1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቱርክ አሸማጋይነት የቀጠለው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ውይይት

ሰኞ፣ ነሐሴ 6 2016

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በሳምንት መጨረሻ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በ X አስታውቋል። ይህም ለጉዳዩ የተሰጠውን ከፍ ያለ ዋጋ የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል

https://p.dw.com/p/4jNz3
Somaliland Berbera 2024 | Großes Schiff, Container und Schwerlastkran im Hafen
ምስል Eshete Bekele/DW

በቱርክ አሸማጋይነት የቀጠለው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ውይይት  

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርክ አንካራ የሚያደርጉት ሁለተኛ ዙር ውይይት ዛሬ እንደሚከናወን ተገለፀ።

ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ፣ አዲስ አበባን የባሕር በር ተጠቃሚ የሚያደርግ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ የሻከረውንየኢትዮጵያ እና የሶማሊያን ግንኙነትበማሸማገል ላይ የምትገኘው ቱርክ ዛሬ ሁለተኛውን ዙር ውይይት እንደምታስተናግድ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አረጋግጧል። 

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ እንድ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ሁለቱ ሀገራት የያዙት የተካረረ አቋም ቱርክ ለጀመረችው ጥረት ቀላል ፈተና እንደማይሆን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ የማሸማገያ ውይይት ላይ እስካሁን ወደ ሕጋዊ ሠነድነት ተለውጦ ውልም ሆኖ ያላደገውን የመግባቢያ  ስምምነት ሰርዛ በምትኩ ከሶማሊያ የባሕር በር ማግኘት የምትችልበት የመደራደሪያ ዕድል ከቀረበላት ይህንን ልትመርጥ እንደሚገባ ገልፀዋል።

በቀጣናው ፍላጎት ያላት ቱርኩ የማሸማገል ጥረቷ ይሰምር ይሆን?

የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ መንግሥታት ኢትዮጵያን የባሕር በር ተጠቃሚ ሲያደርግ፣ ሶማሊላንድን እንደ ሀገር እውቅና ይሰጣል የተባለለትን ስምምነት ከተፈራረሙ ማግስት ሶማሊያ ጉዳዩን ሉዓላዊነቴን የሚነካ ነው በሚል "ሕጋዊ ተቀባይነት የሌለው" በማለት ውድቅ ከማድረጓ ባለፈ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የከረረ ውዝግብ አስከትሏል።

በጉዳዩ ላይ አሸማጋይ ሆና የገባችው ቱርኩ የሁለቱን ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አንካራ ድረስ በመጥራት ከዚህ በፊት ያወያየች ሲሆን፣ ሁለተኛውን ዙር ዛሬ ታስተናግዳለች። ይህንንም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።

ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያን እና ግብጽን ጎብኝተው የተመለሱት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን በሳምንቱ መጨረሻ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ "የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነት እውቅና መስጠቷ እስከተረጋገጠ ድረስ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረቱ ይቋጫል" ብለው ነበር። ውጤት አልባ ሆኖ የተጠናቀቀው የመጀመርያው ዙር ውይይት በዚህኛው ዙር ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ፍንጭ የሰጠውን ይህን የቱርክን አቋም በተመለከተ የጠየቅናቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የዓለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ፣ በቀጣናው ላይ የጅኦ ፖለቲካ ፍላጎት ያላት ቱርክ የማሸማገል ጥረት መጀመሯ በጎ የሚባል መሆኑን ከነ ሥጋታቸው አንስተዋል።

የቱርክ ፕረዚደንት ረሲብጠይብ ኤርዶጋን
የቱርክ ፕረዚደንት ረሲብጠይብ ኤርዶጋንምስል Getty Images/AFP/O. Kose

ኢትዮጵያ የመግባቢያ ስምምነቱን ሰርዛ ከሶማሊያ ጋር ትስማማ ይሆን ?

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በሳምንት መጨረሻ  ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር በስልክ መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በ X አስታውቋል። ይህም ለጉዳዩ የተሰጠውን ከፍ ያለ ዋጋ የሚያሳይ ተደርጎ ተወስዷል። ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ የፈረሙት የመግባቢያ ስምምነት አሳሪ ውል ሆኖ ያደገ ባለመሆኑ በዚህኛው ውይይት ሶማሊያ ከዚህ በፊት ከቱርክ ጋር ከተፈራረመችው ወታደራዊ ስምምነት ጋር በማይጋጭ መልኩ፣ ለኢትዮጵያ የባሕር በር መጠቀሚያ አማራጭ ለማዘጋጀት ከተስማማች ኢትዮጵያ ያለምንም ማቅማማት ልትቀበለው እንደሚገባ ባለሙያው ገልፀዋል።

የሶማሊላንድ ምላሽ እና የቀጣይ ሁኔታ

በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት እጅግ ደስተኛ የሆነችው ሶማሊላንድ ፕሬዝደንቷ ሙሴ ቢሂ ሰሞኑን አደረጉት በተባለ ንግግር "የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሶማሊላንድ ጉዳዮች ጣልቃ ገብተዋል" ሲሉ ወቅሰዋል። "ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ማንኛውንም ነገር ከመፈረሟ በፊት ጉዳዩን እንደገና በማጤን በቅድሚያ ወደ ሶማሌ መሄድ አለባት" በሚል የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሰጡትን መብራሪያ "ይህ የሶማሌላንድን ሉዓላዊነት የሚጎዳ ነው፣ ሶማሌላንድ ይህንን አትፈቅድም" በማለት አጣጥለውታል። 

ሰለሞን ሙጬ

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ኂሩት መለሰ