1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዶዶላ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው የከፋ ጉዳት

ረቡዕ፣ ነሐሴ 22 2016

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ ከትናንት በስቲያ ንፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ በማሳዎች እና የቤት እንስሳት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል። ባስከተለው ጎርፍም ከ270 በላይ ሄክታር በምርት የተሸፈነ መሬት ከጥቅም ውጪ ስለመሆኑም ተነግሯል። ታይቶ የማታወቅ በተባለው ከባድ ዝናብ እስካሁን የሰው ሕይወት ስለመጥፋቱ ግን አልተሰማም።

https://p.dw.com/p/4k1GF
ዶዶላ አርሲ ዞን
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ ሰኞ አመሻሽ ላይ ንፋስ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ ካደረሰው ጉዳት በከፊል ምስል Dodola communication

በዶዶላ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው የከፋ ጉዳት

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ዶዶላ ወረዳ ከትናንት በስቲያ ሰኞ አመሻሽ ንፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ በምርት ማሳዎች እና የቤት እንስሳት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል። ከባዱ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍም ከ270 በላይ ሄክታር በምርት የተሸፈነ መሬት ከጥቅም ውጪ ስለመሆኑም ተነግሯል። ታይቶ የማታወቅ በተባለው ከባድ ዝናብ እስካሁን የሰው ሕይወት ስለመጥፋቱ ግን አልተሰማም።  

ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. አመሻሹን 11 ሰዓት ገደማ ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ውስጥ በዶዶላ ወረዳ በረዶና ንፋስ ቀላቅሎ ለአንድ ሰዓት ያህል የቆየው እጅግ ከባድ ዝናብ 19 ገደማ የቤት እንስሳትን ወዲያው ገድሏል። በወረዳው አምባ ሆሌ ቃንቁቲ በተባለ ቀበለ በጣለው በዚህ ከባድ ዝናብ የሰው ሕይወት ባያጠፋም በንብረት ላይ ግን እጅግ አስከፊ ውድመት ማስከተሉ ነው የተሰማው። በረዶና ንፋስ ቀላቅሎ በጣለው በዚህ እጅግ ከባድ በሆነው ዝናብ ከ12 ሄክታር መሬት ላይ ዛፎች በሙሉ ተነቃቅለው እንዳልነበሩ ሆነዋል ነው የተባለው።

በከባድ ዝናብ በቤት እንስሳት ላይ የደረሰው ከባድ ጉዳት

በተለይም ለቤት እንስሳቱ እልቂት ምክንያት የሆነው ከብቶቹ የሚሰማሩበትመንገድ በደራሽ ጎርፍ ተንዶ ከብቶቹ በከባድ ጎርፍ በመወሰዳቸው ነው ተብሏልም። የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዎሊዪ ናቢ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በዚህ ደረጃ የከፋ ዝናብ በአከባቢው ጥሎ አያውቅም። «እንደዚህ የከፋ ኤደለም እንጂ ባለፈውም ዓመት አንድ ቀበለሌ ላይም ከባድ ዝናብ ጉዳት አድርሶ ነበር። ትናንት በወረዳችን አምባ ሆሌ ቃንቁቲ ቀበሌ የደረሰው ንፋስ የቀላቀለውን በረዷማ ዝናብ ምንም እንኳ በሰው ላይ ጉዳት ባያደርስም 18 ላሞች እና አንድ ፈረስ ባጠቃላይ 19 የቤት እንስሳትን ገድሏል» ነው ያሉት።

በእርሻ ማሳዎች ላይ በደረሰው የውሃ መጥለቅለቅ የደረሰው የምርት ውድመት

እንደ ወረዳ አስተዳዳሪው አስተያየት በጣለው ታይቶ የማይታወቅ በተባለው በዚህ ከባድ ዝናብ እጅግ አስከፊ ጉዳት በምርት ላይ ማድረሱንም አስረድተዋል። «በ270 ሄክታር ላይ የተዘራው አዝርት በሙሉ ወድሟል። የገብስ፣ ስንዴ፣ አተር፣ ባቄላ እና ሌሎችም አዝርት ቡቃያ በዝናቡ ብዛት በጎርፍና በውሃ ተጥለቅልቆ ጉዳት ደርሶበታል። በተለይም የደረሰ የድንች ምርት እንዳለ አውጥቶ ጠራርጎ ወስዶታል። ቡቃያው እንዳለ ጎርፉ ተኝቶበትም ተስተውሏል» ነው ያሉት።

አርሲ ዶዶላ
ከባዱ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ የቤት እንስሳት ላይ ከባድ ጉዳት ከማድረሱም ሌላ ከ270 በላይ ሄክታር በምርት የተሸፈነ መሬት ከጥቅም ውጪ ሆኗል። ምስል Dodola communication

በከባዱ ዝናብ 19 የቤት እንስሳት ያለቁባቸው ስምንት አባወራዎች ቢሆንም በምርት ውድመት የተጎዱ ግን ቁጥራቸው ብዙ መሆኑ ነው የተገለጸው። የወረዳው አስተዳዳሪ እንደሚሉት የጉዳት መጠኑን በርግጥ አስተካክሎ የሚያጠና ኮሚቴ ተዋቅሮ እያጠናም ነው። የተዋቀረው ኮሚቴ የጉዳት መጠኑን በመለየት ተጎጂዎች እንዲረዱና እንዲቋቋሙም ይሠራል ነው ያሉት። «ተጎጂዎቹን ለማቋቋም ማኅበረሰቡ ባለው ነገር እየተረባረበ ነው» ያሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ በቡሳ ጎኖፋ በኩል ከሚደረግ ድጎማም ታክሎ የደረሰውን ከፋ ጉዳት ስለማይሸፍን ችግሩ ለዞንም ደርሶ የድጋፍ ምላሽ በአስቸኳይ እንዲደረግ መጠየቁን ጠቁመዋል።

የከፋው የዝናብ መጠን በኢትዮጵያ እያስከተለ ያለው ጉዳት

ከዚህም ባሻገር ከሰሞኑ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ከ6 ቀበሌዎቸ በላይ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ እስከሁን ከዘጠኝ መቶ በላይ ቤቶች በጎርፍ ሲዋጡ፤ ከስድስት ሺህ በላይ ዜጎች ለከፋ አደጋ መጋለጣቸው ተነግሯል። በአደጋውም ከ1,200 ሄክታር በላይ ምርት ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆኗል ተብሏል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዘንድሮ በሚጥል ከባድ ዝናብ እምብዛም በማይታወቅ መልኩ በዝናቡ መክፋት በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በመሬት ናዳ የበርካታ ዜጎች ሕይወት አልፏል።

ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት በዘንድሮው የክረምት ወራት ከመደበኛ በላይ የሆነ ከባድ ዝናብ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች ላይ እንደሚጥል ገልፆ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማስጠንቀቁን መዘገባችንም አይዘነገጋም።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋየ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ