1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስለሰላም ስምምነቱ በዉጭ የሚኖሩ የትግራይ ፖለቲከኞችና ተወላጆች አስተያየት

ሰኞ፣ ጥቅምት 28 2015

በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስትና በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የሰላም ስምምነት የትግራይ ተወላጆችና የፖለቲካ ፓርቲዎችን እያወዛገበ ነው። በውጭ አገር የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለዶይቸቨለ እንዳሉት የሰላም ሰነዱ የትግራይ ሕዝብን ጥቅም አሳልፎ የሰጠ ብለውታል።

https://p.dw.com/p/4J9jh
Pretoria | Waffenstillstandsabkommen für Äthiopien
ምስል PHILL MAGAKOE/AFP

የትግራይን ሕዝብ ጥቅም አሳልፎ የሰጠ ሰነድ

በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስትና በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የሰላም ስምምነት የትግራይ ተወላጆችና የፖለቲካ ፓርቲዎችን  እያወዛገበ ነው። በውጭ አገር የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለዶይቸቨለ እንዳሉት የሰላም ሰነዱ የትግራይ ሕዝብን ጥቅም አሳልፎ የሰጠ ብለውታል። ሰነዱን የፈረሙት የሕወሐት ባለስልጣናት ስለሰነዱ እስካሁን ምንም ማብራሪያ አለመስጠታቸውም ለሕዝቡ ያላቸውን ንቀት ያሳያል ብለዋል። ዝርዝሩ ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር ያቀርብልናል። 
አቶ ዮሴፍ ሃይለስላሴ የባይቶና ዓባይ ትግራይ የስራአስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሕግ ባለሙያ ናቸው። ስምምነቱ መልካም ቢሆንም፤ የሕወሐት መሪዎች የሕዝቡን ጥቅም አሳልፈው ሰጥተዋል የሚል እምነት ነው ያላቸው።
«መንግስታችን ይመለስ ብለን ስንት መስዋእት ተከፍሎ የተመለሰ መንግስትን አስረክበው ነው የመጡት። ዞሮዞሮ ተማርከው ነው የመጡት። ስለዚህ ይህ ነገር የትግራይ ሕዝብንና የወጣቱን መስዋእት ያላገናዘበ፣ ጥፋተኞችን ተጠያቂ የማያደርግ፣ የኤርትራ መንግስትም ይወጣል አይወጣም ግልጽ ሳይሆን ዞሮ ዞሮ በምርኮ ደረጃ ተማርከው ነው የመጡት። ስለዚህ አሁን ከጫንቃው ላይ አውርዶ አሁን አዲስ ፓርቲ፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ሁኔታ ሁኖ አሁን ከኢትዮጵያ መንግስት ይሁን ከማንም ተደራድሮ አዲስ አሰላለፍ ይፈጥራል ብለን ነው የምናስበው። ዞሮ ዞሮ ግን ሰላሙን ተቀብለነዋል ብየ ልነግርህ እፈልጋለሁ።»
ስምምነቱ በተለይ በውጭ ሃገር በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ዘንድ ማወዛገቡን ቀጥሏል። ወይዘሮ ጸጋ በጀርመን አገር ሙዩኒክ ከተማ ነዋሪ ናቸው።
«ሰላሙ በጣም ይፈለጋል። ግን  መሣሪያ ሁሉ ማስረከብ አለበት የሚለው ግን ከራሴ ጀምሮ ማንም ትግራዋይ የሚቀበለው አይመስለኝም። ምክንያቱም ጀኖሳይድ እየተካሄደ ነው፣ ጦርነትም እየተካሄደ ነው። ሰላም ከተባለ ቦኋላም ጦርነቱ አላቋረጠም። ስለዚህ ለኛ ትንሽ ከባድ ነው። በራሴ ልናገር እምነትም የለኝም። ሰላም እፈልገዋለሁ፣ የትግራይ ሕዝብም ይፈልገዋል። ግን ሰላም እንደሚሆን እየተደረገ ነው ወይ ጦርነት እየቀጠለ ስለሆነ። አሁን በችግር ላይ ስለሆነ ሁሉም ነገር ሰላም እንዲሆንልን በትክክል ከተደረገ በጣም ደስተኛ ነኝ።»
በታላቋ ብሪታንያ የማንችስተር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጡዕማይ በበኩላቸው ተከታዩን ብለዋል።
«አሁን የተፈጠረው የሰላም ሰነድ ምንም አይነት የትግራይ ሕዝብን የማይወክል፣ በተአምር የትግራይ ሕዝብን የሚወክል እንዳልሆነ፣ እኔም የትግራይ ተወላጅ በመሆኔ ይህንን በምንም ተዓምር የማልደግፈው ሐሳብና ሰነድ እንዳልሆነ ነው። ምክንያቱም የትግራይ ሕዝብ የመኖር መብቱን የነፈገ ሰነድ ነው ብዬ ነው የማምነው። 
የሕወሓት መሪዎች ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ስለተደረሰው ስምምነት ዝርዝር ጉዳይ ምንም ባለማለታቸው በትግራይ ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል። በየማሕበራዊ መገናኛ ብዙኃኑም ይኸው ሲገለጽ እየተስተዋለ ነው። አቶ ጡዕማይ ግልጽ ማብራሪያ አለመሰጠቱ የሕወሓት መሪዎች ለሕዝብ ያላቸውን ንቀት ያሳያል ሲሉ ይገልጻሉ።
ድምጽ 3 «ግልጽ የሆነ ማብራሪያና መግለጫ መሰጠት ነበረበት። እስካሁን ድረስ አለመግለጻቸውን ለሕዝብ ያላቸውን ንቀት የሚያሳይ ነው ብዬ ነው የምገምተው።»
በጉዳዩ ላይ አዲስ አበባ የሚገኙ የዓረና ትግታይና የሳልሳይ ወያነ አመራሮችን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልክ ደውለን ባለማንሳታቸው ሐሳባቸውን ማካተት አልቻልንም።


ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ማንተጋፍቶት ስለሺ