በጀርመን ተፈላጊ የሆኑ የውጭ ባለሞያዎች
ማክሰኞ፣ መጋቢት 5 2015በልዩ ልዩ የሞያ መስኮች በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ያለባት ጀርመን በየዓመቱ ከውጭ የሚገቡ 400 ሺህ ሠራተኞችያስፈልጓታል። እነዚህን ባለሞያዎች ለመሳብ ጀርመን የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገች ቢሆንም እንደታሰበው የሚፈለገው የውጭ ሠራተኛ ኃይል አልተገኘም ይላል የዶቼቬለዋ የዛቢነ ኪንካርትዝ ዘገባ።
ሮማንያዊቷ ማራ ጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ውስጥ ጥሩ ክፍያ በምታገኝበት በማስታወቂያ ድርጅት ስራ ስታገኝ ህልምዋ የተሳካ ያህል ነበር የተሰማት።ከፍተኛ ትምህርትዋን ብሪታንያ የተከታተለችውና ለጥቂት ዓመታትም ሮማንያ የሰራችው የ30 ዓመቷ ማራ የስራ እድሉ ሲሳካላት ለዓመታት ስትመኘው የቆየችው እውን ሆነልኝ አለች።
«ጀርመን ጥሩ ስም አላት።ደኅንነትዋ የተጠበቀ፣ጥሩ የስራ ሁኔታ እና የተሻለ የኑሮ ደረጃም ያለባት ሀገር ናት።የጀርመን ምጣኔ ሀብት በአውሮጳ አንቀሳቃሽ ኃይልነት ነው የሚታወቀው።እኔ የመጣሁት ከምሥራቅ አውሮጳ ነው፣ የተማርኩት ደግሞ ብሪታንያ ፤በዚህም ብዙ ባህሎችን የማወቅ እድል አግኝቻለሁ።ጀርመን በተለይም አሁን የምኖርባት በርሊን ምሥራቅና ምዕራብ አውሮጳ ተቀላቅለው የሚኖሩባት ከተማ ናት።ለዚህም ነው እዚህ ለመኖር የወሰንኩት።»
ማራ ጀርመን እንደመጣችም አዲስ ሕይወት እየጀመርኩ ነው አለች ለራስዋ።ለካስ በምዕራብ አውሮጳ መኖር ይቻላል ብላም አሰበች ። ጡረታ እስክትወጣ ድረስ ጀርመን እቆያለሁ አለች። መጀመሪያ ላይ የጀርመን ቢሮክራሲ ትንሽ አንዳንገላታት ታስታውሳለች።
«በኑ በኩል መጀመሪያ ላይ የገጠመኝ ከቢሮክራሲ ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው። ለነዋሪነት ምዝገባና ለሌሎችም ጉዳዮች የተለያዩ ቀጠሮዎች መያዝ ነበረብኝ ።ሌላው ፈተና ፣የባንክ ሂሳብ መክፈት ነበር።ይሄ ሁለት ሳምንት ፈጅቷል። ሌላው ችግር ደግሞ አዲስ ቤት ለመከራየት የሚያስፈልገው ከባንኮች ከኢንተርኔት አቅራቢዎችና ከመሳሰሉ ድርጅቶች የግለሰቡ የእዳ ታሪክ ተጣርቶ የሚቀርብበት ማስረጃ ነበር። ከሁሉ ከሁሉ ግን መኖሪያ ቤት ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባዱ ፈተና ነበር ለኔ»
ከአንድ ዓመት በኋላ ግን ማራ መጀመሪያ የነበራት ስሜት አልዘለቀም። እየቆየ ሲሄድ ቅር ትሰኝ ጀመር። ጀርመን ውስጥ ከኅብረተሰቡ ጋር የሚያቀራርብ ሁኔታ ስላልተፈጠረላት ብቸኝነት ይሰማታል። ይህ የሆነው ደግሞ በቋንቋ እጥረት ምክንያት ነው ።ሮማንያ ዋና ከተማ ቡካሬስት እያለች ጀርመንኛ ተምራ ነበር። ይሁንና ጠለቅ ያለ እውቀት ስለሌላት እንደምትፈልገው መግባባት አልቻለችም። በተቀጠረችበት ድርጅት ውስጥ የምትሰራው በእንግሊዘኛ ቋንቋ በመሆኑ ጀርመንኛ የምትለማመደብት አጋጣሚ አልተፈጠረላትም። በዚህ ላይ ከኮሮና በኋላ ስራ ከቤት በመሆኑ የስራ ባልደረቦቿን በኮምፕዩተር መስኮት እንጂ በአካል አታገኛቸውም።ይህ ደግሞ በእጅጉ ይረብሸኛል ትላለች። በተለይ በሳምንቱ መጨረሻ የት እንደምሄድና ከነማን ጋር መገናኘት እንዳለብኝ አላውቅም ትላለች ማራ ።ማራ እንደምትለው ጀርመን ውስጥ በተለይ ከውጭ ሀገራት ለሚመጡ ሠራተኞች ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲዋሀዱ የሚረዱ መርሃ ግብሮች ያስፈልጋሉ።
«ጀርመን በገንዘብ ረገድ የምትስብ ሀገር ናት።ይሁንና ጥሩ ደሞዝ ብቻ ከኅብረተሰቡ ጋር በተሳካ ሁኔታ ተዋኅዶ ለመኖር በቂ አይደለም።ብዙዎች ከኅብረተሰቡ ጋር በሚያቀራርቧቸው አካባቢዎች መኖር ይመርጣሉ።የውጭ ዜጋ ሀገሪቷን እንደ ቤቱ እንዲቆጥር ጀርመን ከውጭ ሀገራት ለሚመጡ ሠራተኞች ከባህል ተቋማት ጋር በመተባበር የሚዘጋጁ ከኅብረተሰቡ ጋር የሚያዋኅዱ መርሃ ግብሮች ያስፈልጓታል ብዬ አምናለሁ።የውጭ ዜጎች በጀርመን ተረጋግተው ለመኖር የስራ ቦታቸው ወሳኝ ነው።ከሰዎች ጋር በቀላሉ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችል ቦታ ይመስለኛል።በዙም ወይም በፌስቡክ ከመነጋገር ይልቅ ፊት ለፊት መገናኘት በጣም አስፈላጊ ነው።»
ማራ እንደምትለው የውጭ ዜጎች ጉዳያቸውን ለማስፈፀም ወደ ጀርመን መስሪያ ቤቶች ሲሄዱ ጀርመንኛ መናገር ግዴታ መሆኑ አንዱ አስቸጋሪ ሁኔታ ነው።ይህ ችግር የገጠማት ማራ ብቻ አይደለችም። የትዩቢንገኑ የኤኮኖሚ ጥናት ተቋም ፣ለፌደራል ጀርመን የሥራና ሠራተኛ ጉዳዮች መስሪያ ቤት በተካሄደ ጥናት፣ ለ1900 የውጭ ሠራተኞች በፌስ ቡክ በተካሄደ መጠይቅ በሀገሪቱ ቀላል የማይባል የማኅበራዊ ውኅደት ክፍተት እንዳለ ተጠቁሟል። በመጠይቁ ከተካፈሉት ከአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ውጭ ከመጡ ሦስት ከፍተኛ ክህሎች ካላቸው የውጭ ባለሞያዎች ሁለቱ በማንነታቸው ምክንያት እንደተገለሉ ተናግረዋል።ከዚህ በተጨማሪም የሙያ ማስረጃቸው በተገቢው አካሄድ እውቅና እንዳላገኘ የተናገሩም አሉ። በተለይ ግትር የሚባለው የጀርመን የመኖሪያ ፈቃድ አሰጣጥ ለብዙ የውጭ ዜጎች ችግር መሆኑ ነው የሚነገረው።በዚህ የተነሳም የውጭ ባለሞያዎች ጀርመን ከመጡ በኋላ ወዲያውኑ ሀገሪቱን ጥለው ይሄዳሉ። ናይካ ፎሩታን የማኅበራዊ ሳይንስ እና የፍልሰት ተመራማሪ እንዲሁም በሁምቦልት ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው። በጀርመን ፓርላማ የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ ቡድን በፍልስት ጉዳዮች ላይ ባካሄደው ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት ተፈላጊ ተብለው ጀርመን የመጡ የውጭ ሠራተኞች ብዙም ሳይቆዩ ሀገሪቱን ለቀው እየወጡ ነው። ፈጽሞ መምጣት የማይፈልጉም አሉ።ይህም ከባድ መዘዞችን የሚያስከትል በመሆኑ ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል ፎሩታን።
«ይህ በአሀዛዊ መረጃ የተረጋገጠ እውነታ ነው። በተለየ ሁኔታ ተመልምለው የመጡትም ከአጭር ጊዜ ቆይታ በኋላ እዚህ መቆየት አንፈልግም ይላሉ።የምንናገረው መቀየር ስላለበት ሁኔታ ነው። እንኳን ደኅና መጣችሁ ብለን የምንቀበልበት ባህል ያስፈልገናል። ግልጽ ፀረ-መድሎ መመሪያዎች ስራ ላይ መዋላቸው ዋናው ጉዳይ ሊሆን ይገባል። ይህ በቀላሉ ልናሳድጋቸው ከሚያስፈልጉ ደንቦች መካከል አንዱ ነው።»
ዓለም አቀፉ የኤኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት በምኅጻሩ(OECD) በቅርቡ ያካሄደው ጥናት ጀርመን ከውጭ የሚፈለጉ ከፍተኛ ስራ አስፈጻሚዎችን የምትስብ ሀገር መሆኗ በግልጽ መቀነሱን ያሳያል። በድርጅቱ ጥናት መሠረት ጀርመን፣ በባለሞያዎች የስራ እድል ፣ ገቢ፤ የስራ ግብር፣ የወደፊት ተስፋ፣የቤተሰብ አባላት እድሎች፣ ብዝሀነት እና ወደ ጀርመን የመግባትና የመኖር መብቶች ረገድ ከ38 የድርጅቱ አባል ሀገራት 15ተኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው። በጎርጎሮሳዊው 2019 ግን 12ተኛ ደረጃ ላይ ነበረች። የጀርመን የፌደራል የሥራና ሠራተኛ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ ጀርመን በዓመት 400 ሺህ የውጭ ሠራተኛ ያስፈልጓታል። ይሁንና በጎርጎሮሳዊው 2021 ወደ ጀርመን የገባው የውጭ ሠራተኛ 40 ሺህ ብቻ ነው። ይህን ለመለወጥ የጀርመን መንግሥት በዚህ ዓመት የተሻሻለ የፍልሰት ሕግ ለማውጣት በዝግጅት ላይ ይገኛል። ከዚህ ሌላ የጀርመንን ዜግነት አሰጣጥ ሂደትም ይፋጠናል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም የጀርመን ተጣማሪ መንግሥት አባል ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ ገና ስምምነት ላይ አለመድረሳቸው ነው የሚነገረው። ዩጋቭ የተባለ ተቋም ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት መሰረት 59 በመቶ ጀርመናውያን የጀርመን ዜግነት አሰጣጥ ሂደት እንዲፈጥን አይፈልጉም።የፍልስት ጉዳዮች አጭኚዋ ፎሩታን ይህ አስተሳሰብ መለወጥ ይገባዋል ሲሉ የሌሎች ሀጋራት ተሞክሮዎችን ያካፍላሉ።
«እኛ ገና ስንዘጋጅ ሰዎች እንደሚያስፈልጉን ስናስብ ብሪታንያ ዩናይትድ ስቴትስ ካናዳና አውስትሬሊያ እየተገበሩት ነው። እነርሱ ብቻ አይደሉም። ሳዑዲ አረብያ ኳታር እና አረብ ኤምሬቶች ባለሞያዎችን ለመሳብ መጠነ ሰፊ የማስታወቂያ ዘመቻ ላይ ናቸው። ፊሊፒኖች ዜጎቻቸውን ለስራ አንልክም እያሉ ነው። አፍሪቃም ቢሆን ዜጎቹን በክፍለ ዓለሙ ለማቆየት እየጣረ ነው።»
ሌላዋ የፍልሰት ጉዳዮች ባለሞያ አላዲን ኤል ማፋኒ በኦስናብሩክ ዩኒቨርስቲ የፍልሰት ጉዳዮች መምህር በሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ጉባኤ ላይ ጀርመን እንደሌሎቹ ሀጋራት ተፈላጊ ያልሆነችበትን ምክንያት እንድትገነዘብ ያሳስባሉ።
«ክህሎት ያላቸው ባለሞያዎችን ፍልሰት በሚመለከት በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚፈለገው ይሆናል ብዬ አላስብም። አንድ ብሔራዊ ቋንቋ ብቻ ነው ያለን። የአየሩ ጸባይ ጥሩ አይደለም። የባህር ዳርቻ መዝናኛዎች የመሳሰሉት ብዙ የሉንም።ብዙ ጎዶሎዎች አሉን። »
አላዲን ኤል ማፋኒ መንግሥት ከውጭ ከሚመጡት ሠራተኞች ይልቅ ሀገር ውስጥ ባሉት በተለይ በ2015 በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ጀርመን የገቡት ስደተኞች ላይ እንዲተኮር ያሳስባሉ።ለዚህም ምክንያት ያሉትን ሲናገሩ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ጀርመን የገቡት ስደተኞች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነው። ከመካከላቸው አብዛኛዎቹ ስልጠናዎች ወስደው በተለያዩ ስራዎች ተሰማርተዋል። ወጣት ኤርትራውያንን ሲንከባከቡ የነበሩት መምህርት ክሪስታ ኤርትራውያኑ ወደ ሞያ ማሰልጠኛ ተልከው ስልጠናቸውን በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቃቸውን አስታውሰዋል። በእጅና በቴክኒክ ሞያ በነርስነት በድልድይ ግንባታ እና በሲቪል መህንድስና ትምህርታቸውን የጨረሱት ኤርትራውያኑ 8 ዓመት ተኩል ያህል ጀርመን ከቆዩ በኋላ የጀርመን ዜግነት ለማግኘት ቢያመለክቱም የልደት ምስክር ወረቀት ማቅረብ ባለመቻላቸው አልተሳካላቸውም ።በዚህ የተነሳም ወደ ሌሎች ሀገራት ለመሄድ እያሰቡ መሆኑን ክርስቲና ተናግረዋል ።
ሮማንያዊቷ ማራ እንደበፊቱ የጡረታ እድሜዋ እስኪደርስ ጀርመን የመቆየት ፍላጎት የላትም። እርስዋ እንደምትለው ጀርመን አንድ ወይ ሁለት ዓመት ብትቆይ ነው። ከዛ ውጭ አምስትና አስር ዓመት የመቆየት ሃሳብ የላትም።ተመራማሪዋ ናይካ ፎሩታን በጀርመን የፍልሰት ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ያሳስባሉ። እርሳቸው እንደሚሉት ምናልባት ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ጀርመን በተለያዩ የስራ መስኮች እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ባለሞያዎችን ልታጣ ትችላለች።
ዛቢነ ኪንካርትስ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ