በጀርመን የኢኦተቤ/ክርስቲያን ምሥረታ 40ኛ ዓመት
ማክሰኞ፣ ሰኔ 20 2015ምዕራብ ጀርመን የሚገኘው ኮሎኝ ሎንገሪሽ ክፍለ ከተማ ፣እንደ አብዛኛዎቹ ከከተማ ማዕከል ወጣ ያሉ የጀርመን አካባቢዎች ብዙም የሰዎች እንቅስቃሴ የሚታይበት አይደለም።እሁድ እሁድ ግን ፣ከአዘቦቱ ቀናት በተለየ በዚህች ክፍለ ከተማ በሚገኘው የኮሎኝ-ቦን ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በሚሰጠው አገልግሎት ምክንያት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በሎንገሪሽ ሲመላለሱ ማየት የተለመደ ነው። በዓመታዊ የንግሥ በዓላት ጊዜ ደግሞ ከሌሎች የጀርመንና የተለያዩ የአውሮጳ ሀገራት ከተሞች የሚመጡ ምዕመናን ተደምረው አካባቢውን ያደምቁታል። ዘንድሮ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ምስረታ አርባኛ ዓመትና የሰኔ ሚካኤል የንግስ በዓል በተከበረበት በዚሁ ቦታ ሰኔ 10 እና ሰኔ 11 ቀን 2015 ዓም የታየው ደግሞ ከእስከዛሬው እጅግ የተለየ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅ እና የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አብርሃምና የጀርመንና አካባቢው እና የምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዲዮናስዮስ በእንግድነት በተገኙበት በዚሁ በዓል ላይ ከአንድ ሺህ በላይ እንደሚሆን የተገመተ ምዕመን አካባቢውን አጥለቅልቆት ነበር ። ሎንገሪሽ በሚከበር በዓል ላይ እንደ ዛሬ አስር ቀኑ በርካታ ምዕመን ሲገኝ የዘንድሮው የመጀመሪያው ነው።አብዛኛዎቹ ታዳሚዎች ኢትዮጵያ ያሉ ያህል እንደተሰማቸው ነበር ለዶቼቬለ የገለጹት።።
በዓሉ ቅዳሜ ሰኔ 10 ቀን 2015 ዓም ከሰዓት በኋላ በፀሎት ከተከፈተ በኋላ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን መስራችና የኮሎኝ-ቦን ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የእንኳን ደኅና መጣችሁ ንግግር አድርገው በብጹእ አቡነ አብርሃም መንፈሳዊ ትምሕርት ተሰጥቷል። የቤተክርስቲያኗን የ40 ዓመት ጉዞ የሚያሳይ የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይም በብጹእ አቡነ አብርሃምና በብጹእ አቡነ ድዮንያሶስ ተመርቆ ተከፍቷል። የበዓሉ አከባበር ለሊቱን በማኅሌትና በዝማሬ ቀጥሎ በማግስቱ ሰኔ 11 ቀን 2015 ዓም ከስርዓተ ቅዳሴ በኋላ ታቦተ ሕጉ በሊቃነ ጳጳሳቱ ፣በተለያዩ የጀርመን ከተሞች በሚገኙ አድባራት አስተዳዳሪዎችና ካህናት፣ጥሪ በተደረገላቸው የጀርመን አብያተ ክርስቲያን ተጠሪዎችና እንግዶች እንዲሁም በምዕመናን ታጆቦ በሎንገሪሽ ጎዳናዎች ዑደት ሲያደርግ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት እና ምዕመናኑ በዝማሬ አድምቀውታል።
ታቦቱ ባረፈበት በቤተ ክርስቲያኑ አጠገብ በሚገኘው ሰፊ መናፈሻ በተከበረው በዓል ላይ ቡራኬና ቃለ ምእዳን የሰጡት ብጹአ አቡነ አብርሃም ከብጹእ አቡነ ማቲያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ የተላከ የእንኳን ደስያላችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ በጀርመን በዓሉ በነጻነት መከበሩን ትምሕርት ሰጭ ሲሉ አወድሰዋል።
አምባሳደር ኃይላይ ብርሀነ ተሰማ በጀርመን የኢትዬጰያ ኤምባሲ ምክትል ሚስዬን መሪና የኤኮኖሚ ዘርፍ ሀላፊ ፣ የጀርመን አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮችና የኮሎኝ ከተማ ከንቲባ በበዓሉ ላይ የመልካም ምኞት መግለጫዎቻቸውን አሰምተዋል።ቤተ ክርስቲያኗን በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሲሉ ያወደሷት አምባሳደር ኃይላይ ለኅብረተሰቡ ለሰጠቻቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶችም አመስግነዋታል።
የኮሎኝ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ራልፍ ሃይነን በበኩላቸው በህዝቡ ብዛት መደነቃቸውን ገልጸዋል።እለቱ ለታሳሚዎች ብቻ ሳይሆን ለኮሎኝ ጭምር የተለየ ነው ብለዋል።
«ዛሬ በጀርመንና በአውሮጳ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለኮሎኝም ልዩ ቀን ነው። ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ይካሄድ በነበረው ጦርነት ምክንያት ጀርመን በተለይም ኮሎኝ የመጡ ብዙዎች እዚህ ሀገር አግኝተዋል። ዛሬ እዚህ በተገኘው ከአንድ ሺህ በላይ በሚሆን ህዝብ ተደንቄያለሁ። ኢትዮጵያ በራይን አካባቢ ያላት እውቅና በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውበት ይጠናከራል።»
በጀርመን ብሎም በአውሮጳ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን መስራች እና የኮሎኝ ቦን ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ካኅናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት በጀርመን ብሎም በአውሮጳ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱ ተስፋፍቷል። ዛሬ በጀርመን ወደ 25 በአውሮጳ ደግሞ ወደ 60 አብያተ ክርስቲያን ይገኛሉ ። በተውሶ ይገለገሉ ከነበሩ አብያተ ክርስቲያን መካከል ዛሬ የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን የገዙም ጥቂት አይደሉም።
በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ሲወሳ ቤተክርስቲያኗ የተመሰረተችበት የደቡብ ምዕራብ ጀርመንዋ ከተማ ሀይድልበርግ አብራ ትነሳለች ከዛሬ 40 በፊት ለዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት ጀርመን የመጡት የያኔው ካኅን የአሁኑ ሊቀ ካኅናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀና ሌሎች ጓደኞቻቸው ይማሩበት በነበረው በሀይድልበርግ ከተማ ነው የቤተ ክርስቲያኗ መሰረት የተጣለው። ወይዘሮ ንጋት ከተማ የቀድሞ የዶቼቬለ ባልደረባና የሊቀ ካኅናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ ባለቤት ከመስራቾች አንዷ ናቸው።እርሳቸው እንደሚያስታውሱት እጅግ በጣም ጥቂት ሆነው ነው ቤተ ክርስቲያኗን የመሰረቱት።
ያኔ ጥቂት የነበረው የምዕመናን ቁጥር አሁን እጅግ አድጎ የሚሰጠውም አገልግሎት ከጠበቁት በላይ ሰፍቶ ማየታቸው ለወይዘሮ ንጋት ተዐምር ነው ። ዶቼቬለ ያነጋገራቸው በበዓሉ ላይ የታደሙ ምዕመናን መጽናኛና ናፍቆት ማስረሻ የሚሏትን በውጭ ሀገር የምትገኘውን ቤተ ክርስቲያን የሀገራቸው ምትክ አድርገው ነው የሚቆጥሯት። በውጭ የሚገኝ ቤተ ክርስቲያን በተለያየ የዓለምክፍል ለሚገኝ ምዕመን ምን ትርጉም አለው ?ከጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የ40 ዓመት ጉዞ ጋር ሳምንት በስፋት እንመለስበታለን።
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ