ሶማሊያ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 9 2011የአውሮጳ የሰላም ተቋም ዋና ሃላፊ እና የቀድሞ የተመድ የሶማሊያ ልዩ ልዑክ ሚካኤል ኬቲንግ እንደሚሉት ከ5 እና 10 ዓመታት በፊት የነበረው የሶማሊያ ሁኔታ አሁን ተለውጧል። ኬቲንግ በአሁኑ ጊዜ የዓለም ባንክን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ አጋሮች እንዲሁም የአውሮጳ ህብረትን የመሳሰሉ ተቋማት ለሀገሪቱ የሚሰጡት ድጋፍ መጨመር ከተለወጡት እና ጥሩም ከሚባሉት ምልክቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን ይናገራሉ። በርሳቸው አስተያየት የመቅዲሾ ጎዳናዎች ከቀድሞው አሁን በሰዎች ተሞልተዋል። ያም ሲባል ግን ሀገሪቱ ውስጥ አሁን ችግሮች የሉም ማለት አይደለም። ሆኖም እንደ ኬቲንግ ሶማሊያ አሁን የምትከተለው አቅጣጫ ግን በጣም ጥሩ ነው።
«ሀገሪቱ እጅገ አደገኛ ለሆነ ጽንፈኝነት ተጋልጣለች። የሶማሊያ ፖለቲካ ባህርይ በራሱ ዕድገቱን እያጓተተ ነው። ሶማሌዎች ሀገራቸው ለመልከዐ-ምድራዊ ፖለቲካ ተጻራሪ ኃይሎች በቲያትር መድረክነት መጠቀሚያ እንደሆነች ይሰማቸዋል። ለረዥም ጊዜ የዘለቀው ድህነት የዓየር ንብረት ለውጥ የህዝብ ቁጥር እድገትና የከተሞች መስፋፋት አደጋዎች ፈጥረዋል። ሆኖም አሁን በመከናወን ላይ ያሉት ተግባራት ጥሩ አቅጣጫ የያዙ ናቸው።»
ለዓመታት በጦርነት ስትናጥ የቆየችው ሶማሊያ ብዙ አጥታለች። በቀደሙት የርስ በርስ ውጊያዎችም ሆነ አሁን በሚካሄዱት የደፈጣ ጥቃቶች በርካታ ዜጎቿ ሞተዋል። ብዙ ንብረትም ወድሟል። ሰላም የራቀው የሶማሊያ ህዝብ በዓለም ዙሪያ እንደ ጨው ተበትኗል። የሶማሊያ መንግሥት ከደፈጣ ተዋጊው ከአሸባብ ቡድን ጋር የሚያካሂደውን ውጊያ ለማገዝ የአፍሪቃ ህብረት ጦር ሶማሊያ ከዘመተ ዓመታት ቢቆጠሩም ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ አልቻሉም። ይህና ገና ብዙ ይቀረዋል የሚባለው የሶማሊያ ፖለቲካ ሳይስተካከል ሀገሪቱ መረጋጋት መቻሏን የሚጠራጠሩ ጥቂት አይደሉም። ማይክ ግን ሀገራቸውን የመለወጥ ብቃት ያላቸው ሶማሊያውያን ከበረቱ እና ፖለቲከኞችዋም ከተቻቻሉ እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እገዛም ከታከለ ሀገሪቷን የማረጋጋት ከፍተኛ እድል አለ ይላሉ። በተለይ ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ በዚህ ረገድ ሊጫወት የሚችለው ሚና ከፍተኛ ነው እንደ ኬቲንግ።
« የሶማሊያ አጋሮች በሙሉ የአካባቢው ፣የአረብ ባህረ ሰላጤ ሀገራት አውሮጳ ሰሜን አሜሪካ እና ቻይና በፀጥታ በኤኮኖሚ እና በፖለቲካ ጥቅሞች ምክንያት ሶማሊያ ይበልጥ እንድትረጋጋ ፣ይበልጥ ኤኮኖሚዋ ምርታማ እንዲሆን ይፈልጋሉ። አጋሮች የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ስልቶች ለመደገፍ ደግሞ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ ትልቁ ፈተና ነው። በጣምም ከባድ ነው። አውሮጳም ጀርመንም ብትሆን ይህ ገቢራዊ እንዲሆን አዎንታዊ ተጽእኖ የማድረግ ሚና አላቸው።»
በኪቲንግ አስተያየት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሶማሊያ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምዋን እንድታጎለብት፣የግሉ ዘርፍ አስተዳደር እንዲጠናከር በፀጥታውም በኩል ብዙ ፖለቲካዊ ተቀባይነት ያለው እና ተጠያቂ የፀጥታ ኃይል እንዲኖራት ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል። ፀጥታውም ከህዝቡ እንጂ ከለጋሾች ጥቅም አንጻር ብቻ ሊታይ አይገባም። ከዚሁ ጋር የፖለቲከኞች መቻቻልም አስፈላጊነቱ የጎላ ነው።
«እንደሚመስለኝ ለጋራ ጥቅም ሲባል በስተመጨረሻ በፖለቲካው ሰጥቶ መቀበል እውን ሊሆን ይገባል። ያም ማለት በህዝቦች መካከል ከፍተኛ መተማመንን መፍጠር፣ ሰዎች ሥራዎቻቸውን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉባቸውን እና የሚያምኑባቸውን ደህንነታቸው የተጠበቀ ቦታዎችን እና ተቋማትን መፍጠር ማለት ነው። ይህ ጠጠር ያለ አጀንዳ ነው። ሊሰራ የሚችለው ግን በሶማሊያውያን በኩል ወደፊት የመራመድ ቁርጠኝነት እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች በኩልም በሚሰጥ ተጨማሪ ድጋፍ ነው።»
በኬቲንግ እምነት በብዙ ጎሳዎች የተከፋፈለውን የሶማሊያን ህዝብ ለማግባባት ኳሱ በሶማሊያ መሪዎች እጅ ውስጥ ነው። መሪዎቹ በተለይ ከወጣቶች ከሴቶች እና ከሲቪክ ማህበራት ጋር የመተሳሰር ፈቃደኝነቱ ካላቸው ችግሩን ሊፈቱት ይችላሉ። ሥራው ግን ቀላል አይሆንም።
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ