1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል መርዶ መንገሩ ቀጥሏል

ማክሰኞ፣ መስከረም 22 2016

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት ሕይወታቸውን ያጡ የቀድሞ የክልሉ ተዋጊዎች የሚዘክር የተባለ ብሔራዊ ሐዘን በክልሉ በቅርቡ እንደሚታወጅ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ። በክልሉ መርዶ መንገሩ ቀጥሏል ።

https://p.dw.com/p/4X4r9
ትግራይ ክልል፥ ኢትዮጵያ
በትግራይ ክልል በጦርነቱ ሕይወታቸውን ላጡ የኅሊና ጸሎት ሲደረግ፦ ኢትዮጵያምስል Million H. Silase/DW

በትግራይ ክልል ብሔራዊ ሐዘን እንደሚታወጅ ተገልጿል

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ወቅት ሕይወታቸውን ያጡ የቀድሞ የክልሉ ተዋጊዎች የሚዘክር የተባለ ብሔራዊ ሐዘን በክልሉ በቅርቡ እንደሚታወጅ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ። ከዚህ በተጨማሪ በቀጣይም በጦርነቱ ወቅት ላለፉ ቤተሰበቦች፣ የጦር ጉዳተኞች እንዲሁም ለተቀረው የትግራይ ኃይሎች ጦር አባላትን «ልዩ ተጠቃሚ» የሚያደርግየተባለለት የሕግ ማእቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑም ተገልጿል ። ይህ የህግ ማእቀፍ በቅርቡ እንደሚፀድቅ የቀድሞ የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ እና የአሁኑ የክልሉ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ ተናግረዋል።

ከጦርነቱ ፍፃሜ ረዥም ወራት በኋላ በትግራይ በጦርነቱ ወቅት በየግንባሩ የሞቱ ታጋዮች መርዶ ካለፉት ሳምንታት ወዲህ በስፋት እየተነገረ ይገኛል። በመቐለ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ መመልከት እንደሚቻለው በርካታ ቤተሰቦች በጦርነቱ ወቅት የሞቱ የቀድሞ ታጋዮች መርዶ ተነግረው ለቅሶ ተቀምጠው ይገኛሉ። ከዚሁ የመርዶ መንገር ስነ-ስርዓት ጋር ተያይዞ ትላንት መግለጫ የሰጡት የቀድሞ የትግራይ ኃይሎች አዛዥ እና የአሁኑ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ አስተዳደራቸው በጦርነቱ ወቅት ሕይወታቸው ያጡ የቀድሞ የትግራይ ኃይሎች የሰራዊት አባላት የመለየት እና ማጣራት ስራ አከናውኖ በይፋ ለሁሉም ቤተሰብ እንደሚነግር እና ብሔራዊ ሐዘንም እንደሚታወጅ አስታውቀዋል። በጦርነቱ ፥ በጦር ሜዳ ይሁን ደጀን የትግራይ ህዝብ በርካቶች አጥቷል ያሉት የቀድሞ የትግራይ ሐይሎች ዋና አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ ፥ የተከፈለው መስዋእትነት የትግራይ ህዝብ ድህንነት እና ህልውና በማረጋገጥ ሂደት የደረሰ ኪሳራ ነው ብለውታል። ጠላት ያሉት ኃይል ትግራይ ላይ ሊያደርሰው ፈልጎ ከነበረ ኪሳራ ጋር ሲነፃፀር የሆነው ዝቅተኛ ነው ያሉት ጀነራሉ ይሁንና በጦር ግንባር የደረሰው ሞት እንዲሁም በተለያየ ደረጃ የሚገለፅ የአካል ጉዳት "ትንሽ የማይባል" በማለት፥ ቁጥሩ በትክክል ሳያስቀምጡ ቀርተዋል።

ትግራይ ክልል በረሐብ ሰዎች እየሞቱ ነው

ጀነራል ታደሰ በመግለጫቸው በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ለመርዶ አመቺ ያልሆነ ሁኔታ ቢኖርም፣ መደረግ ስላለበት በይፋ መርዶ እንነግራለን ብለዋል። ጀነራል ታደሰ ወረደ «ለመርዶ በሚመች ሁኔታ ላይ ተኹኖ አይደለም የሚረዳው። ግን የግድ መሆን ስላለበት ነው ለማርዳት ወስነን ያለነው። በመጀመርያ ምዕራፍ በአስተዳደራችን ስር ያለው ሕዝብ ነው የምናረዳው። በጠላቶች ስር ባለው ቦታ ያለው ሕዝብ መርዶ አነጋገር ለብቻው እያየነው ነው። ስንጨርስ ግልፅ እናደርጋለን። ከዚህ አልፎ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና ውጭ ሀገር መጥተው ትግሉን የተቀላቀሉ አሉ። እነሱ የሚመለከት መርዶም እንዴት ነው የምንነግረው የሚለው በቅርቡ ይገለፃል። ስለዚህ በቅርቡ በዋነኝነት በአስተዳደራችን ስር ባለው ሁሉም አካባቢ መርዶ እንነግራለን» ብለዋል።

የቀድሞ የትግራይ ኃይሎች አዛዥ እና የአሁኑ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ
የቀድሞ የትግራይ ኃይሎች አዛዥ እና የአሁኑ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ በመግለጫቸው በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ለመርዶ አመቺ ያልሆነ ሁኔታ ቢኖርም፣ መደረግ ስላለበት በይፋ መርዶ እንነግራለን ብለዋል።ምስል Million H. Silase/DW

መርዶ ከመንገር በኋላባለው ፥ ቀኑ በትክክል ባይቀመጥም፥ በቅርቡ በትግራይ ብሔራዊ ሐዘን እንደሚታወጅ የገለፁት ደግሞ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው። ፕሬዝዳንት ጌታቸው «ይህ አንፃራዊ ሰላም እንዲገኝ በሺዎች መስዋእትነት ከፍለናል። የትግራይ ህዝብ ህልውናው ለማረጋገጥ በከፈለው መስዋእትነት ሕይወታቸው የሰጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቻችን ለክብራቸው በሚመጥን መንገድ ብሔራዊ ሀዘን ለማወጅ በተዘጋጀንበት፥ በቅርቡ እነዚህ ሰማእታት በይፋ በምንዘክርበት ወቅት ላይ እንገኛለን» ብለዋል።

የትግራይ ክልል አስተዳደር መርዶ ከመንገር፣ ብሔራዊ ሐዘን ከማወጅ በተጨማሪ በቀጣይ የሰማእታት ቤተሰቦች፣ የጦር ጉዳተኞች እንዲሁም የተቀረው የትግራይ ሐይሎች ጦር አባል ልዩ ተጠቃሚ የሚያደርግ የሕግ ማእቀፍ እያዘጋጀ መሆኑ የገለፁት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ይህ የሕግ ማእቀፍ በቅርቡ ፀድቆ ይፋ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ጀነራል ታደሰ «ተቋማዊ በሆነ መንገድ መቀጠል ያለባቸው ነገሮች አሉ። ሰማእታት አሉን፣ የሰማእታት ቤተሰብ አሉን። እነዚህ ቤተሰቦች የያልታገለ መጫወቻ እንዳይሆኑ በቀጣይ የሚያስፈልጋቸው እንክብካቤ አለ። ምን ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያስፈልገዋል ? ምን ዓይነት በገንዘብ የሚለካና የማይለካ ማሕበራዊ ክብር ? የሚያስፈልጋቸው ነፃ አገልግሎት የሚመለከት ፥ ለሰማእታት ቤተሰብ፣ ለጦር ጉዳተኞች እንዲሁም በተጨባጭ በሰራዊት ያሉ የሚመለከት እየረቀቀ ያለ ደንብ አለ። የመጀመርያ ደረጃ ማርቀቅ ተጠናቋል። በአጭር ግዜ በካቢኔ ፀድቆ ይታወጃል» ሲሉ አስታውቀዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ