በደቡብ ጀርመን በረዶ እንቅስቃሴዎችን ማስተጓጎሉ
ሰኞ፣ ኅዳር 24 2016ማስታወቂያ
በደቡባዊ ጀርመን የወረደው በረዶ እና ውሽንፍር እንቅስቃሴዎችን አስተጓጉሏል። መሬቱን የሸፈነው በረዶ የአየር እና የምድር መጓጓዣ መስመሮችን ከቅዳሜ ጀምሮ ከመዝጋቱ በተጨማሪ የቡድንደስሊጋ ግጥሚያዎችም እንዲሰረዙ አስገድዷል። በተለይ የሙኒኪ አውሮፕላን ማረፊያ ቅዳሜ ዕለት ሙሉ ለሙሉ እንዲዘጋ ከማድረጉም ሌላ የባቡር እንቅስቃሴንም አስቁሟል። የሙኒክ አውሮፕላን ማረፊያ ትናንት እሑድ ከታቀዱት በረራዎች ግማሹን መሰረዙን ያስታወቀ ሲሆን የረዥም ርቀት ባቡሮችም መስመሮቻቸውን ለማሳጠር መገደዳቸው ተገልጿል። በረዶው የሕዝብ መጓጓዣዎችን መርሃግብር ከማወኩ በተጨማሪም በአውራ ጎዳናዎች ላይ የመኪና ደጋዎችን ማስከተሉን መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።
በዛሬው ዕለትም ሙኒክ ከተማ የተከመረው በረዶ ከአውሮፕላን በተጨማሪ የባቡር መጓጓዣ መስመሩን በመዘጋጋቱ መንገደኞች በባቡር ጣቢያም ሆነ በአውሮፕላን ማረፊያ ሲጉላሉ ታይቷል። ከጀርመን በተጨማሪ በአጎራባች ሃገራት ስዊዘርላንድ እና ኦስትሪያም ኃይለኛ በረዶ መውረዱ ነው የተነገረው። በተቃራኒው የበረዶው ክምር ለሚወዱት የሸርተቴ ስፖርት የጠቀማቸው የስፖርቱ አዘውታሪ ወጣቶች እና አዋቂዎች በደስታ እየተዝናኑበት ነው።
ይልማ ኃይለሚካኤል
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ