1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአውሮጳ የኢ.ኦ.ተ አብያተ ክርስቲያን ፋይዳ

ረቡዕ፣ ሰኔ 28 2015

የአብያተ ክርስቲያኑ ቁጥር እየጨመረ በውጭ የሚኖረውም ተገልጋይ ቁጥር እያደገ በሄደ መጠን ቤተ ክርስቲያኗ የምትሰጠው አገልግሎትም መስፋቱ አልቀረም። ሃይማኖት ሳይለዩ ለሀገሩ ባዳ ለሰዉ እንግዳ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞችን መርዳት ከአብያተ ክርስቲያኑ ተግባራት መካከል እንደሚጠቀሱ ሊቀ ካኅናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4TPP3
Deutschland I 40-jähriges Jubiläum der Michaeliskirche in Köln Longerich
ምስል Hirut Melesse/DW

በአውሮጳ የኢ.ኦ.ተ.አብያተ ክርስቲያን ፋይዳ

በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ አብያተ ክርስቲያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በአውሮጳም የዛሬ አርባ ዓመት አንድ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያንና የተገልጋዩ ቁጥር ዛሬ እጅግ ያድጋል ። አብያተ ክርስቲያን ለዳያስፖራው ምን ትርጉም አላቸው? ፋይዳቸውስ ምንድነው? 
የዛሬ አርባ ዓመት በጀርመን ብሎም በአውሮጳ አንድ ተብሎ የተጀመረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በጀርመን ወደ 25 በአውሮጳ ደግሞ ወደ 60 አድጓል። በአውሮጳ የሚኖረው የቤተ ክርስቲያኗ ተገልጋይ  ቁጥር በውል ባይታወቅም የዛሬ 40 ዓመት ከነበረው ጋር ሲነፃጸር ግን አሁን በብዙ እጥፍ ማደጉን ማየት ይቻላል። ይህም ለቤተ ክርስቲያኗ መስፋፋት ዐብዩ ምክንያት ሆኗል። በጀርመን የመጀመሪያው የኢኦተቤ/ክርስቲያን ምስረታ 40ኛ ዓመት በዓል ሲከበር እንደታየው ያኔ ጀርመን የመጡ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እዚህ የወለዷቸው ልጆች ቤተሰብ መስርተው፣ ያፈሩት ሦስተኛው ትውልድም በቤተ ክርስቲያኗ እየተገለገለ ነው። ለመሆኑ በውጭ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ለዳያስፖራው ምን ትርጉም አላት?ፋይዳዋስ ምንድነው? ከሁለት ሳምንት በፊት ኮሎኝ በተከበረው በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ምስረታ 40ኛ ዓመት በዓል ላይ ያገኘኋቸው ከተለያዩ የጀርመንና የአውሮጳ ከተሞች የመጡትን የበዓሉ ታዳሚዎች ቤተ ክርስቲያኗ ለነርሱ ምን ትርጉም እንዳላት ጠይቋያቸው ነበር። ሉከኔዘርላንድስ በበዓሉ ላይ የተገኘው ጋዜጠኛ ደረጀ ሀብተ ወልድ የመጀመሪያ ልጁን ምዕራፍን በርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የዛሬ 14 ዓመት  ነው ክርስትና ያስነሳው። ደረጀ ቤተ ክርስቲያንን በውጭ የምትገኝ መጽናኛችን ነው የሚላት። ከኑርንበርግ ለመጣው ለታመነ ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ነገር ናት። እንዳልካቸው መኮንን ሉክሰምበርግ አውሮጳ ሲኖር ሀያ ዓመት ተጠግቷል። የቤተ ክርስቲያንን ትርጉም ለመስረዳት፣ በሚኖርነት አካባቢ ቤተ ክርስቲያን ባልነበረበት ወቅት ይሰማው የነበረውን ነው የተናገረው።
 ትርጉሟ ትልቅ ነው የሚለው የኔዘርላንዱድሱ ነዋሪ የሺጥላ ፋይዳውንከወቅቱ ሁኔታ ጋር በማገናኘት ነው የገለጸው። እንደ  የሺጥላ ሁሉ ድዩስቡርግ ጀርመን ለሚኖረው ለአራት ልጆች አባት ሀብታሙ ገብረ ፃዲቅም የቤተ ክርስቲያን ፋይዳ ። ቀላል የሚባል አይደለም። መሪጌታ ዳዊት ከፍያለው የኑርንበርግ ጀርመን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በበዓሉ ላይ ካተገኑት በርካታ ካኅናት አንዱ ናቸው። ቤተ ክርስቲያኗ ከምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ጎን ለጎን ኢትዮጵያን በውጭው ዓለም በማስተዋወቅ የምታደርገው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም ብለዋል። 
የአብያተ ክርስቲያኑ ቁጥር እየጨመረ በውጭ የሚኖረውም የቤተ ክርስቲያኗ ተገልጋይ አሀዝ እያደገ በሄደ መጠን ቤተ ክርስቲያኗ የምትሰጠው አገልግሎትም መስፋቱ አልቀረም። ሃይማኖት ሳይለዩ ለሀገሩ ባዳ ለሰዉ እንግዳ የሆኑ በባዕድ ሀገር ሕይወት ያልተስተካከለላቸውን ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞችን መርዳት ከአብያተ ክርስቲያኑ ተግባራት መካከል እንደሚጠቀሱ በጀርመን እንዲሁም በአውሮጳ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን መስራችና የኮሎኝ ቦን ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀካህናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ ተናግረዋል ። ሊቀ ካኅናት ዶክተር መርዓዊ እንደሚሉት የሌሎች እምነት ተከታዮችም ቤተክርስቲያኗን በመርዳት የሚሳተፉባቸው አጋጣሚዎች አሉ። አብያተ ክርስቲያኑ እዚህ የተወለዱ ልጆች ሃይማኖታቸውን ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያውቁ ልዩ ልዩ ጥረቶች ያደርጋሉ።በጀርመን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን መስራቾች አንዷ የሊቀካኅናት ዶክተር መርዓዊ ተበጀ ባለቤት ወይዘሮ ንጋት ከተማ ለዚህ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት አገልጋዮች መካከል አንዷ ናቸው።ወይዘሮ ንጋት የአብያተ ክርስቲያኑም ሆነ የምዕመኑ ቁጥር ማደግ አሁን ህልም ቢሆንባቸውም የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ጉዳይ ግን ያሳስባቸዋል። 

Deutschland I 40-jähriges Jubiläum der Michaeliskirche in Köln Longerich
ምስል Hirut Melesse/DW
Deutschland I 40-jähriges Jubiläum der Michaeliskirche in Köln Longerich
ምስል Hirut Melesse/DW

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ