በኔዘርላንድስ ምርጫ ስደተኛ ጠል የሆነው የቀኝ አክራሪ ፓርቲ አሸነፈ
ሐሙስ፣ ኅዳር 13 2016በኔዘርላንድስ ትላንት ረቡዕ በተካሔደ ምርጫ እስላምና ጠል፤ ስደተኛ ተቃዋሚ እና ብዙዎቹን የአውሮፓ ህብረትን ፖሊስዎች የማይደግፈው የሆላንድ ነጻነት ፓርቲ (ፔቬቬ) ከፍተኛውን ድምጽ አግንቶ ትልቁ ፓርቲ ለመሆን በቅቷል። የፓርቲው መሪ ሄርት ቪልደርስ የፓርቲያቸውን ውጤት የማይታመን በማለት ነበር የገለጹት።
“በኔዘርላንድስ ትልቁ ፓርቲ! እላችኋለሁ ሆላንዶች ዛሬ በግልጽ ተናግረዋል። በጣም መሮናል ብለዋል። ከእንግዲህ ሆላንዳዊ ቁጥር አንድ ተጠቃሚ እንዲሆን እናደርጋለን” ያሉት ሄርት ቪልደርስ “ተስፋ አለን፤ ሆላንዶች አገራቸውን ዳግም የራስቸው ያደርጋሉ” በማለት ይህ ቀን በፖለቲካ ህይወታቸው ትልቁ የደስታ ጊዜያቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የብሪታኒያ ተገን ጠያቂዎችን ወደ ርዋንዳ ለማጓጓዝ የያዘችው ዕቅድ
ፓርቲው ሊመረጥ የቻለባቸው ምክንያቶች
የስደተኞች ጉዳይ እና የኑሮ ውድነት ዋናዎቹ የምርጫ ዘመቻ አጀንዳዎች የነበሩ ሲሆን በነባሮቹ ፖለቲከኞች እና ፓርቲዎች ላይ የተፈጠረው የመሰላቸት ስሜት ይህን አክራሪ ፓርቲ ተመራጭ እንዳደረገው ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ዊለም የተባሉ የዚሁ ፓርቲ መራጭ “እኔ ዘረኛ አይደለሁም፤ ግን ለተሻለ ዕድል ወደ አገራችን በብዛት የሚፍልሰው ስደተኛ እንዲቆም እፈልጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል። “ይህ አገር ትንሽ አገር ነው። ቤት መስራት ብንፈልግ ሰማይ ላይ አንሰራም። ስለዚህ መፍትሄ መፈለግ አለበት” የሚሉት ዊለም “መፍትሄው ስደተኞችን ማቆም ነው” በማለት የሄርት ዊልድርስ ፓርቲ ይህን እንዲያደርግ እንደመረጡት ሲናገሩ ተሰምተዋል።
መንግስት መመስረት ይችላልን?
ይህ የቀኝ አክራሪ ፓርቲ አሸናፊና ትልቁ ፓርቲ ይሁን እንጂ ከ150 የፓርላማ መቀመጫ ውስጥ 37ቱን ብቻ እንዳገኘ ነው የተገለጸው። በመሆኑም መንግስት ለመሆን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ጥምረት መፍጠር የሚኖርበት ሲሆን፤ ከዚህ ፓርቲ ጋር የትኞቹ ፓርቲዎች ለመስራት ፈቃደኞች እንደሚሆኑ ግን ገና አልታወቀም። የኢሮ ነውስ ጋዜጠኛዋ ፊርናንዴ ቫን ቴትስ “የመራጮች መልዕክት ግልጽ ነው። በስደተኞች እና ፈላስያን ላይ ጠንካራ አቋም መያዝ አለበት የሚል ነው” ስትል ተናግራለች።
የአውሮጳ ሕብረት በስደተኞች ጉዳይ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ
“ሚስተር ሄርት ይህን ለማድረግ ቃል ገብተዋል” የምትለው ጋዜጠኛ “አላማቸውን ለማስፈጸም በመንግስታቸው ውስጥ የሚገቡ ሌሎች ፓርቲዎች ይፍልጋሉ፤ ግን የሚሳካላቸው ስለመሆን አለመሆኑ ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው” በማለት በኔዘርላንድስ ፖለቲካ፤ አሸናፊና ትልቁ ፓርቲ ተሁኖም መንግስት ለመመስረት አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጻለች።
በአውሮፓ ህብረት ፖለቲካ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተዕጽኖ
በሆላንድ አክራሪው የነጻነት ፓርቲ ትልቁ ፓርቲ ሆኖ መውጣቱ የኒዘርላንድስን ፓለቲካ ብቻ ሳይሆን የአውሮፓን ፖለቲካም እንድሚያናጋው ይታመናል። ከሰባት አመታት በፊት ኔዘርላንድስ በህብረቱ የመቆየቷ ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ እኒዲወሰን ሲጠይቁ የነበሩት ፖለቲከኝ ዊልደርስ፤ ዛሬም ተመሳሳይ ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ ባይባልም፤ በበርካታዎቹ የህብረቱ አጀንዎች እና በዩክሬን ጦርነት ጭምር ግን የተለየ አቋምና ፍላጎት አላቸው።
በስደተኞች ቀውስ ላይ የመከረው የአውሮጳ ኅብረት
ከሁሉም በላይ ግን በሆላንዱ ምርጫ የተገኘው ውጤት በሌሎቹ የህብረቱ አገሮች ያሉ ብሄርተኞች ጎልብተው እንዲወጡ ሊያግዝና ይህም በአውሮፓ ህብረት የወደፊት የፖሊሲ አቅጣጫ ላይ ተጽኖ እንዳያሳድር ያሰጋል።
በስደተኞች እና መጤዎች ህይወት ላይስ?
በሆላንድ በርካታ ኢትዮጵያውያንም እንደሚኖሩ የሚታወቅ ሲሆን ይህ አዲስ የፖለቲካ ክስተትና የጸረ ስደተኛ ስሜት መናር፤ በስደተኛው እና መጤው ህብረተስብ ህይወት ላይ ሊያሳድረው የሚችለውን ተጽኖ በሚመለከት የሆላንድ የበርካታ አመታት ኑዋሪ የሆነውንና በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተሳትፎው የሚታወቀውን የሱፍ ገደፋው “ኔዘርላድ በጥምረት የሚታወቅ አገር ነው። አንድ ፓርቲ ብቻውን አሸንፎ የሚወጣበት ሁኔታ አልነበረም፤ አይኖርምም” በማለት ተናግሯል።
ገበያው ንጉሴ
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር