1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

በኢትዮጵያ ሐቀኛ የሽግግር ፍትሕ እንዲሰፍን አሜሪካ ጥሪ ማቅረቧ

ዓርብ፣ ጥቅምት 23 2016

በኢትዮጵያ ተበዳዮችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ ስርዓት እንዲሰፍን ዩናይትድስቴትስ ጥሪ አቀረበች። ብሊንከን፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ያስቆመው የሰላም ስምምነት አንደኛ ዓመት በማስመልከት ባወጡት መግለጫ፤ በዐማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱትን ግጭቶች ለማስቆም በአስቸኳይ ውይይት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

https://p.dw.com/p/4YNpu
የዩናይትድስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን
የዩናይትድስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንምስል Elizabeth Frantz/REUTERS

በዐማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱትን ግጭቶች ለማስቆም በአስቸኳይ ውይይት እንዲደረግ ተጠየቀ

በኢትዮጵያ ተበዳዮችን ማዕከል ያደረገ የሽግግር ፍትሕ ስርዓት እንዲሰፍን ዩናይትድስቴትስ ጥሪ አቀረበች። የዩናይትድስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ያስቆመው የሰላም ስምምነት አንደኛ ዓመት በማስመልከት ባወጡት መግለጫ፤ በዐማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱትን ግጭቶች ለማስቆም በአስቸኳይ ውይይት እንዲደረግ ጠይቀዋል። በአትላንቲክ ካውንስል ከፍተኛ ባልደረባ አቶ ገብርኤል ንጋቱ ለዶይቸ ቨለ እንዳሉት፣በሰላም ስምምነቱ ላይ አተገባበር ላይ የተከሰቱ ክፍተቶች በአካባቢው ዘላቂ መረጋጋት እንዳይሰፍን አድርጓል።  ጦርነቱ በአስቸኳይ ይቁም፦ ዩናይትድ ስቴትስ

የሰላም ስምምነቱን አንደኛ አመት አስመልክቶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ባወጡት መግለጫ፣ዩናይትድስቴትስ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡና በደል የደረሰባቸውን ሰዎች እንደምታስታውስ አመልከተዋል። እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን ሰላምና ፍትሕ ለመደገፍ ቃል እንገባለን ብለዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣በሰላም ስምምነቱ አተገባበር ላይ መሻሻል አሳይተዋል ባሏቸው፣የትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር መመመስረት፣አስፈላጊ የአገልግሎቶች እንደገና መጀመርና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጓቾች ተደራሽ መደረጋቸውን አወድሰዋል። ይሁን እንጂ፣በሰላም ስምምነቱ አተገባበር ላይ የቀሩ ተግዳሮች እንዳሉ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ መግለጫ አብራርቷል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የቀጠናውን አገራት ነጻነት፣ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት በማክበር ጠብ ከሚያጭሩ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። በዐማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉት ግጭቶች ያሳስቡናል ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣በቀላሉ ሊታወክ የሚችል ያሉትን የኢትዮጵያን ሰላም አደጋ ላይ እንደጣለው አመልክተዋል።

የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት
የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

በዐማራና በኦሮሚያ ያሉ ግጭቶችን ለመፍታት በአስቸኳይ ውይይት እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል። እንዲሁም፣ በሃገሪቱ የተለያዩ ወገኖች የቀጠለው የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና ጥቃት፣የመርዛማ ንግግሮች መስፋፋት፣ በጦርነት ምክንያት የሳሳውን ማኀበራዊ ትስስር የበለጠ እየሸረሸረው እንደሆነ ስጋታቸውን ገልጸዋል። አስተማማኝ የሽግግር ፍትሕ፣ሐቀኛና አካታች ብሔራዊ ምክክር በመላው ሃገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታወቀዋል። ስለ ሰላም አተገባበሩ ሂደት ዶይቸ ቨለ አስተያየት የጠየቃቸው፣በአትላንቲክ ካውንስል ከፍተኛ ባልደረባ አቶ ገብርኤል ንጋቱ፣ በዋነኛነት ይካሄድ የነበረውን ጦርነት ለማስቆም ማስቻሉን ይጠቅሳሉ። "በዚህ አንድ አመት ውስጥ ዋናው ከሁሉም በላይ ያን ይካሄድ የነበረውን ጦርነት ማስቆሙ ነው፤አሜሪካኖች በዋነኛነት የሚያነሱት እሱን ነው።" ይሁንና በስምምነቱ አተገባበር የተከሰቱ ክፍተቶች በአካባቢው ዘላቂ የሆነ መረጋጋት እንዳይኖር ማድረጉን ከፍተኛ ተመራማሪው አብራርተዋል። ለኢትዮጵያ ጦርነት የአሜሪካ የመፍትሔ ሐሳብ

"በእዛ አካባቢ አሁንም ሰላም ሙሉ በሙሉ ሊወርድ እንዳልቻለ፣ኤርትራ ትውጣ የሚለው ጥያቄ ረጋ ተብሎ ሲመረመር፣ ህወሓት እንዳለ ታጥቆ ተቀምጦ ጥሎ መውጣት መልሶ በህወሓት መጠቃት ነው የሚል አስተያየት ያለ ይመስለኛል።እና የኤርትራ መውጣት ከህወሓት መሳሪያውን ከማስቀመጥ ጋራ በጣም በቅርብ የተሳሰረ ነው። በተጨማሪም፣በዐማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት፣ከሰላም ስምምነቱ አተገባበር ጉድለት ጋር ተያያዥነት እንዳለው አቶ ገብርኤል አስረድተዋል። "በዐማራው ክልል የሚታየው አንዳንድ አለመግባባት ዋናው መንሴው፣የዐማራ ፋኖ እና ልዩ ኀይል፣መሣሪያውን አውርዶ ጦር ኀይሉ ወይም ፖሊስ ውስጥ ይግባ ሲባል፣እኛ የትግራይ ህወሓት እንዳለ ጦርሩንም መሳሪያውን ይዞ እንዴት አድርገን ነው እኛ ምኑን አምነን ነው?ያ እንዳለ እንዴት አድርገን ነው መሳሪያ አውርደን የምንዋሃደው የሚለው እና በአካባቢው ያለው አለመረጋጋትና ቀጣይ ግጭት ስትመለከት፣ ዞሮ ዞሮ የስምምነቱ አለመከበር ነው፤ አሁን ያለው ችግር የፈጠረው።እና ወደፊት ለመሄድ ይህን ሁኔታ እንደገና ተመለሶ ዐይቶ ቀሩ የተባሉትን ያልተተገበሩ ስምምነቶችን ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል ብዬ እገምታለሁ።

ታሪኩ ኃይሉ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ