1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬን ጦርነትና የጀርመን የፖሊሲ ለውጦች

ማክሰኞ፣ የካቲት 22 2014

ጀርመን በሩስያ የዩክሬን ወራራ ሰበብ ለመጀመሪያ ጊዜ የፖሊሲ ለውጥ አድርጋለች። ባለፈው እሁድ ጀርመን ለዩክሬን ፀረ ታንክ የጦር መሳሪያዎችንና ሚሳይሎችን እንደምትሰጥ አስታወቃለች። የአውሮጳ ኅብረትደግሞ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ መግዣና ለማጓጓዣ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብቷል።

https://p.dw.com/p/47psH
Berlin | Sondersitzung des Bundstags zur Krise in der Ukraine - Olaf Scholz
ምስል FABRIZIO BENSCH/REUTERS

በጀርመን የፖሊሲ ለውጦች ያስከተለው የዩክሬን ጦርነት

ሩስያ ዩክሬንን መውረሯ በምዕራቡ ዓለም ብዙ ለውጦችን አስከትሏል። ምዕራቡ ዓለም በሩስያ ላይ ከእስከዛሬዎቹ እጅግ ጠንከር ያሉ ማዕቀቦችን ጥሏል። ጀርመንም በጦርነቱ ሰበብ ዋና ዋና የፖሊሲ ለውጦችን አድርጋለች። የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን የፖሊሲ ለውጡን ምንነት ምክንያትና አንድምታውን ያስቃኘናል። ሳምንት ሊደፍን ሁለት ቀናት የቀሩት የሩስያ የዩክሬን ወረራ ያስከተለው ሰብዓዊውም ሆነ ቁሳዊ ጥፋት ተባብሶ ቀጥሏል። ግጭቱን ለማብረድ የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች ትናንት ቤላሩስ ድንበር ላይ ተገናኝተው ቢነጋገሩም የንግግሩ ዋናኛ ዓላማ የሆነው ተኩስ አቁም ላይ መድረስ አልቻሉም።ከዚያ ይልቅ ንግግሩን በሌላ ጊዜ ለመቀጠል በመስማማት ነው የተለያዩት።በጦርነቱ ከሞቱትና ከቆሰሉት በተጨማሪ ከ660 ሺህ በላይ ሰዎች ከዩክሬን ፖላንድና ሩማንያን ወደ መሳሰሉ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል ።  ሩስያ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የዩክሬን ድንበር በተለያየ አቅጣጫ ጥሳ ጥቂት የማይባሉ የዩክሬን ከተሞችን ከወረረችና ጦርነቱንም ካስፋፋች ወዲህ ምዕራባውያን በሩስያ ላይ ከእስከዛሬው የተለየ ጠጠር ያለ አቋም ይዘዋል።  ሩስያ ዩክሬንን መውረሯ አይቀርም ስትል አሜሪካን በተደጋጋሚ ስታስጠነቅቅ ሩስያ ያን ያህል ርቃ ትሄዳለች የሚል ስጋት እምብዛም ያልታየባቸው አውሮጳች  ከአምስት ቀናት በፊት ጦርነቱ እውን ሲሆን ከውግዘት አልፈው ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ዩክሬንን በጦር መሳሪያ ለመደገፍና አስፈላጊውንም እገዛ እንደሚያደርጉ አስታወቁ። የአውሮጳ ኅብረት ለዩክሬን የጦር መሣሪያ መግዣና ለማጓጓዣ የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገባ። ጀርመንም ፀረ ታንክ የጦር መሳሪያዎችንና ሚሳይሎችን እንደምትሰጥ አስታወቀች።ልዑል ዶክተር አስፋወሰን አስራተ በጀርመን የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ ፣ደራሲና የፖለቲካ ተንታኝ ናቸው።እርሳቸው እንደሚሉት ይህ እስከዛሬ ታይቶ የማይታወቅ አውሮጳውያን አንድነታቸውን ያሳዩበት እርምጃ ነው። 
። የጀርመን መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ባለፈው እሁድ የጀርመን ምክር ቤት ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ላይ ጀርመን ለዩክሬን ከምትሰጠው የጦር መሣሪያ  ድጋፍ በተጨማሪ  በ2022 በጀት ዓመት 100 ቢሊዮን ዩሮ 112.7 ቢሊዮን ዶላር ለአገራቸው ጦር ሠራዊት ለመመደብም ቃል ገብተዋል።የጀርመን የውጭና የመከላከያ ፖሊሲ ለውጥ ለብዙዎች ያልተጠበቀ ነው። የፖሊሲ ለውጡን ካልጠበቁት አንዱ ጀርመን የተማሩትና የሚሰሩት ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ የሕግ ባለሞያና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ናቸው። ጀርመን በዚህ ወቅት ላይ የፖሊሲ ለውጥ ልታደርግ የቻለችበትን ምክንያትና አንድምታውን አስረድተዋል። 
የጀርመን መራኄ መንግሥት በእሁዱ ልዩ ስብሰባ ጀርመን ከአጠቃላይ አገራዊ ምርቷ 2 በመቶውን ለመከላከያ እንደምትመድብ ለጀርመን ምክር ቤት  አስታውቀዋል ።ዶክተር አስፋወሰን ይህ የጀርመን መንግሥት እርምጃ ምክንያታዊና አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ዶክተር ለማ የሩስያ የዩክሬን ወረራ አንዱ ምክንያቱ ሩስያ እንደምትለው የየሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት ወደ ምስራቅ አውሮጳ መስፋፋት መሆኑን ያስታውሳሉ።ጉዳዩ ተካሮ ሩስያ ጢርነት ከከፈተች በኋላ  የሩስያ ፕሬዝዳንት ፑቲን በቅርቡ ለወታደራዊ የጦር ሹማምንቶቻቸው የኒዩክለልየር ጦር መሳሪያዎቻቸውን በተጠንቀቅ እንዲያዘጋጁ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ዶክተር ለማ ክፍለ ዓለሙ ይህን መሰል ችግር ውስጥ የወደቀው  አውሮጳ  ከአሜሪካን ጥገኝነት ነጻ ባለመሆንዋ ነው ይላሉ።  
ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮጳ ኅብረት በሩስያ ላይ ጠንካራ ማዕቀቦችን ጥለዋል።ሩስያም የአጸፋ እርምጃዎችን ወስዳለች። ። እርምጃዎቹም ህዝቡን ተጎጂ ማድረጋቸው የማይቀር መሆኑን ዶክተር አስፋወሰን ሊሆን የሚችለውን በመገመት ያስረዳሉ።ዶክተር ለማ ደግሞ ድንጋይ መወራወር ያሏቸውን ከነዚህ እርምጃዎች ይልቅ የሰላም አማራጮች ቢፈለጉ ይበጃል ብለዋል። 

Ukraine Kiew | Explosion am Fernsehturm
ምስል UKRAINIAN INTERIOR MINISTRY PRESS SERVICES/AFP
Polen Flüchtlinge in Przemysl
ምስል Arafatul Islam/DW

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ