አንድ ዓመት የሞላው ግጭት የማቆም ስምምነት
ሐሙስ፣ ጥቅምት 22 2016የዛሬ ዓመት ፕሪቶሪያ-ደቡብ አፍሪቃ ግጭትን የማስቆም ስምምነት የመጀመርያና ዋናውን ዓላማዉን ከግብ ማድረሱን አንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ አስታወቁ። ተንታኙ እንደሚሉት ትጥቅ በማስፈታት እና የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ኑሮ በመመለሱና ችግሮችን በንግግር ፣ በመፍታቱ ረገድ አሁንም ብዙ ይቀራል። በጦርነቱ ወቅት ከፌዴራል መንግሥቱ ጎን በመሰለፍ ድጋፍ ይሰጡ የነበሩና ጦርነቱ እንዲቀጥል ያበረታቱ ሰዎች ግን ባሁኑ ወቅት አንድም ከመንግሥት ርቀዋል ወይም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በአብዛኛው የሰሜን ኢትዮጵያ ተብሎ ሲገለጽ የቆየውና የተመዘገበው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ አንደኛዋ ርእሠ መዲና ፕሪቶሪያ በዝግ ለአሥር ቀናት ንግግር እና ድርድር ከተደረገበት በኋላ ልክ የዛሬ አንድ አመት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ. ም በተኩስ ማቆም ስምምነት ፊርማ መቋጨቱ ይታወሳል። አዲስ አበባ ውስጥ በምኖርበት አካባቢ የምትገኝ አንድ የልጆች እናት በዚሁ ጦርነት ልጇ የመከላከያ ሠራዊት አባል ሆኖ ሲሳተፍ ማይጠምሪ በተባለው የዐውደ ውጊያ ግንባር ላይ እንደሞተ ከተነገራት ሦስት ወር ቢሆናት ነው።
ይህቺ እናት ልጇ "ትርጉም የለሽ" ባለችው ጦርነት ሰለባ እንደሆነ አጫውታኛለች። ይሄው በሰላሳዎቹ መጀመርያ ላይ የሚገኝ ልጇ ለመጨረሻ ጊዜ በግንባር እያለ በጓደኛው በኩል ኢንተርኔት ያለበት ቦታ አስልኮ የላከላትን ፎቶውን በትልቁ አሳጥባ ጥቁር ለብሳ በመብሰክሰክ ላይ የምትገኘው እናት የደረሰባትን ሀዘን በድምፅ ቅጂ ለመናገር ባለመፈለጓ አስተያየቷን ማካተት አልቻልኩም።
ጦርነቱን በሙያ ፣ በልምድ እና በሀሳብ ይደግፉ የነበሩ አንድ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል አሁን ዝምታን ምርጫ አድርገዋል። እኒህ ሰው በወቅቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሕወሓትን እስከመጨረሻው እንዲያጠፋ ያልተቋረጠ የሚዲያ ቅስቀሳ ካደረጉት ምካከል ናቸው። ዛሬ ላይ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቀናቸው "ለሀገሬ ፀሎት ከማድረግ በቀር ምንም ማለት አልሻም" ብለዋል።«የሰላም ስምምነቱ በምልዓት ገቢራዊ አልሆነም »ህወሓት
የእኒህ ሰው ሀሳብ እንዲህ ቀረበ እንጂ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ሆነው ጦርነቱን ግፋ በለው ሲሉና ድጋፍም፣ ማበረታቻም፣ ስንቅም ሲያቀብሉ የነበሩ ስመ ጥር ፖለቲከኞች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ስፖርተኞች ዛሬ አንድም ዝምታን መርጠዋል ፣ አልያም ከተደረሰው የተኩስ ማቆም ስምምነት በኋላ ከመንግሥት አካባቢ ገሸሽ ብለዋል።
በዘጠናዎቹ መጀመሪያ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በገባችበት ጦርነት ለሀገሩ ኢትዮጵያ የቆሰለ አንድ ጎልማሳ መንግሥት ከሕወሓት ጋር አድርጎት የነበረው ጦርነት በሠራዊቱ አሸናፊነት እንዲደመደም ከሚወዱት አንዱ ነበር። አስተያየቱን ጠይቀናል።
"ስምምነቱ ያመጣው ፍሬ ሐሳብ እናቶች የሞቱ ልጆቻቸውን እንዲረዱና እንዲያለቅሱ እንጂ ሌላ ያመጣው ነገር የለም"ዉይይት፤ የፕሪቶርያዉ ስምምነት በርግጥ ተፈጻሚ እየሆነ ነዉ?
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ በጉዳዩ ላይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ስምምነቱ ዋናውንና አንደኛውን ግቡን አሳክቷል። "ተኩስ መለዋወጥን ሙሉ በሙሉ ማቆም የሚለውንና የመጀመርያ ዋናውን ግቡን አሳክቷል"
ስምምነቱ ምን አሳካ ? ምንስ ሳያሳካ ቀረ ?
የስምምነቱ አተገባበር የአንድ ዓመት ጉዞ ብዙ ሊነሱ የሚችሉ ጎደሎዎች አሉት የሚሉት እኒህ ሰው ተፋላሚዎችን እንደገና ማቋቋም እና ማህበራዊ ፣ ሥነ ልቦናዊ ጉዳታቸውን ማከም ላይ ተስተውሏል ያሉት ሥራ አለመኖርና የፖለቲካ መፍትሔ ለመስጠት የሚጠበቀው የስምምነቱን አንቀጽ አብነት ጠቅሰዋል።
በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተቋቋመው ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን በ ስምንት ክልሎች ውስጥ 371 ሺህ 971 የቀድሞ ተዋጊዎችን ምለየቱና እስከ ሕዳር 30 2016 ዓ. ም ድረስ በመጀመሪያ ዙር 75 ሺህ ያህሉ እንዲበተኑ ይደረጋል ማለቱ ይታወሳል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ በአማራ ክልል ያለውን የፀጥታ ሁኔታ አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ ስለ የፕሪቶሪያው የተኩስ ማቆም ስምምነት ያሉት ነገር የለም። ይልቁንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከቀናት በፊት በአማራ ክልል ንፁሃን ዜጎች በድሮን እና በከባድ መሣሪያ ስለመገደላቸው ፣ አሳሳቢ ያለው የሴቶች መደፈር ወንጀል እና ከሕግ ውጪ ግድያ ስለመበራከቱ ኮሚሽኑ ያወጣውን መግለጫ ሚኒስትሩ አጣጥለውታል።
ሰለሞን መጬ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ