1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ የሰላማዊ ሰዎች ሞትና አለመረጋጋት ያስከተለው ግጭት እንዳሳሰባቸው ሃገራት ገለጹ

ዓርብ፣ ነሐሴ 5 2015

በኢትዮጵያ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች የሰላማዊ ሰዎች ሞት ያስከተለው አለመረጋጋት እንዳሳሰባቸው ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ አምስት ሃገራት ሥጋታቸውን ገለጹ። መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የአውሮጳ ሕብረት ልዑክ እና የ19 ሃገራት ኤምባሲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ «ሁሉም ወገኖች ሲቪሎችን እንዲጠብቁ» ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/4V2RT
የጎንደር ከተማ
የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ረቡዕ ነሐሴ 3 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ ባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ላሊበላ፣ ጎንደር እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ አስታውቋል። በስድስቱ ከተሞች እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2015 የሚዘልቅ የሰዓት ዕላፊ ተደንግጓል።ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ አምስት ሃገራት በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሰላማዊ ሰዎች ሞት እና አለመረጋጋት ያስከተለው ግጭት እንዳሳሰባቸው ገለጹ። «ጉዳት ለደረሰባቸው ሕዝቦች የተሟላ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀጣይነት ያለው ሰብአዊ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ» በኢትዮጵያ የአውሮጳ ሕብረት ልዑክ እና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የ19 ሃገራት ኤምባሲዎች ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሰው እና የሰላማዊ ሰዎች ሞት እና አለመረጋጋት ያስከተለው ግጭት እንዳሳሰባቸው አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ የአምስት ሃገራት መንግሥታት ሥጋታቸውን ገለጸዋል። መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው የአውሮጳ ሕብረት ልዑክ እና የ19 ሃገራት ኤምባሲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ «በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ሁከት፣ የዜጎች ሞት እና አለመረጋጋት» እንዳሳሰባቸው ተመሳሳይ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የአውሮጳ ሕብረት ልዑክ እና ኤምባሲዎቹ «ሁሉም ወገኖች ሲቪሎችን እንዲጠብቁ» ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ከተሞች የሰዓት ዕላፊ ገደብና የዕለቱ እንቅስቃሴ

በግጭቱ የሚሳተፉ «ሁሉም ወገኖች ሲቪሎች ላይ ጥቃት እንዳይደርስ እንዲከላከሉ፤ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩ እንዲሁም ለሚያጋጩ ጉዳዮች መፍትሄ በሰላማዊ መንገድ ለማፈላለግ በጋራ እንዲሠሩ» የአውስትራሊያ፤ ጃፓን፤ ኒው ዚላንድ፤ የዩናይትድ ኪንግደም እና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥታት ዛሬ ዓርብ በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል። በጋራ መግለጫቸውም ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያውን ሁሉ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የሚደረገውን ጥረት መደገፉን እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የአውሮጳ ሕብረት ልዑክ እና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የ19 ሃገራት ኤምባሲዎች በበኩላቸው «ጉዳት ለደረሰባቸው ሕዝቦች የተሟላ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ቀጣይነት ያለው ሰብዓዊ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ» ጥሪ አቅርበዋል። በጋራ መግለጫቸው «የውጭ ዜጎች ከግጭቱ አካባቢ ለቅቀው እንዲወጡ እና ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲተላለፉ እንዲፈቀድ» ጠይቀዋል። 

የአውሮጳ ሕብረት ልዑክ እና ኤምባሲዎቹ «የሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም በሚቀጥልበት ጊዜ ውስብስብ ጉዳዮችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት በጋራ መሥራት እና ግጭቱ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክልሎች ተዛምቶ ብጥብጥ እንዳይፈጠር ተገቢው መከላከል እንዲደረግ» እንደሚያበረታቱም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ያቀረበው ጥሪ

ከአውሮጳ ሕብረት ልዑክ ጋር መግለጫውን ያወጡት የኦስትሪያ፣ የቤልጅየም፣ የቼክ ሪፐብሊክ፣ የዴንማርክ፣ የፊንላንድ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የሐንጋሪ፣ የአየርላንድ፣ የጣልያን፣ የሉክሰምበርግ፣ የማልታ፣ የኔዘርላንድስ፣ የሮማኒያ፣ የፖላንድ፣ የስሎቬኒያ፣ የስፔን እና የስዊድን ኤምባሲዎች ናቸው።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ