በጀርመን ኮሮናን ለመካለክ የተደነገገው ሕግ መላላትና አዲሱ "XE" ዝርያ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 27 2014የኮሮና ተሕዋሲ ባህሪ ተለዋዋጭ መሆን ሥርጭቱን በመከላከሉ ሂደት ላይ የራሱ የሆነ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩን የጤና ባለሙያዎች ደጋግመው ሲገልጹ ቆይተዋል። ተሕዋሲው የሚያስከትለውን ውስብስብ ጉዳት መከላከልና መቀነስ የሚቻልበት መከላከያ ክትባት ተመርቶ ጥቅም ላይ ቢውልም ዛሬም ድረስ በተለያየ ልውጥ ባህሪ እያገረሸ የሥርጭት አድማሱን ማስፋቱ ተስፋውን ሌላ ስጋት ውስጥ ከቶታል። ይህ ተሕዋሲ በጎርጎሪዮሳዊው አቆጣጠር በታኅሣስ ወር 2019 ዓ.ም ቻይና ውስጥ በሁቤዋ ግዛት ውሃን ከተማ መገኘቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ዓለምን በፍጥነት ያዳረሰ ሲሆን ከዛም አልፋ የሚባለው የቫይረሱ አዲስ ዝርያ በእንግሊዝ፣ ቤታ በደቡብ አፍሪቃ፣ ጋማ በብራዚል፣ ዴልታ በህንድ በተለያየ ዝርያና ባህሪ እየተከሰተ ሳይንቲስቶች ተሕዋሲውን በፍጥነት ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ከፍተኛ የምርምር ጥረት በእጅጉ ሲፈትን ቆይቷል። የዚህ ተሕዋሲ ሌላው አደገኛና በፍጥነት የመዛመት ባህሪ አለው የተባለ ዝርያ ኦሚክሮንም ባለፈው በኅዳር ወር ላይ በምዕራብ አውሮጳ እና ደቡብ አፍሪቃ ተከስቶ በሃገራቱ ላይ ጠንካራ የጉዞ ማዕቀብ እስከመጣል በማድረሱ ለውዝግብ መንስኤ ሆኗል። ከሦስት ቀናት በፊት ደግሞ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በእንግሊዝ ሀገር የቤታ 1 እና 2 ኦሚክሮን ቫይረሶች ቅይጥ የሆነ ከቀደሙት አስር እጥፍ በፍጥነት የመሰራጨት አቅም ያለው ሳይንቲስቶች "ኤክስ.ኢ-XE" የሚል ስያሜ የሰጡት አዲስ የኮረና ቅይጥ ተሕዋሲ መገኘቱን ይፋ አድርጓል።
ኮረና ተሐዋሲ እስካሁን በዓለም ዙሪያ ከ 491 ሚልዮን በላይ ሕዝብ ያጠቃ ሲሆን ከ 6.1 ሚልዮን የሚልቁ ሰዎችንም ሕይወት ቀጥፏል። በጀርመንም የተያዙት ቁጥር ወደ 22 ሚልዮን ሊጠጋ የተቃረበ ሲሆን 131 ሺህ አካባቢ ሰዎችም መሞታቸውን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። ባለፈው ዓመት ታኅሣስ ወር ከ 100ሺህ ሰዎች መካከል 340 አካባቢ ሰዎች የተያዙ ሲሆን የሮበርት ኮህ የጤናና ምርምር ተቋም እንዳለው ከጥር ወር ጀምሮ ግን ታይቶ በማይታውቅ ሁኔታ ቁጥሩ በቀን ከ 300 ሺህ በላይ ማሻቀቡ የፌደራል ፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዶ በኮረና ወረርሽኝ መከላከል ደንብ ላይ በተለይም ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች፣ በምግብ ቤቶችና የመዝናኛ ሥፍራዎች እንዲሁም በጤና፣ በገበያና በስፖርት እንቅስቃሴ ማከናወኛ ማዕከላትና በሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎቶችና በመሳሰሉት መከተብን፣ ከቫይረሱ ማገገምንና ዕለታዊ የናሙና ምርመራ ውጤት ማሳየትን እንደ ግዴታ የሚያጸና ደንብ ገቢራዊ አድርጎ ቆይቷል። በክትባት ግዴታ ላይም በአንድ በኩል «ክትባት ግዴታ መሆን አለበት» በሚሉና ፤ «ክትባት አስገዳጅ መሆኑ የጀርመን ሕገ መንግሥት ስለ ግለሰብ መብትና አካልን ስለመጠበቅ መብት የሰጠውን ነጻነት የሚጋፋ ነው» የሚል ተቃውሞ ባንጸባረቁ ወገኖች መካከል ክርክር ሲካሄድ ቢቆይም የጀርመን ፌደራል የጤና ሚኒስትሩ ካርል ላውተርባህና ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ «ኮሮናን ለመከላከል ክትባት መተኪያ የሌለው ብቸኛው አማራጭና አስፈላጊ ነው» ሲሉ ለፓርላማው በአጽንዖት አስገንዝበዋል። ምንም እንኳ የተከተቡትም ቢሆኑ ዳግም በተሕዋሲው የሚጠቁበት አጋጣሚ ሊኖር ቢችልም ቀደም ካሉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸ ግን ሆስፒታል የሚገቡትና በዚህ ምክንያት የሚሞቱት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ በመሄዱ ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ በጀርመን አብዛኛዎቹ የኮረና አስገዳጅ ህጎች መነሳታቸውን መንግሥት ይፋ አድርጓል። ህዝብ በሚሰበሰብባቸውና ረጅም አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ውስጥ ካልሆነ በስተቀር ለምሳሌ ማስክ ማድረግና የክትባት ማረጋገጫዎችን መጠየቅ ግዴታ መሆናቸው እንዳበቃ ነው የተገለጸው። ታዲያ የሕጉ መነሳትና መሻሻል ያስደሰታቸውም ያሳሰባቸውም እንዳሉ ለዶይቼ ቨለ ገለጸዋል።
ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ማዕቀፉ ያድምጡ
እንዳልካቸው ፈቃደ
ሸዋዬ ለገሠ