጎት መካከል አሁንም ሰፊ ክፍተት አለ ሲሉ ደጋግመዉ ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስከ ነሐሴ መጨረሻ ለሶማሊያ ከ 1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመስጠት ቃል ከገባዉ 67 በመቶውን እንደተሰጠ ተገልጿል። ይሁን እና በሶማልያ በቀጠለዉና የአምስተኛው የበልግ ወራት ዝናብ በመጥፋቱ የሚያስፈልገው የርዳታ መጠን እየጨመረ መሆኑ ተነግሯል። የሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልእክተኛ እንደተናገሩት ለሶማልያ አሁን በቂ ሰብዓዊ ርዳታ ካልቀረበ የረሃቡ ሁኔታ ወደ ከፍተኛ ጠኔ ይቀየራል ሲሉ አሳስበዋል። ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ ሶማሊያ ከአሥር ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በከፍተኛ ረሃብ አፋፍ ላይ ነጥ ሲሉ መናገራቸዉ ይታወቃል። በሶማልያ የሚታየዉ ረሃብ በተለይ ህጻናትን ለከባድ ጉዳት መዳረጉ ተነግሯል።
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ