1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌስቲቫል

ዓርብ፣ ሐምሌ 25 2006

በጀርመኗ ሙኒክ ከተማ ከተለያዩ የአውሮፓ ሃገሮች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን አመታዊውን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል በማክበር ላይ ናቸው።

https://p.dw.com/p/1Cnde
ምስል picture alliance / JOKER

ባለፈው ረቡዕ በተጀመረው በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፌስቲቫል የእግር ኳስ ውድድር አራት ቡድኖች ለዛሬው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ደርሰዋል።ኢትዮ- ኖርዌይ ኢትዮ- ስዊዝን ሁለት ለአንድ፤ ኢትዮ-ሆላንድ ኢትዮ ኮሎንን ሁለት ለባዶ፤ ኢትዮ-በርሚንግሃም ኢትዮ-ቱሉዝን አምስት ለሦስት፣ እንዲሁም ኢትዮ-ለንደን ኢትዮ- ቤልጅየምን አንድ ለባዶ አሸንፈዋል። የፌስቲቫሉ መርሃ ግብር ዛሬ ሲጥል ኢትዮ-ኖርዌይ ከኢትዮ-ሆላንድ እንዲሁም ኢትዮ-በርሚንግሃም ከኢትዮ-ለንደን ለዋንጫ ለማለፍ ይጫወታሉ።ሶስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው ይህ ፌስቲቫል ዘንድሮ በጀርመኗ ባየር ሙኒክ አዘጋጅነት የሚካሄደው ፌስቲቫል ሲጀመር በጥቂት ግለሰቦች አነሳሽነት መጀመሩን በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ ከበደ ሃይሌ ይናገራሉ።

Allianz Arena München
ምስል imago/Imagebroker

በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ያገናኘው የአራት ቀናት የሙኒክ ፌስቲቫል ከእግር ኳስ በተጨማሪ በልዩ ልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች እና ዝግጅቶች እስከ ነገ የሚቆይ መሆኑን አቶ ከበደ ሃይሌ ተናግረዋል።

ካሁን ቀደም ፍራንክፈርት፤ኦስሎ፤ኮሎኝ፤ደልፍት፤ስቶክሆልም፤ፓሪስ፤አምስተርዳም እና ኑረንበርግን በመሳሰሉ ከተሞች የተካሄደው በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፌስቲቫል በየአመቱ እውቅ ሰዎችን ወደ መድረኩ የመጋበዝ ልምድ አለው። ቴክኒካል ዳይሬክተሩ አቶ ከበደ ሃይሌ ዘንድሮም ለኢትዮጵያ ስፖርት የጎላ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሁለት እንግዶች አሉን ይላሉ።

በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና ባህል ፌስቲቫል ነገ በህጻናትና አዋቂዎች የእግር ኳስና የሩጫ ውድድሮች እና የሙዚቃ ዝግጅቶች ፍጻሜውን ያገኛል።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ