1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮ-ቴሌኮም መደበኛ የአክሲዮን ሽያጭ ልብ መባል ያለባቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥቅምት 13 2017

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የኢትዮ-ቴሌኮምን መደበኛ አክሲዮን ሽያጭ ከጀመረ በኋላ የኩባንያውን ያለፈ ዓመት ገቢ እና ትርፍ በማስላት “ያዋጣል” ወይስ “አያዋጣም” የሚሉ ትንታኔዎች በማኅበራዊ ድረ-ገጾች እና በመገናኛ ብዙኃን እየታዩ ነው። ለመሆኑ ልብ መባል ያለባቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? ባለሙያዎችስ ምን ይመክራሉ?

https://p.dw.com/p/4m9X1
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ
ፍሬሕይወት ታምሩ በዋና ሥራ አስፈፃሚነት የሚመሩት እና በሰኔ 2016 የአክሲዮን ኩባንያ ሆኖ የተመዘገበው የኢትዮ-ቴሌኮም 45 በመቶ ድርሻ ለውጪ ባለወረቶች ይሸጣል ተብሎ ይጠበቃል። ምስል Solomon Muche/DW

በኢትዮ-ቴሌኮም መደበኛ የአክሲዮን ሽያጭ ልብ መባል ያለባቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

የኢትዮ-ቴሌኮም የመደበኛ አክሲዮን ሽያጭ ከጥቅም 7 ቀን፣ 2017 ጀምሮ በመካሔድ ላይ ይገኛል። የኩባንያውን 10 በመቶ ድርሻ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው ሒደት እስከ ታኅሳስ 25 ቀን፣ 2017 ድረስ የሚቆይ ነው። በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የጸደቀው የኢትዮ-ቴሌኮም አክሲዮን ኩባንያ ደንበኛ ሳቢ መግለጫ (prospectus) እንደሚያሳየው የግዢ ማመልከቻ የተጠየቀባቸው የአክሲዮኖች ብዛት ከተቀመጠለት 200,000,000 ገደብ ከደረሰ ሒደቱ ሊቆም ይችላል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከፍተኛ ተስፋ የጣሉበት ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ ሥራ ሲጀምር ድርሻዎቹን ለሽያጭ በማቅረብ የ130 ዓመታት ባለ ጸጋ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ቀዳሚ ይሆናል ተብሎ ይጠብቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በዋናነት በተለያዩ ሚናዎች የሚመሩት ግብይት በሚቀጥለው አንድ ወር ገደማ ሊጀመር እንደሚችል ባለሥልጣናቱ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ጥብቅ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት በወረቀት ሲካሔድ በቆየው የአክሲዮን ግብይት ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል ገበያ የፕራግማ ኢንቨስትመንት አድቫይዘሪ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ መርዕድ ብሥራትን የመሳሰሉ ባለሙያዎች ጭምር ተስፋ የጣሉበት ነው።

የፋይናንስ እና የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ መርዕድ “አንድ ድርጅት ማስታወቂያ ያስነግራል። ማስታወቂያ ካስነገረ በኋላ እንደ አክሲዮን ድርጅት ካፒታል ይሰበስባል። ከዚያ በኋላ እልም ብሎ ነው የሚጠፋው” ሲሉ እስካሁን ሥራ ላይ የቆየው የአክሲዮን ገበያ “ሥርዓት ያጣ” እንደነበር ይተቻሉ።

አቶ መርዕድ ኢትዮጵያ መልሳ የምታቋቁመው የካፒታል ገበያ ለአክሲዮን ድርሻ የሕግ ማዕቀፍ እና ሥነ ሥርዓት በማበጀት፣ ለባለቤቶች ጥበቃ በመስጠት እና ሰነዶቹን ዲጂታላይዝ በማድረግ “በጣም በቀላሉ እንድንገበያይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል” ሲሉ ፋይዳውን ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ ሰነደ-ሙዓለ ንዋዮች ገበያ
የኢትዮጵያ ሰነደ-ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በአንድ ወር ገደማ ውስጥ ሥራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ባለሥልጣናት ፍንጭ ሰጥተዋል። ምስል Ethiopia Securities Exchange (ESX)

የኢትዮ-ቴሌኮም 10 በመቶ ድርሻ ለምን ይሸጣል?

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሥራ እስኪ ጀምር ድረስ የኢትዮ-ቴሌኮም መደበኛ አክሲዮኖች ሽያጭ ቢጠናቀቅም “መገበያየት፣ መሸጥ፣ ማስተላለፍ” አይቻልም። የሽያጩ ዓላማ “የኢትዮጵያ ሕዝብ በኩባንያው ባለቤትነት እንዲሳተፍ መፍቀድ” እንደሆነ ይፋ የተደረገው የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ይጠቁማል።

ከዚህ ቀደም የመንግሥት የልማት ድርጅት የነበረው ኢትዮ-ቴሌኮም አደረጃጀቱን በመቀየር የአክሲዮን ኩባንያ ሆኖ ባለፈው ሰኔ 24 ቀን 2016 ተመዝግቧል። የአክሲዮን ሽያጩ በስኬት ከተጠናቀቀ የኢትዮ-ቴሌኮም 90 በመቶ ድርሻ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተያዘ ይሆናል።

የመንግሥት የመዋዕለ-ንዋይ ክንፍ ሆኖ የሚያገለግለው እና በኢትዮ-ቴሌኮም የአብላጫ ባለ ድርሻ የሆነው ተቋም “የቀረውን 90.0% ድርሻ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የአክሲዮን ሽያጩ ከተጠናቀቀ በኋላ ለሌሎች አክሲዮን ገዥዎች ለመሸጥ ሊወስን ይችላል።”

የኢትዮ-ቴሌኮም የተፈቀደ እና የተከፈለ ካፒታል 100 ቢሊዮን ብር ነው። ኩባንያው አንድ ቢሊዮን መደበኛ አክሲዮኖች አሉት። የአንድ አክሲዮን ዋጋ (par value) 100 ብር ተተምኗል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የኩባንያውን 10 በመቶ ድርሻ ለኢትዮጵያውያን ሲሸጥ የአንድ አክሲዮን ዋጋ የ200 ብር ልዩነት አለው። አንድ አክሲዮን በ300 ብር ተመን ሲሸጥ የኩባንያውን አጠቃላይ ዋጋ ወደ 300 ቢሊዮን ብር (2.5 ቢሊዮን ዶላር) ከፍ ያደርገዋል።

የፋይናንስ እና የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ መርዕድ ብሥራት የመደበኛ አክሲዮኖች ሽያጭን በማጠናቀቅ ድልድል ተሰርቶ በኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ (Ethiopia Securities Exchange) ሕዝቡ እርስ በርስ መገበያየት ሲጀምር ዋጋው ሊለወጥ እንደሚችል ይናገራሉ። “የአንዷ ሰነድ ዋጋ አሁን በ300 ብር ነው የምትሸጠው። የዚያን ጊዜ ገበያው ነው የሚወስነው” የሚሉት አቶ መርዕድ መሸጫው “ከ300 ከፍ ሊል ይችላል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ “የቀረውን 90.0% ድርሻ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የአክሲዮን ሽያጩ ከተጠናቀቀ በኋላ ለሌሎች አክሲዮን ገዥዎች ለመሸጥ ሊወስን” እንደሚችል የኢትዮ-ቴሌኮምን መደበኛ አክሲዮኖች ለመሸጥ የተዘጋጀው የደንበኛ ሳቢ መግለጫ ይጠቁማልምስል Ethiopian Investment Holdings

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ለሽያጭ ያቀረባቸው የኢትዮ-ቴሌኮም መደበኛ አክሲዮኖች በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የተመዘገቡ ናቸው። ኢትዮ-ቴሌኮም “ለሽያጭ ከቀረቡት አክሲዮኖች ምንም ዓይነት ገቢ” አያገኝም። ከሽያጭ የሚሰበሰበው ገንዘብ “ሙሉ በሙሉ ለአብላጫ አክሲዮን ባለድርሻው ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ገቢ ይደረጋል።”

ኢትዮጵያውያን ዝቅተኛውን 33 አክሲዮኖች በ9,900 ብር ወይም ከፍተኛውን 3,300 አክሲዮኖች በ999,900 ብር መግዛት ይችላሉ። ገዥዎች ተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር 1.5% የአገልግሎት ክፍያ ማለትም 4 ብር ከ50 ሣንቲም በእያንዳንዱ መደበኛ አክሲዮን ይጠበቅባቸዋል።

አክሲዮን ገዥዎች ማመልከቻቸዉን ባስመዝገቡ በ48 ሰዓታት ውስጥ ክፍያውን መፈጸም ይኖርባቸዋል። አክሲዮን ለመግዛት ክፍያ የፈጸሙ ገንዘብ እንዲመለስላቸው መጠየቅ አይችሉም። ሙሉ የሽያጭ ሒደቱ ቴሌ-ብር በተባለው እና በግንቦት 2013 ሥራ በጀመረው የኩባንያው መተግበሪያ ብቻ የሚከናወን ነው።

አክሲዮን ለመግዛት ማመልከቻ አቅርበው ክፍያ የፈጸሙ ሁሉ ግን የፈለጉትን ላያገኙ ይችላሉ። ለአክሲዮን ግዥ የተመደበው ጊዜ ሲያበቃ ኩባንያው “ያልተጠናቀቁ ማመልከቻዎችን የማረጋገጥ እና የብቁ አመልካቾችን የአክሲዮን ድልድል ሥራ” በስድስት ሣምንታት ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ አሳውቋል።

አቶ መርዕድ “የ10 በመቶ ባለድርሻ የሚሆኑ የድርጅቱ የትርፍ ተካፋይ ይሆናሉ” ሲሉ ተሳክቶላቸው ባለ አክሲዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሚያገኙትን ቀዳሚ ጥቅም ይናገራሉ። ኢትዮ-ቴሌኮም በሀገሪቱ የንግድ ሕግ መሠረት “የአክሲዮን ድርጅት እስከሆነ ድረስ አስተዳደሩ የሚሠራቸውን ማንኛውም ሥራዎች በየሩብ ዓመቱ ሊሆን ይችላል፤ በየዓመቱ ሊሆን ይችላል ለባለ አክሲዮኖቹ ሪፖርት ማድረግ አለበት።” በዚህም የ10 በመቶ ድርሻ ባለቤት የሚሆኑ የኩባንያውን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት የመቀበል ሕጋዊ መብት ይኖራቸዋል።  

የመደበኛ አክሲዮን ሽያጭ ከተጀመረ በኋላ የኢትዮ-ቴሌኮምን ያለፈ ዓመት ገቢ እና ትርፍ በማስላት “ያዋጣል” ወይስ “አያዋጣም” የሚሉ ትንታኔዎች በማኅበራዊ ድረ-ገጾች እና በመገናኛ ብዙኃን እየታዩ ነው።

የኩባንያው የደንበኛ ሳቢ መግለጫ የኢትዮ-ቴሌኮምን የትርፍ ትንበያ ወይም ግምት አላካተተም። መግለጫው “ኩባንያው ለመደበኛ አክሲዮን ባለአክሲዮኖች በሚጠብቁት ደረጃ የትርፍ ክፍፍል ማድረግ ላይችል ወይም እንዳይከፈል ሊወስን” እንደሚችል በግልጽ አስፍሯል።

ኤሪክሰን
ኢትዮ-ቴሌኮም ከኤሪክሰን በተፈራረመው የብድር ሥምምነት ምክንያት ወደ አክሲዮን ኩባንያነት የሚደረገውን ሽግግር እንደማይቃወም የሚጠይቅ ደብዳቤ መላኩን የደንበኞች ሳቢ መግለጫው ይጠቁማል።ምስል Maxppp/kyodo/dpa/picture alliance

የፋይናንስ እና የኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ መርዕድ በመገናኛ ብዙኃን ማንም ሰው የኢትዮ-ቴሌኮምን መደበኛ አክሲዮኖች መግዛት “ያዋጣል አያዋጣም” ስላለ ኢትዮጵያውያን ኢንቨስት ማድረግ እንደማይኖርባቸው ይመክራሉ። “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያዋጣኛል አያዋጣኝም የሚለውን መወሰን ከፈለገ ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ ካገኙ የኢንቨስትመት አማካሪዎች ወይም የኢንቨስትመንት ባንኮች ሙያዊ ትንታኔዎችን እና ምክሮችን ካገኘ በኋላ” መወሰን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተዘጋጀው 227 ገጾች ያሉት የደንበኛ ሳቢ መግለጫ የኢትዮ-ቴሌኮምን የፋይናንስ መረጃዎች እና የአክሲዮን ሽያጭ ሒደቱን ጨምሮ ዝርዝር መረጃዎች የሚያቀርብ ነው። የኢትዮ-ቴሌኮም የቦርድ ዳይሬክተሮች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የፈረሙበት ሰነድ ተቋሙ ሊያጋጥሙት የሚችሉትን ሥጋቶች ይዟል።

ከዚህ ውስጥ ኢትዮ-ቴሌኮም የስዊድን የቴሌኮም ኩባንያ ከሆነው ኤሪክሰን ጋር የቴሌኮምዩንኬሽን ቁሳቁሶች ለመግዛት የተፈራረመው የብድር ሥምምነት ይገኝበታል። ኢትዮ-ቴሌኮም የኤሪክሰን 1 ቢሊዮን 113 ሚሊዮን 907 ሺሕ 948 ብር ወይም 19 ሚሊዮን 49 ሺሕ 955 ዶላር ዕዳ አለበት።

ዕዳው ኢትዮ-ቴሌኮም የመንግሥት የልማት ድርጅት ሣለ የተበደረው በመሆኑ ወደ አክሲዮን ኩባንያነት የሚደረገውን ሽግግር ኤሪክሰን እንደማይቃወም የሚጠይቅ ደብዳቤ መላኩን የደንበኞች ሳቢ መግለጫው ይጠቁማል። ለጥያቄው ምላሽ እንዳልተሰጠ የሚገልጸው የደንበኞች ሳቢ መግለጫ ይኸ ኤሪክሰን እና ኢትዮ-ቴሌኮም የተፈራረሙት የብድር ሥምምነት “ተጥሷል አልተጣሰም” የሚል ውዝግብ በማስነሳት በተቋሙ መልካም ሥም፣ የፋይናንስ አቋም እና የሥራ ክንውን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ያትታል።

በገበያው የሚፈጠር ብርቱ ውድድር፤ በተቋሙ ንብረቶች ላይ ሊፈጸሙ የሚችሉ ጉዳቶች እና ሥርቆት በኩባንያው ሥራ አፈጻጸም ላይ ዕክል ሊፈጥሩ እንደሚችሉ መደበኛ አክሲዮን ለሚገዙ ዜጎች አስቀድሞ ያስጠነቅቃል። በኢትዮጵያ ሊከሰቱ የሚችሉ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ አለመረጋጋቶች እንዲሁም መንግሥት የሚከተላቸው ፖሊሲዎች መቀልበስ ወይም ከፍተኛ ለውጥ በኩባንያው ላይ ተጽዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችልም ይጠቁማል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ