በአዲስ አበባ ከተማ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን የተከተለው የገበያ አለመረጋጋት
ሐሙስ፣ ነሐሴ 9 2016የኢኮኖሚ ማሻሻያውን የተከተለው የገበያ አለመረጋጋት
የኢትዮጵያ መንግስት ከሳምንታት በፊት ይፋ ያደረገውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ የመሰረታዊ የምግብ ፍጆታ እቃዎች መጠነኛ አለመረጋጋት አሳይተዋል፡፡
በውጪ ምንዛሪ ተሸምተው ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡ ምርቶች በተጨማሪ አገር ውስጥ በሚመረቱ የአትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም የእህልና ጥራጥሬ ምርቶች ላይ መጠነኛ የዋጋ ጭማሪዎች መስተዋሉን ሻጭና ሸማቹ ይናገራሉ፡፡
“ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት 900 ብር ገደማ የነበረው የዜት ዋጋ አሁን ላይ 1200 ብር በመግባቱ የምንመገበው ምግብ ውስጥ ዘይት ለመጠቀም እስከመቸገር አድርሶናል” ያሉት በጉልት አነስተኛ ንግድ ተሰማርተው የሚገኙ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ እናት አስተያየት ነው፡፡ በመገናኛ አከባቢ ድንች፣ ቲማቲም እና ጎምን ይዘው ለጉልት ንግድ ጎዳና ላይ የተቀመጡ እኚህ እናት በተለይም የዘይት ዋጋ ይቀንሳል ብባልም በተግባር ግን እምብዛም ለውጥ መጥቶ አለማየታቸውን በመግለጽ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡
«የኤኮኖሚ ማሻሻያው» የብር አቅም መዳከም ለብዙኀኑ ሕዝብ ምን ማለት ይሆን?
በሾላ ገቢያ በጥራጥሬ እና የቅመማ ቅመም ምርት የችርቻሮ ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩት እናት ደግሞ ብያንስ በነዚህ ምርቶች ከተወሰኑት ውጪ እምብዛም ጭማሪ አልታየም ይላል፡፡ “ዶላር እኛ ከያዝነው ምርት ጋር እምብዛም ግንኙነት ያለው አይመስለኝም፡፡ ብርግጥ ነጋዴ በጣም የዋጋ ጭማሪ እያደረገ ነው፡፡ ያ ግን ሸማቹ እንዲሸሸን ስለሚያደርግ ትንሽ ትርፍ እያገኘን ብንሸት ይሻላል የሚል እምነት ነው ያለኝ” ሲሉም ሃሳባቸውን አክለዋል፡፡
መጠነኛ ዋጋ ጭማሪ የታየበት የጥራጥሬ ምርት
እኚህ በችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩት እናት ምስር በተለይም የአገር ውስጡ ምርት ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ ይህም ከ160 በመነሳት እስከ 200 ደርሶ የነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ወደ 180 ግን ይገኛል ነው ያሉት፡፡ ይህም የሆነው በጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች ምርቱን በስፋት ከገቢያው በማጥፋት እጥረት እንዲፈጠር በመደረጉ ነው ብለዋል፡፡ ከውጪ የሚገባውና በሸማቾች እምብዛም ተፈላጊ ያልሆነው ምስር ላይ ግን ከ10 ብር ያልበለጠ አነስተና ጭማሪ መደረጉንም አክለዋል፡፡ መኮሮኒ 115፣ ባቄላ 130፣ ሽንብራ 85፣ ቡና እንደየጥራት መጠኑ ከ400-500 በኪሎ ስሸጡም ተመልክተናል፡፡
የሸቀጦችና እቃዎች ዋጋ ንረትt፤የፓስፖርት አገልግሎት ክፍያ ጭማሪ
ሌላው በዚሁ በሾላ ገቢያ በጥራጥሬ ችርቻሮ ንግድ ላይ የተሰማሩት ነጋዴ አቅርቦትም ጭምር ላይ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ያነሳሉ፡፡ “የዋጋ ጭማሪ ለምሳሌ ምስር ላይ ታይቷል፡፡ ይህም የሆነው በአቅርቦት እትረት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የትራንስፖርት ችግሩ ይሁን የዶላሩ ጭማሪ መንስኤው ምን እንደሆነ አናውቅም” ነው ያሉት፡፡
በቆሎ በ90፣ የሽምብራ ሽሮ 120፣ የአተር ሽሮ እስከ 140፣ ምስር 180 በኪሎ እንደሚሸጥም ቸርቻሪው ተናግረዋል፡፡
የመንግስት ገቢያ ቁጥጥር ጥረት
በመርካቶም ዞር ዞር ብለን በጎበኘንባቸው አከባቢዎች የገቢያው ሁኔታ ከዚህ ጋር እምብዛም ልዩነት ያለው አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያና አንደምታዎች
በዚሁ ወቅት ገቢያውን ለማረጋጋትና የቁጥጥር ስራውን ለመከወን ተሰማርተው ሚገኙት የንግድና ኢንደስትሪ ሰራተኞች ተመልክተናል፡፡ ስማቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው አስተያየታቸውን የሰጡን እኚህ ባለሙያ መንግስት የዋጋ ቁጥጥር በሚደርግበት ወቅት አሁናዊ ዋጋውን ከኢኮኖሚው ማሻሻያ በፊት ከነበረው ያነጻጽራል፡፡ “መንግስት ዋጋ ለማረጋጋት እየሰራ ካለው ተግባር አንዱ ከዶላር ጭማራ በፊት ከነበረው አንጻር የዋጋ ጭማሪው ምን ህል እንደሆነ በማየት ነጋዴዎች የዋጋ ዝርዝር እየለጠፉ እንዲሸጡ ይደረጋል” ነው ያሉት፡፡
ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየው የጤፍ ዋጋ
ሸማቾች እንደሚሉት ግን በርካታ የምግብ ፍጆታ እቃዎች ጭማሪ እያሳየ ነው፡፡ ለአብነትም 130 እና 140 ገደማ የነበረው ጤፍ አሁን ከ160 እስከ 180 መድረሱን ሸማቾች ገልጻሉ፡፡ “አንደኛ ደረጃ የተባለውን ጤፍ በኪሎ 160 ነው የገዛሁት” ይላሉ አንደኛዋ አስተያየት ሰጪ ሸማች….. ሌላኛዋም ይቀጥላሉ “በጣም ተወደደ ስባል ጤፍ ከፍተኛው 140 ነበር አሁን 160-180 ደርሷል በኪሎ..” ብለዋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ በገበያ እንዲመራ ከተወሰነ ወዲህ ገበያው ምን ይመስላል?
ሌላው ሸማቾች አማረው የሚያነሱት ወቅታዊው የዋጋ ጭማሪ ሽንኩርት ነው፡፡ “ሽንኩርት ሁሌም ክረምት ላይ ይወደዳል፡፡ ምክንያት የሚሉንም በጭቃው የመንገድ ችግር መኖሩን ነው፡፡ ሽንኩረት ከ60 ብር ገደማ ተነስቶ አሁን ወደ 80 ብር ከፍ ብሏል” ብለዋል ሸማች አስተያየት ሰጪ፡፡ እንደ ሩዝና መኮረኒ ያሉ ምርቶች ላይም በኪሎ እስከ 10 ብር ጭማሪ ተስተውሏል ነው የተባለው፡፡ በርካታ አትክልት እና ፍራፍሬ ላይም ጭማሪ ብስተዋልም ጭማሪው ግን አነስተኛ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሸማቹም ሆነ ነጋዴው ግን ሁሉም ሸመማች ነውና ለንግዱ ዘርፍ ስርዓት ብበጅለት ሚል ጥሪ ያቀርባሉ፡፡
ስዩም ጌቱ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ