1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትኩረት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ መጋቢት 16 2015

ወደ ሀገራቸው ገንዘብ ለሚልኩ አፍሪቃውያን ዲጅታል የገንዘብ መላኪያዎች ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው። በሌላ በኩል በታንዛኒያ በቅኝ ግዛት ዘመን ለተፈጸሙ በደሎችን ጀርመን ካሳ እንድትከፍል እየተጠየቀ ነው። የዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ርዕሰጉዳዮች ናቸው።

https://p.dw.com/p/4PEzT
Gemeinsame Sonderausstellung zur Geschichte Tansanias in Berlin
ምስል Stiftung Humboldt Forum im Berliner Schloss

ትኩረት በአፍሪቃ

ለእህት እና ለወንድም ልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ፣ ለታመመ ወላጅ የህክምና ሂሳብ  ወይም ለእህት ለወንድሞቻቸው የጡረታ  ይከፍላሉ። በዚህ መልኩ በውጭ አገር ከሚገኙ የቤተሰብ አባላት የሚላከው ገንዘብ በመላው አፍሪካ ማህበረሰቡን ይደግፋል።  

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ዙሪያ ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወደ ሀገራቸው ገንዘብ ይልካሉ።ከዚህም 800 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ባለፈው አመት 626 ቢሊዮን ዶላር (584 ቢሊየን ዩሮ)  በዚህ መልኩ መላኩን የዓለም ባንክ አስልቷል።

ነገር ግን ይህንን ወደ 1 ቢሊዮን የሚጠጋ  ማህበረሰብን የሚያካትት ገበያ ዋጋው በጣም ውድ ነው። ከየዓለማችን ጥግ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ግብይቶች በመኖራቸው ለገንዘብ ኢንዱስትሪው ትርፋማ ገበያ ቢሆንም አገልግሎቶቹ ውድ ናቸው።

በዓለም ዙሪያ፣ የመላኪያ ክፍያ  አሁንም ከሚላከው ገንዘብ በአማካኝ  6.5% ነው።  በምስራቅ አፍሪካ ወደ 9.4% የሚደርስ ሲሆን ፤እያንዳንዱ የሚላክ 100 ዶላር ከ90 ዶላር በላይ ሆኖ ይደርሳል። ነገር ግን የመላኪያ ክፍያዎቹ ከዓመት ዓመት እየቀነሱ መጥተዋል።

በጣም ርካሹ የመላኪያ ተመን ወደ 3.5% ሲሆን፤ ዲጂታል አገልግሎቶችን በመጠቀም የሚከናወን ነው። እንደ ዓለም ባንክ በዚህ መንገድ  1% ብቻ ያህሉ ይከናወናል ።

ከተባበሩት መንግስታት የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD)ፔድሮ ደ ቫስኮንሴሎስ በዘርፉ ብዙ መሰራት አለበት ይላሉ ።

«አሃዞች በመሠረቱ ገና እዚያ እንዳልነበርን ይናገራሉ። ከአራት አመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር እኛ እንሆናለን ብለን ከምንገምተው በላይ ገደላማ  መታጠፊያ ላይ ብንሆንም" በማለት ተናግረዋል።

 Kenia, Nairobi | Mobiles Bezahlsystem M-PESA
ምስል Tony Karumba/AFP/Getty Images

አገልግሎቱ ወደ ዲጂታል ለመቀየሩ ትልቁ ምክንያት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ነው። ኮቪድ በሐዋላ ዝውውር ላይ መስተጓጎል ካስከተለ በኋላ፣ ጥብቅ የማህበራዊ ርቀት መስፈርቶች በዓለም ዙሪያ  ብዙ ሰዎችን በዲጂታል ዓለም ላይ ያላቸውን ፍርሃት ወይም አለመተማመን እንዲያሸንፉ አድርጓቸዋል።

 ይህም ለቪዲዮ ስብሰባዎች እና ለዲጂታል የገንዘብ አገልግሎቶች አዲስ የገበያ ዒላማ ፈጥሯል። ለምሳሌ፣ በጎርጎሪያኑ 2020 ዓ/ም፣ በናይጄሪያ፣ በጋና እና በኬንያ በዋነኛነት የሚሰራው የሐዋላ አገልግሎት አቅራቢ አዚሞ፣ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ ከተጠበቀው በላይ የተመዘገቡ አዳዲስ ደንበኞች ወደ 200% ጭማሪ አሳይቷል።

15 አመታትን ያስቆጠረው የኬንያው ሳፋሪኮም በበኩሉ ኤም-ፔሳ  የተባለ የሞባይል ክፍያ አማራጭ አቅርቧል።ፈር ቀዳጁ የኬንያ የገንዘብ ቴክኖሎጅ ኤም-ፔሳ ዛሬ ከ56 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች አሉት። በአብዛኛው በኬንያ፣ ግን ደግሞ በታንዛኒያ፣ ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክም ጭምር። በዚህ መሠረት ኤም-ፔሳ ከ30 የሚጠጉ የሐዋላ ገንዘብ አጋሮች ጋር አብሮ ይሰራል። ከነሱ ጋር የተቀመጠ ገንዘብ በኤም-ፔሳ  በራሱ 700,000 የክፍያ ቦታዎች መቀበል ወይም ከዲጂታል የገንዘብ ቦርሳ መላክ ይቻላል ይላሉ የኤም-ፔሳ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሲቶዮ ሎፖኮይት።

«ግን በተጨማሪ ከደንበኛ እስከ የንግድ ክፍያዎች ያለውን ችሎታ እየተመለከትን ነው። ስለዚህ ለምሳሌ ብሪታኒያ ውስጥ ያለ አንድ ሰው የሆስፒታል ክፍያን በቀጥታ በኤም-ፔሳ አካውንት ውስጥ መክፈል ይችላል።እንበል እና ታንዛኒያ ላለ ሆስፒታል። ስለዚህ ያ ቀጣዩ  ደረጃ ነው። »

Nigeria Änderung der Wähung Naira
ምስል Ubale Musa/DW

እያደገ የመጣው የበይነመረብ የንግድ ዘርፍ በመተግበሪያዎች በኩል ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲሳለጥ እየተደረገ ነው።

ይሁን እንጂ አዲሱ የዲጂታል ክፍያ ለዓለም አቀፍ የወንጀል ድርጊቶችም ሊጋለጥ ይችላል።  የኤም-ፔሳ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሎፖኮይይት እንደሚሉት ይህንን ለማስቀረት በእነሱ ዘንድ ሁሉም ግብይቶች ማረጋገጫ ያላቸው ናቸው።

«በዓለም አቀፍ የገንዘብ ዝውውሮች ሁሉንም ግብይቶቻችንን በቅጽበት በማጣራት ላኪው እና ተቀባዩ ማን እንደሆነ እናውቃለን። ይህም በእኛ ፈለግ  ውስጥ እየሆነ ያለ ደህንነቱ የተጠበቀ ግብይት ነው።» በማለት ገልፀዋል።

 Kenia, Nairobi | Mobiles Bezahlsystem M-PESA
ምስል Donwilson Odhiambo/ZUMA/IMAGO

እናም M-Pesa ከዓለም የዱር እንስሳት ፈንድ (WWF) ጋር በመተባበር አገልግሎቱ ለህገ-ወጥ የዝሆን ጥርስ ንግድ ጥቅም ላይ እንዳይውል አድርጓል ብለዋል። የዓለም አቀፍ የገንዘብ ፍሰት ፖለቲካዊ ማዕቀቦችን እንዳያስተጓጉል ለማድረግም እንደ ዌስተርን ዩኒየን ያሉ ሌሎች አቅራቢዎችም ተገቢ ማጣሪያዎችን ያካሂዳሉ።

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት በዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) ባወጣው ግብ  በ2030 የሐዋላ ክፍያዎች ከፍተኛው የግብይት ዋጋ 3% ብቻ መሆን አለባቸው። ሎፖኮይይት እንዳሉት፣ ኤም-ፔሳም ለዚህ ግብ ቁርጠኛ ነው።

«በአንዳንድ አገሮች ይህ ግብ የማይደረስ ነው ይላሉ ።አስቀድሜ ልነግርህ እችላለሁ።በአንዳንድ አገሮች ደርሰናል።መኖሩ አስፈላጊ ነበር? አዎ የት መሄድ እንዳለበት አቅጣጫ ሰጥቷል።ስለዚህ መኖሩ በጣም ጥሩ ግብ ነው።» ከሁሉም በላይ ደግሞ M-Pesa እና ሌሎች ኩባንያዎች ለደንበኞቻቸው ተጨማሪ ግልግሎቶችን ያቀርባሉ ብለዋል።

«የብድር፣ የቁጠባ፣ ኢንሹራንስ፣ ጡረታ እና ሌሎች  የአገልግሎት ዓይነት ውስጥ በመግባት፤ ለተቋሙ ትርፋማ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን መስራት እንችላለን።  እና ለአገልግሎት ተቀባዮቹ በመሠረቱ ሕይወት የሚለውጥ ነው። ምክንያቱም አሁን የቀረበው ከገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት በላይ ነው።»

ወደ ሀገር የሚላከው ገንዘብ ላይ ለ20 ዓመታት በተደረገው ስልታዊ ክትትል በተለይም በችግር ጊዜ  ከፍተኛ መሆኑንም ሀላፊው ገልፀዋል።

«አንዳንድ መዋዕለ ፍሰቶች ወይም ዕርዳታ አንዳንዴም ሲቀንስ ቢታይም፤  የሚላከው ገንዘብ ግን ከፍ ይላል። ስደተኞች ለቤተሰቦቻቸው ፍላጎት ምላሽ ይሰጣሉ። እኔ እና እርስዎ እንደምናደርገው የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት አያደርጉም።ለቤተሰቦቻቸው ፍላጎት ምላሽ እየሰጡ ነው።, በአሁኑ ጊዜ ይህ አይነቱ ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በላይ ነው።, ስለዚህም ቤተሰቦቻቸው በየቀኑ እያጋጠማቸው ያለውን እውነታ  ይገነዘባሉ።

የታንዛኒያ የቅኝ ግዛት በደል

አንቂዎች  እና የታሪክ ተመራማሪዎች ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ የጀርመን የቅኝ ግዛት ታሪክ እንዳይረሳ  አድርገዋል። ቅኝ ገዥዎች ለፈፀሙት የፍትህ መጓደል  ካሳ እንዲከፍሉ  ያደረጉት ሙግትም ጉዳዩን እንደ ናሚቢያ ባሉ ሀገራት የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሆን አድርጎታል። .

በአንድ ወቅት የጀርመን ምስራቅ አፍሪካ እየተባለ በሚጠራው ግዛት አካል የነበረችው ታንዛኒያ ግን በቅኝ ግዛት ዘመን  የተፈፀመባት በደል በአንጻራዊነት ብዙ አልወራለትም።

በሁለቱ ሀገራት ያሉ ፖለቲከኞች ያለፉትን ክስተቶች በተመለከተ በግልፅ መነጋገር እና ትክክለኛ  መፍትሄ መስጠት ይፈልጋሉ።በቅኝ ግዛት ወቅት በተካሄደ ጦርነት ሰለባ የሆኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች አፅሞቻቸውን ወደ ታንዛኒያ መመለስ አንዱ ጉዳይ  ነው። ምክንያቱም የእነዚህ  ሰዎች አፅም  «የተዘረፉ ጥበባት»/looted Arts/ በሚል ከሌሎች ባህላዊ ቅርሶች ጋር በጀርመን ሙዚየሞች ተከማችተዋል። ታንዛኒያዊው የታሪክ ምሁር ፊልሞን ማቶይ እናም ህዝቦችን ለማስታረቅ እና የጋራ የወደፊት ጊዜ ለመገንባት አሁንም አልረፈደም ይላሉ።ነገር ግን ጀርመን ከቅኝ ግዛት በኋላም ከታንዛኒያ ጋር የነበራትን ግንኙነት እንዳታፈርስ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ሲሉ ይገልፃሉ።

Tansania Die Präsidentn von Tansania Samia Suluhu Hassan mit der Staatsminsterin des Auswärtigenamtes Katja Keul
ምስል Tanzania Statehouse

«እነሱ (ጀርመኖች)  ከቅኝ ግዛት  በኋላ ከታንዛኒያ ጋር የነበረውን ግንኙነት እንዳያበላሹ መጠንቀቅ አለባቸው።በዚያ ወቅት  እነሱ አልነበሩም ነገር ግን ያለፈውን ጊዜ ለማስታወስ በቅንነት ማረጋገጥ ይችላሉ። በተጨማሪም ሰዎች ትምህርት እንደወሰዱበት ያሳያል። የወሰዱት ትምህርትም   ለሌሎች   እድሎች አዳዲስ በሮችን በሕይወት ውስጥ ይከፍታል ።»

ታንዛኒያ ውስጥ በጀርመን የቅኝ ግዛት ዘመን የተፈፀመውን ግፍና በደል የመቀበል ሂደት ገና በጅምር ላይ ነው። ነገር ግን የተለያዩ አካላት ነገሩ እንዲፋጠን ግፊት እያደረጉ ነው።

የጀርመን የፌዴራል  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ካትጃ ኬል በታንዛኒያም ሆነ በጀርመን የተፈጠረው ነገር በበቂ ሁኔታ አልታወቀም ሲሉ ይናገራሉ።

«በታንዛኒያም ሆነ በጀርመን እነዚህ ክስተቶች በበቂ ሁኔታ የሚታወቁ አይደሉም። እና ያ አስፈላጊ ነው ምክንያቱም ከባድ ወንጀሎችም ተፈጽመዋል። እና ያንን በጋራ መስራቱ የወደፊቱን ጊዜ ይመለከታል፣ ከዚያም  የበለጠ ጠንካራ እና ጥብቅ ግንኙነቶችን መፍጠር ይቻላል። ስለዚህ ለመናገር ያህል  በአሁኑ ጊዜ ታንዛኒያን የሚጎዱ በጣም በጨለማ ውስጥ ግልፅ ያልወጡ እና እስካሁን ድረስ ያልተሰሩ ብዙ ነገሮች አሉ።»

በጀርመን የቅኝ ግዛት ዘመን በርካታ ህዝባዊ አመፆች በአሰቃቂ ሁኔታ ታፍነዋል። በተለይም በ1905-1907 በነበረው የማጂ-ማጂ አመፅ ዙሪያ የተፈፀሙ በደሎች እጅግ አስከፊ ነበሩ። በምስራቅ አፍሪካ እስከ 300,000 የሚደርሱ ሰዎች እንደተገደሉ የታሪክ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ። ስፍር ቁጥር የሌላቸው የራስ ቅሎች እና የሰው ቅሬተ አካሎችም  ወደ ጀርመን ተወሰደዋል።

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የበርሊን የፕሩሺያን የባህል ቅርስ ፋውንዴሽን የሰዎች አፅም  ወደ ታንዛኒያ እንዲመለስ ወይም በተገቢው ቦታ እንዲቀበር ይፈልጋሉ።ፕሬዚዳንቱ ኸርማን ፓርዚንገር እንደሚሉት  ፋውንዴሽኑ በ2011 ዓ/ም ከቻሪቴ የህክምና ታሪክ ሙዚየም በርካታ  አፅሞችን ተረክቧል።

«አሁን ያለው ሁኔታ ከአስር አመታት በፊት በትክክል ለመናገር በ2011  ከፍተኛ የሰዎች አፅም ስብስብ ከቻሪቲ የህክምና ታሪካዊ ሙዚየም ወደ ተረክበናል። ከዚያም የእነዚህን ሰዎች ትክክለኛነት መመርመር ጀመርን። ቅሪቶች፣ በዋናነት የራስ ቅሎች በ19ኛው እና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ከነበሩ የመንደር ነዋሪዎች መቃብር አውሮፓ በተለይም ጀርመን  የአንትሮፖሎጂ ጥናቶችን ለማካሄድ የተሰረቁ ናቸው።»  

ፓርዚንገር  እንደሚሉት ጉዳዩ  ጀርመን ውስጥ  አሁን ድረስ የሚያስቀጣ ከባድ ጥፋት እና ዝርፊያ ነው።ስለሆነም የተዘረፈው የአፅም መመለስ እንዳለበት ያምናሉ። ነገር ግን አስቀድሞ መረጃ መሰብሰብ ግዴታ በመሆኑ፤ በተቻለ መጠን  የቅሬት አካሉን አመጣጥ በትክክል ለመወሰን  በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት አንዳንድ መረጃዎች  መሰብሰቡን ገልፀዋል ።

በዚህም መሰረት ከሁለትና ሶስት አመት በፊት  የ1,200 የራስ ቅሎችን ክምችት ለሚመለከታቸው ሀገራት መረጃው የተላከ ሲሆን፤ 250 ያህሉ ከታንዛኒያ፣ 900 ከሩዋንዳ እና 35ቱ ከኬንያ መሆናቸውን ፓርዚንገር አመልክተዋል።

Deutschland l Namibia erhält 23 Artefakte von Deutschland zurück
ምስል Tobias Schwarz/AFP

ታንዛኒያ በምስራቅ አፍሪካ በጀርመን በቅኝ ግዛት ዘመን ለደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የጀርመን መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወስድ ግፊት እያደረገች ነው።

በጎርጎሪያኑ  2020 መጀመሪያ ላይ በበርሊን የታንዛኒያ አምባሳደር አብዳላህ ፖሲ የጀርመን መንግስት ለእነዚህ ወንጀሎች ካሳ እንዲከፍል ጠይቀዋል።

የታንዛኒያ የባህል፣ የጥበብ እና ስፖርት ሚኒስቴር ዋና  ጸሃፊ ሳይድ ኦትማን ያኩቡ እንዳሉት፣ የታንዛኒያ መንግስት ከጀርመን መንግስት ጋር በጋራ ለመስራት በዝግጅት ላይ ሲሆን ለዚሁ አላማ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሟል። «ኮሚቴው አሁንም እየሰራበት ነው። ልክ ሂደቱ  እና ከጀርመን ባልደረቦቻችን ለመጠየቅ የምንፈልገው ነገር ሲብራራ ተጨባጭ መልሶች ይኖራሉ። የካሳ ጥያቄ ከሚቀርቡት ነጥቦች አንዱ ነው።»

ታሪክ ምሁሩ ማቶይ፤ ካሳ ብቻውን በህብረተሰብ ውስጥ ሰላምና ፈውስ ሊያመጣ አይችልም ይላሉ። መንግስት፣ ፖለቲከኞች እና የተጎጂዎች ተወላጆች «ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት ወርቃማ ጊዜ»አድርገው ሊመለከቱት እንደማይገባም አስጠንቅቀዋል።

ይልቁንም አፍሪካውያን እና ታንዛኒያውያን በወቅቱ በነበረው የጀርመን  መንግሥት በምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያልፉም፤ታሪካቸውን በቁሳዊ ጥቅም ማካካሻ ሳይሆን ሊታደስ እና ሊከበር የሚገባውን እውነታ ሊያከብሩ ይገባል ብለዋል።

በመጭው መስከረም በሚካሄደው የበርሊን ሃምቦልት ፎረም አውደ ርዕይ  የታንዛኒያ የቅርስ ስብስብ ወሳኝ እይታ ይኖረዋል። የማጂ-ማጂ አመፅ መሳሪያዎችም በ2024 ለዕይታ ከቀረቡ በኋላ ወደ ታንዛኒያ እንደሚመለሱ ይጠበቃል።

ፀሀይ ጫኔ

እሸቴ በቀለ