1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ ህብረተሰቡን መረጋጋት የነሳው ግጭት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 2016

በኦሮሚያ ክልል በኢትዮጵያ መንግስትና መንግስት ሸኔ ባለው እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል የሚካሄደዉ ጦርነት የህብረተሰቡን የእለት ተእለት ህይወት መፈተኑን ቀጥሏል፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች በጸጥታ ችግሩ አለመረጋጋት ምክንያት ህይወታቸውን በተረጋጋ ሁኔታ መምራት ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4a1lv
ኦሮምያ ክልል
ኦሮምያ ክልልምስል Seyoum Getu/DW

በኦሮምያ የጸጥታው ሁኔታ አለመረጋጋት በመፍጠሩ ወጥቶ መግባትን ፈታኝ ሆንዋል

በምዕራብ ኦሮሚያ የቀጠለው የጨጥታ መናጋት

ምዕራብ ኦሮሚያ ከምራብ ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ ግራዊጦንቃ ከሚባል ቀበሌ አስተያየታቸውን የሰጡን፤ ነገር ግን ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ነዋሪ እንደሚሉት ያለው የጸጥታው ሁኔታ አለመረጋጋት በመፍጠሩ ወጥቶ መግባትን ፈታኝ አድርጓል፡፡ “ወጥቶ መግባት ተስኖናል፡፡ ከብቶቻችንን አሰማርተን በሰላም እንዴት ውለን እንገባለን የሚለው ሁሌም ለኛ ፈተና ነው፡፡ የዘራነውን ምርት መሰብሰብም ለኛ አሁን አሳሳቢው ጉዳይ ሆኖብናል፡፡ አሁን እርሰበርስ ተኩስ ልውውጡ እምብዛም የለም፡፡ ነገር ግን ቤታችን ይቃጠላል፡፡ በዚም በዚህም እረፍት አጥተናል፡፡ እንዴት እንደምንኖር ግራ ገብቶን ችግር ውስጥ ነን” ብለዋል፡፡

ከዚሁ ዞን አንፊሎ ወረዳ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳንጠቀም ጠይቀው አስተያየታቸውስ የሰጡን ነዋሪ ደግሞ ከታንዛንያውየኦሮሚያ ተፋላሚ አካላቱ ድርድር መክሸፍ በኋላ አለመረጋጋቱ ጸንቶ መቀጠሉን በማንሳት ይህም ህይወታቸውን መፈተኑን አስረድተዋል፡፡ “እውነት ለመናገር አሁን ስቃይ እያሳየን ያለው በአንድ አካል ላይ ብቻ የሚፈረድ አይደለም፡፡ በሁሉም በኩል ነው የምንሰቃየው፡፡ የሰው ንብረት እየተዘረፈ፣ ቤት እየተሰበረ ሰው መሄጃ አጥተናል፡፡ ብዙዎቻችን በድርድሩ ላይ ተስፋ ጥለን ነበር፡፡ እናርፋለን ብለን ብናስብም አልሆነም” ብለዋል፡፡ 

የመጓጓዣ ፈተና እና ከቦታ ቦታ ሚደረግ አንቅስቃሴ

ሌላው በትራንስፖርት ስራ ተሰማርተው ህይወታቸውን የሚመሩት ከምዕራብ ሸዋ ዞን ጌዶ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን ደግሞ የፀጥታ ሁኔታ መደፍረሱ ክፉኛ ከተጎዱ አንዱ የትራንስፖርት ስራ ነው ባይ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ህይወታቸውን በቀጥታ መፈተኑን አመልክተዋል፡፡ “ያለው ሁኔታ ደስ አይልም፡፡ ሰው ላይ በጣም ፍርሃት አንዣቧል፡፡ አሁን ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ትራንስፖርት ያን ያህል ችግር ነው ማለት አይቻልም፡፡ ግን ሰው እንደወትሮው ስለማይንቀሳቀስ ቶሎ ቶሎ ከቦታ ቦታ ለመድረስ ይፈትናል”ይላሉ፡፡

ከአንድ ሳምንት በፊት ክፉኛ የጸጥታ ሁኔታው ተናግቶ ከ40 በላይ ንጹሃን ተገድሎበታል በተባለው የአርሲ ዞን ሽርካ ወረዳ አሁን ላይ ወደ አንጻራዊ ሰላም ብመለስም አርሶ አደሩ በተለመደው ሁኔታ ምርቱን መሰብሰብ ላይ ተግዳሮት እንደገጠመው የአከባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የአከባቢው ነዋሪ ከጸጥታው አንጻር አሁን የተሻለ ነገር ብኖርም ስጋቱ ግን አሁንም መኖሩን ያስረዳሉ፡፡

“በመንግስት እርምጃ ከተወሰደ በኋላ አሁን አንጻራዊ ሰላም አለ፡፡ ችግር ያደረሱትን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ ተሰርቷል፡፡ ግን ደግሞ ስጋቱ አሁንም አለ” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪ አርሶ አደሩ ስጋቱ ምርቱን በጊዜ መሰብሰቡ ላይ እና ህይወትን አሻግሮ ማሰብ ላይም ከፍተኛ ክፍተት መፍጠሩን ግን አልሸሸጉም፡፡

ለዓመታት በግጭት ላይ የከረሙትን ወደ ቄያቸው የመመለስ ውጥንና ስጋቱ

ከምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ በአከባቢው አሁን ላይ የሚስተዋል ግጭት ባይኖርም ማህበረሰቡ ከስጋቱ ነጻ ነው የሚባልበት ደረጃ ላይ ግን ገና አለመደረሱን ያወሳሉ፡፡ በዚህ አከባቢ ከአንድ ዓመት በፊት በኪረሙ በተፈጸመው የለየለት ግጭት ተፈናቅለው ወደ ከተማመግባታቸውን የሚያነሱት አስተያየት ሰጪ አሁን አሁን ከቄዬያቸው ተፈናቅለው ወደ ከተማ የተሰደዱትን ነዋሪዎች ወደ ቀዬያቸው የመመለሱ ግፊት ብያይልም አሁንም ግን ማህበረሰቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ቀዬው ተመልሶ ለማምረት ከስጋት ነጻ አይደለም ብለዋል፡፡

ኦሮምያ ክልል
ኦሮምያ ክልልምስል Seyoum Getu/DW

“አስቀድሞ በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ እደሚታወቀው ምርት ያለበት መሬት ውስን ነው፡፡ ወደ ከተማ ዙሪያ ያሉ ደጋማ አከባቢዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ማህበረሰቡ እየሰበሰቡ ነው፡፡ ግን አሁንም ድረስ ወደ ቆላማ ቀበሌያት ለመመለስ ህብረተሰቡ ስጋት አለው፡፡ በነዚያ አከባቢዎች እርሻ ከቆመ ሁለት ሶስት ዓመታት ስለተቆጠሩ ወደ ደንነት ተቀይሯል፡፡ እርሻ ያረሱና አሁን እየሰበሰቡ ያሉት ሁለት ሶስት ቀበሌዎች አይበልጡም፡፡ አሁንም አስተማማኝ ሰላም በሁሉም ቦታ ተመልሷል በምለው ያልተማመን ከከተማው ተቀምጠናል፡፡ የወረዳው 90 ከመቶ አሁን ደን ሆኗል ማለት ትችላለህ” ሲሉ አስተያየታቸውን አብራርተዋል።

የግጭቱ መቀጠልና ዘላቂ እልባቱ

ዶይቼ ቬለ ስለነዋሪዎች ስጋት እና ቀጣይ የመፍትሄው አቅጣጫ ላይ ለኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ደውሎ  ለመጠየቅ ብጥር ስልካቸው አይነሳም፡፡ በኦሮሚያ የቀጠለው ጦርነት የህብረተሰቡን ህይወት ክፉኛ መፈተኑ ግን ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ የመንግስት ባለስልጣኑና የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ሆነው በማህበራዊ ገጻቸው መንግስትን በመተቸት የሚታወቁት አቶ ታዬ ደንደዓ ይህ የሚስተዋለው የከፋ የጸጥታ ችግሩ ቤተሰባቸውን እንኳ መጠየቅ አዳጋች እንዳደረገባቸው ከሰሞኑ መግለጻቸውም ይታወቃል፡፡ ባሳለፍነው ህዳር ወር በኦሮሚያ ተፋላሚዎች መካከል በታንዛንያ ዳረሰላም የተቀመጠው የሰላም ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁ አይዘነጋም፡፡

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ