1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራ ክልል ሰዎች በድርቅ የተነሳ እየሞቱ ነው

ማክሰኞ፣ መስከረም 22 2016

በአማራ ክልል በተከሰተ ድርቅ ቢያንስ 32 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ ። በድርቁ የተነሳ 53 ሺህ ግድም የቤት እንስሳት ማለቃቸው ተዘግቧል ። በክልሉ በ8 ዞኖች በተከሰተው ድርቅ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን ደግሞ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መርኃ ግብር ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታውቋል ።

https://p.dw.com/p/4X4jp
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና መርኃ ግብር ማስተባበሪያ ኮሚሽን
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና መርኃ ግብር ማስተባበሪያ ኮሚሽንምስል Alemnew Mekonnen/DW

ቢያንስ 32 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተ ድርቅ ቢያንስ 32 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ ። በድርቁ የተነሳ 53 ሺህ ግድም የቤት እንስሳት ማለቃቸው ተዘግቧል ። በክልሉ በ8 ዞኖች በተከሰተው ድርቅ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ ፈላጊ መሆናቸውን ደግሞ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መርኃ ግብር ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታውቋል ። በድርቁ የተነሳ በአሁኑ ወቅት ሰዉ እየሞተ መሆኑን፤ እንስሳትም መዳከማቸውን ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። 

አማራ ክልል ድርቅ ብርቱ ጉዳት እያስከተለ ነው

ባለፈው የክረምት ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያበተለያዩ የአማራ ክልል ዞኖች በዝናብ እጥረት፣ በበረዶ፣ በአዝርት በሽታና ሰብል በግሪሳ ወፍ  በመጎዳቱ ሰፊ የእርሻ ማሳ ያለምርት በመቀቅረቱ በርካቶች ለመፈናቀል፣ ሌሎች ደግሞ ለከፍተኛ ርሀብ ተጋልጠዋል ። በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት ደግሞ በድርቁ ምክንያት ሞተዋል፣ ታመዋልም ። ድርቅ በአጠቃው አካባቢ የሚኖሩ አንድ አርሶ አደር ድርቁ በእጅጉ ነዋሪውን እየጎዳው እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ተናግረዋል ።

«ድርቁ እንደቀጠለ ነው ያለው፣ እንስሳትም ተዳክመዋል፣ ሰውም አደጋ ላይ ነው እየሞተም ነው፣ ያጡ እቤታቸው ምንም የሌላቸው ሰዎች አሉ» ብለዋል፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ይርዳው ሲሳይ በድርቁ እንስሳትና ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መርኃ ግብር ማስተባበሪያ ኮሚሽን
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መርኃ ግብር ማስተባበሪያ ኮሚሽን። ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ ፈላጊ መሆናቸው ተገልጿል ።ምስል Alemnew Mekonnen/DW

 «4088 ሰዎች ወደ ወረዳ ማዕከል ተፈናቅለው ርዳታ ፍለጋ መጥተዋል፣ ... 32 ሰዎች ከድርቁ ጋር በተያያዘ ምክንያተ ሕይወታቸው አልፏል፣ ወደ 53 ሺህ እንስሳትም በድርቁ ምክንያት ሞተዋል» በማለት ገልጠዋል ።

በድርቁ ምክንያት ሰዎች እየሞቱ ነው

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት በበኩላቸው በወረዳው የችግሩን መጠን ለመቀነስና ርዳታ ለማቅረብ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አመልክተው፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

«በምግብ፣በመጠለያና በመድኃኒቶች እጥረት እየተሰቃየን ነው»የአማራ ክልል ተፈናቃዮች

ድርቁን ተከትሎ በሰዎች ላይ የተቅማጥ፣ የኩፍኝ፣ የትክትክ፣ የእከክ በሽታናና ርሀብ ተከስቷል፣ በእንስሳቱ ላይ ደግሞ ዶሮዎችን የሚያጠቃው፣ ፈንግል፣ ለዳልጋ ከብቶች ሞት ምክንያት የሆኑት የአባጎርባና የአባ ሰንጋ በሽታዎች መከሰታቸውን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል በክልሉ 8 ዞኖች በሚገኙ 22 ወረዳዎች በዘናብ እጥረትና በሌሎችም ምክንያቶች ድርቅ መከሰቱንና 1 ሚሊዮን ያህክል ሰዎች ለጉዳት ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡

«በሰሜን ጎንደር ዞን ጃን አሞራ 13 ቀበሌዎች፣ ጠለምት 8 ቀበሌዎች ፣ምስራቅ ጠለምት 4 ቀበሌዎችና  በየዳ 2 ቀበሌዎች ዝናብ ያልጣለባቸው ቀበሌዎች ናቸው፤ በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደርሳሕላ ዝናብ ያልጣለበት ወረዳ ሲሆን ፣ አበርገሌና ዝቋላ የተቆራረጠ ዝንብ የነበረባቸው ናቸው፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኪንፋዝና ምስራቅ በላሳ፤ በደቡብ ጎንደር ዞን መቀጠዋና እብናት፤ በደቡብ ወሎ ዞን አርጎባ፤ በሰሜን ወሎ ዞን ራያ፣ ሀብሩና መቄት ወረዳዎች የዝናብ እጥረት የነበረባቸው ናቸው፡፡ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር  ደግሞ ባቲ፣ አርጡማና ጂሌ ጥሙጋ ከፊል ጉዳት ያለባቸው ናቸው፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ምንጃር፣ በረኸት፣ ቀወትና አንፆኪያ ምርት በግሪሳ ወፍ የተጎዳባቸው ወረዳዎች ናቸው፡፡ በተገኘ መረጃ መሰረት አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች በዚህ ድርቅ ለጉዳት የተጋለጡ ናቸው፡፡”

 ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ረጂ ድርቶች ርዳታ አቋርጠዋል

ረጂ ድርጅቶች ከግንቦት 2015 ዓ ም ጀምሮ ርዳታ ማቆማቸውን ጠቁመው አሁን እየተደረ ያለውን ድጋፍ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፡፡ «ረጂ ድርጅቶች ከግንቦት ወር ጀምሮ እርዳታ መስጠት አቁመዋል፣ ... የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመቋቋም 300 ሚሊዮን ብር መድቧል፣ 57 ሺህ 741 ኩንታል እህል ገዝተናል፣ እኛ በራሳችን በየወሩ የምንመግባቸው 51 ሺህ 532 ተፈናቃይ ወገኖች አሉ፣ አሁን እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ከ20 ቀን በፊት ጀምሮ ለሰሜን ጎንደር ዞን ለ34ሺህ 146 ተረጂዎች  5ሺህ 122 ኩንታል፣ ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን 8 ሺህ ተጠቃሚዎች 1ሺህ 200 ኩንታል  ለደቡብ ጎንደር ዞን 5ሺህ ተጠቃሚዎች 750 ኩንታል ለዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር 4000 ተረጂዎች 600 ኩንታል፣ ለደቡብ ወሎ ዞን  7ሺህ 574 ተጠቃሚዎች 1ሺህ 136 ኩንታል ፡፡ በአጠቃላይ 8ሺህ 808 ኩንታል እህል ለ58 ሺህ 825 ተጠቃሚዎች ተሰራጭቷል፡፡»

ድርቁ በሰዎችና በእንስሳት ላይ ሞት ስለማስከተሉ የተጣራ መረጃ እንደሌላቸው የተናገሩት ዲያቆን ተስፋሁን በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ደግሞ ወደ አንዳንድ በድርቁ ወደ ተጎዱ አካባቢዎች እርዳታ ለማድረስ እንቅፋት እንደሆነባቸውም ገልጠዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ