በጀርመን አይሁዶች ላይ የተፈፀመው ግፍ 75 ተኛ ዓመት መታሰቢያ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 3 2006
ህዳር ዘጠኝ ሌሊት በመቶዎች የሚቆጠሩ የአይሁዳውያን ሙክራቦችና የፀሎት ቤቶች ተዘረፈዋል በእሳት ጋይተው እንዲወድሙም ተደርጓል ። በየመንገዱ ይሁዲዎችን የሚያዋርዱ ድርጊቶች ተፈፅመዋል ። አይሁድ በመሆናቸው ብቻ የተደበደቡና የታሰሩ በአንዳንድ አጋጣሚዎችም የተገደሉት ቁጥር ቀላል የሚባል አልነበረም ። ህዳር ዘጠኝ ለህዳር 10 አጥቢያ የደረሰው የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አልነበረም ። ህዳር 10 ፣ 30ሺህ ወንድ ይሁዲዎች ፣ዳኻው ዛክሰንሃውዘን እና ቡኽንቫልድ በተባሉት ከተሞች ወደ ሚገኙ የማጎሪያ ካምፖች ተወሰዱ ። ከመካከላቸው አንዱ የሚሻኤል ብሉመንታል አባት ነበሩ ።
« በጠዋት ሁለት ፖሊሶች አባቴን ከቤታችን ሲወስዱት እናቴ የተናገረችው እስካሁን ድረስ ጆሮዬ ላይ አለ ። ምንድን ነው የሆነው ? ምን ልታደርጉት ነው ? ምን አድርጓል ? የት ነው የምትወስዱት ? ትል ነበር እናቴ ።አባቴን ከማጋዛቸው በፊት መጀመሪያ ወደ አንድ ማረፊያ ቤት የወሰዱት ይመስለኛል ። ያኔ የ 12 ዓመት ልጅ ብሆንም የእናቴ ፍርሃትና የእዋቂዎቹ ጭንቀት ለኔም ይሰማኝ ነበር ።»
ከ75 ዓመት በኋላ ዛሬም ብሉመንታል ያን እለት በፍፁም አይረሱትም ። ካደጉበት ከበርሊኑ ሻርሎትንበርግ ሰፈር የወጣትነት ትዝታዎቻቸው በተለይ አባታቸው በፖሊስ ተይዘው ሲወሰዱ የፈጠረባቸው ስሜት ምን ጊዜም የሚረሳ አይደለም ።
ብሉመንታል ምንም እንኳን ያኔ እናታቸው ከቤት እንዳይወጡ ቢከለክሉዋቸውም ተደብቀው የሆነውን ማየታቸው አልቀረም ። በፋሳነን መንገድ ላይ የተሰባበሩ መስኮቶችን የሚጬሱ ሙክራቦችን አይተዋል ። አባታቸው በሺህዎች ከሚቆጠሩ ሌሎች ይሁዲዎች ጋር ቡኽንቫልድ ወደ ሚገኘው ማጎሪያ ሰፈር ነበር የተወሰዱት ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላም ተለቀው ወደ ቤታቸው ተመለሱ ። ሆኖም የሚሻኤል ብሉመንታል ቤተሰብ ያኔ ህይወታቸውን ለማትረፍ ጀርመንን ለቆ ከመውጣት በስተቀር ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም ። በወቅቱ ወደ ሌሎች ሃገራት ለመሄድ ቪዛ ማግኘቱ አስቸጋሪ ስለነበረ በ1938 ተሳክቶላቸው ውጣ ውረድ ወደ ሌለበት ወደ ሻንጋይ ተሰደዱ ። ሻንጋይ ያኔ ያለ ቪዛ ሊገቡ የሚችሉባት ብቸኛዋ ሃገር ነበረች ። ትውልደ ጀርመናዊው ብሉመንታል በ1970 ዎቹ የአሜሪካን የገንዘብ ሚኒስትር ነበሩ ። አሁን ደግሞ ከ75 ዓመታት በኋላ ወደ በርሊን ተመልሰው የበርሊኑ የአይሁዶች መታሰቢያ ቤተ መዘክር ሃላፊ ሆነው በመስራት ላይ ናቸው ። በአዶልፍ ሂትለር ይመራ የነበረው የናዚዎች መንግሥት ሥልጣን ከያዘበት ከጎርጎሮሳውያኑ 1933 ዓም ጀምሮ በጀርመን በሰዎች ላይ የአካል ጥቃት ማድረስና ሰዎችን ማሸማቀቅ የእለት ተእለት ክስተት ነበር ። በተለይ ይሁዲዎች በዚህ ጊዜ መሥራት አይፈቀድላቸውም ፣ በነፃነት መንቀሳቀስም አይችሉም ነበር ። ንብረታቸውም ይወረስ ነበር ። በዚህ ዓይነት ሁኔታ በደል ሲፈፀምባቸው የቆዩትን ይሁዲዎች እጎአ ህዳር ሰባት ፣ 1938 ሂትለር የሚያጠቃበት አጋጣሚ ተመቻቸለት ። ሄርሽል ግሪንስትስፓን የተባለ ወጣት ይሁዲ በዚያን እለት ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ አንድ የጀርመን ዲፕሎማት ላይ ከተኮሰ ከሁለት ቀናት በኋላ ሂትለር የአይሁዶችን ቤተ እምነትና ሱቆች እንዲሁም መኖሪያዎቻቸው እንዲቃጠሉ ትዕዛዝ አስተላለፈ ። የታሪክ ምሁሩ ራፋኤል ግሮስ፣
« በህዳር 1938 ሁሉም እያየው በፕሬሱ ፊትና ህዝቡም እያወቀው የሆነው ፣ በታሪክ ተመዝግቦ መያዝ ያለበት ክሰተት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል ። »
ይህ ሁሉ የሆነው የጀርመን ህዝብ እያየ ዓለምም እየተመለከተ ነበር ። ያኔ ጀርመን ከነበሩ ዲፕሎማቶች አንዳንዶቹ በወቅቱ ያዩትን ዘግበው ነበር ። ከመካከላቸው የብራዚሉ ዲፕሎማት ቴሚስቶክለስ ዳ ግራሳ አራንሃ ለሃገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባቀረቡት ዘገባ «ወጣት ወሮበሎች ከእስራኤላውያኑ የእምነት ቤቶች የዘረፏቸውን ንዋየ ቅድሳት ለህዝቡ ሲያሳዩና ከመካከላቸውም በሂብሩ ቋንቋ የተፃፈውን የመፀሀፍ ቅዱስ ገጾች እየቀደዱ ለማስታወሻ ሲያከፋፍሉ መመልከታቸውን በወቅቱም ፖሊስም እሰየው እያለ ያበረታታቸው እንደነበር ፅፈዋል ።
ሌሎች የውጭ ዲፕሎማቶችም ያዩትን ወደ ሃገራቸው ያስተላልፉ ነበር ። ላይፕዚሽ ከተማ የነበሩት የፖላንድ ቆንስላ ሃላፊ የፖላንድ ዜግነት ባላቸው በሽፔርሊግ ቤተሰቦች ላይ የተፈፀመውን ግፍ «የሽፔርሊንግ ባለቤት እርቃናቸውን እንዲቀሩ ካደረጓቸው በኋላ ሊደፍሯቸው ሞክረዋል » በማለት ፅፈው ነበር ፣
የላትቪያው አምባሳደር ደግሞ ኩርፉርስተንዳም የተባለው መንገድ የጦር አውድማ መስሎ ነበር ሲሉ ዘግበዋል።
አምባሳደሮቹ የሆነውን ከማሳወቅ ውጭ ለመንግስታቶቻቸው ምን መደረግ እንደሚገባው ያሉት ነገር አልነበረም ። የይሁዲዎች ማዕከል ሃላፊ ሄርማን ዚሞን በወቅቱ የ20 ሃገራት ዲፕሎማቶች ያስተላለፏቸውን መልዕክቶች ለዐውደ ርዕይ አሰባስበዋል ። በርሳቸው አስተያየት የዲፕሎማቶቹ መልዕክቶች የፈየዱት ነገር የለም ።
« በተለያ ኃያላኑ መጋፈጡን አልፈለጉም ። ከጀርመን በርካታ ስደተኞች እንዲመጡባቸውም አልፈለጉም ። ቁጥብ ሆነው ነበር ። ምናልባትም በሆነ መንገድ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ይደረሳል በሚል ያልተጨበጠ ተስፋ ዝም ብለው ይጠብቁ ነበር ። ዘገባቸው ያስተጋባውም መልዕክት ያን ያህል አልነበረም ።»
የታሪክ ምሁሩ ራፋኤል ግሮስ እንዳሉት በወቅቱ አምባሳደሯን ከጀርመን ያስወጣችው ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ነበረች ። ብሪታኒያ ደግሞ ብቻዋን ስደተኞችን ትረዳ ነበር ።
« ብሪታኒያ ህፃናትን ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነች አስታውቃ ነበር ። በዚሁ መሠረት በአይሁዳውያን ላይ ከደረሰው የህዳር 1938ቱ ጥቃት በኋላ 10 ሺህ ህፃናት ወዲያውኑ ወደ ብሪታንያ እንዲወሰዱ ተደርጓል ። ይህም እንደ አዲስ እርምጃ ነው የተቆጠረው ። በዚህ ረገድ የተወሰኑ ሃገራት መጠነኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ብዙዎች በጣም አነስተኛ ቁጥብ እርምጃ ነበር የወሰዱት ። »
ዚሞንና ግሮስ እንደሚሉት ናዚዎች ይሁዲዎችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ማሰባቸውን በዛ ወቅት ለመገመት ያዳግት ነበር ። የኢጣልያ ኤምባሲ እንደፃፈው 500 ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን በአንድ ቀን ውስጥ ፊታቸውን ወደ ግድግዳ አዙሮ መረሸን የራሳቸውን ህይወት በገዛ እጃችሁ አጥፉ ብሎ መፍረድ ወይም በትልቅ ማጎሪያ ቦታ ውስጥ ቆልፎ ማስቀመጥ ለመገመት የሚከብድ ነው ። የሚሻኤል ብሉመንታል ቤተሰብ በ1938 ተሳክቶላቸው ወደ ሻንጋይ ተሰደዱ ። ሻንጋይ ያኔ ያለ ቪዛ ሊገቡ የሚችሉባት ብቸኛዋ ሃገር ነበረች ። የታሪክ ምሁር ራፋኤል ግሮስ ከዛን ጊዜው ግፍና ግፉ ካስከተለው ስደት ዛሬ ብዙ መማር ይቻላል ይላሉ።
« ከዚህ ምን መማር ይቻላል ብለው የሚጠይቁ አሉ ። እያንዳንዱ ሰው ራሱን በተሰደዱት ሰዎች ቦታ አድርጎ ቢመለከት ጥሩ ነው ። በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው ። በሸንገን ስምምነት ፈራሚ ሃገራት አካባቢ ቁጥራቸው እስከ 20 ሺህ የሚደርስ ስደተኞች አብዛኛዎቹ በሜዴትራንያን ባህር ውስጥ ሰጥመው አልቀዋል ። የእነዚህን ስደተኞች ፍርሃት ብቻ ሳይሆን ምን እንደሚሰማቸው ራሳችንን በነርሱ ቦታ አድርገን ማየት ይኖርብናል ። »
የዛሬ 75 ዓመቱ ፀረ ሴማዊነት ዛሬም በጀርመን ብሎም በአውሮፓ ሙሉ በሙሉ አልተወገደም ። ጀርመን የሚኖሩ ይሁዲዎች አሁንም በልዩ ልዩ መልኩ የሚፈፀም ጥቃት ሰለባ መሆናቸው አልቀረም ።የመታሰቢያውን እለት ምክንያት በማድረግ የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጀርመኖች በሙሉ ፀረ ሴማዊነትን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል ። ፒንቻስ ጎልድሽሚት በአውሮፓ የይሁዲ እምነት የሃይማኖት አባቶች ለህዳር ዘጠኙ ግፍ መታሰቢያ ያዘጋጁት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ስጋቱ አሁንም መኖሩን ችግሩን ለማስወገድም የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ ።
«ፀረ ሴማዊነት መልኩን የሚቀይርና የሚለዋወጥ ቫይረስ ነው ። አውሮፓ ሃይማኖታዊ በነበረችበት በመካከለኛው ዘመን ፀረ ፅዮናዊነት ሃያማኖታዊ ነበር ። አውሮፓ ከሃይማኖት ራሷን ባገለለችበት ወቅት ደግሞ ፀረ ሴማዊነት እንዲሁ ራሱን ከሃይማኖት ውጭ ያደረገና ዘረኛም ሆኗል ። የእስራኤል መንግሥት ከተመሰረተ በኋላ ደግሞ ፀረ ሴማዊነት ከተለመደው ፀረ ሴማዊነት ተለይቷል ። አሁን የወንዶች ግርዘት ይቅር አይቅር በሚል በተነሳው ክርክር ላይ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልም እንዳሉት ሁሉም ባይሆን አብዛኛዎቹ አስተያየቶች ዘረኛና ፀረ ሴማዊነትንየሚያስተጋቡ ነበሩ ። እናም ይህ አዲሱ የፀረ ሴማዊነት ገፅታ እንዳይሆን እንሰጋለን ። »
በጎልድሽሚት አስተያየት በተለያዩ ሃገራት እንዲሁም በአውሮፓ ለሺህ ዓመታት የዘለቁ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ልምዶችን የመሸፈን ወይም የማጥፋት ሙከራዎች እየተደረጉ ነው ። ከዓለማችን ህዝብ በአንድ ሶስተኛው ተግባራዊ የሚሆነውን የወንዶች ግርዘት ለማስቀረት የሚደረገው ጥረት አንዱ የዚህ መገለጫ ነው ። ይህ ግን ፋይዳ የለውም
« የወንዶች ግርዘት ለይሁዲዎች መሰረታዊ ጉዳይ ነው ።ይሁዲ ለመሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በዚህ ሂደት ውስጥ ማለፍ አለበት ።እንደምታውቀው የቻኑካ በዓል ከፊታችን ይጠብቀናል ። ከገና በዓል ጋር በተመሳሳይ ወቅት ላይ የሚውለው ይህ በዓል የሚከበረው በግሪክ ወረራ ወቅት ግርዘት መከልከሉን በመቃወም በተካሄደው አብዮት ምክንያት ነው ። በአንጀሊካውያንና በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የአዲስ ዓመት የቀድሞው መጠሪያ «የክርስቶስ የግርዘት በዓል» ነበር ። አውሮፓ በሃይማኖት ጣልቃ አትገባም ። አውሮፓ ከመካከለኛው ምስራቅና ከሰሜን አፍሪቃ በሚመጡ ስደተኞች ምክንያት ችግር ውስጥ እንዳለች ይታወቃል ። ሆኖም አውሮፓን ብዙ ዝርያዎች በአንድ ላይ የሚኖሩባት ክፍለ ዓለም ለማድረግ የተጀመረው መንገድ የሚቃናው የሃይማኖት ነፃነትን በመገደብ አይደለም ።»
በጎልድሽሚት እምነት አሁን በርግጠኝነት ያለፈው ጊዜ እንዲደገም የሚሞክሩ ጨለምተኛ ኃይሎች አይኖሩም ብሎ በርግጠኝነት መናገር አይቻልም ። ህሊና ያለው ጀርመናዊም ሆነ እያንዳንዱ የአውሮፓ ዜጋ በማናቸውም የዘረኝነትና የፀረ ሴማዊነት መገለጫዎች ላይ ተቃውሞውን ከፍ አድርጎ ማሰማት ይኖርበታል ። ይህ ደግሞ የተለየውን የዘረኝነት ዓይነት ማለትም በእስልምና ላይ የሚሰነዘረውን ጥላቻም ይጨምራል ፤ በርሳቸው አስተያየት ይህ የተባበረችውን አውሮፓን አደጋ ላይ የሚጥል ዓይነት አለመቻቻል ማለት ነው ።
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ