ሳዑዲ አረቢያ የጨከነችበት ጀማል ኻሾግጂ
ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2011ቱርካዊት እጮኛውን ሊያገባ የቆረጠው ጀማል ኻሾግጂ ከመንግሥቱ የሚያስፈልገውን ሰነድ ፍለጋ መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በቱርኳ የኢስታንቡል ከተማ በሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ ገብቶ አልተመለሰም። ኻሾግጂ በጠፋባቸው የመጀመሪያዎቹ አምስት ቀናት የቱርክ ባለሥልጣናት ሳይገደል አልቀረም የሚል ጥርጣሬያቸውን ለመንግሥት ቅርበት ባላቸው ጋዜጦች በኩል ቢያናፍሱም በይፋ ግን ያሉት ነገር አልነበረም።
የቱርክ ጋዜጦች እንደፃፉት ኻሾግጂ ወደ ቆንስላው በገባበት ዕለት በሁለት አውሮፕላኖች ቱርክ የደረሱ የሳዑዲ አረቢያ የደኅንነት ሰራተኞች ይጠብቁት ነበር። ሳባህ የተባለው ጋዜጣ የደኅንነት ሰራተኞቹን ማንነት፤ በሳዑዲ አረቢያ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ያላቸው ኃላፊነት እና በቱርክ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በሆቴል እና በቆንስላው አካባቢ የነበራቸውን እንቅስቃሴ የሚያሳይ ዘገባ በምስል አስደግፎ አስነብቧል። እንደ መገናኛ ብዙኃኑ ዘገባ ከሆነ የደኅንነት ሰራተኞቹ ጀማል ኻሾግጂን በቆንስላ ፅህፈት ቤቱ ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለው ሰውነቱን ቆራርጠው ጥለዋል። በቱርክ የመረጃ ምንጮች መሠረት እስካሁን ይፋ አይደረግ እንጂ አሰቃቂውን ግድያ የሚያስረዳ በምስጢር የተቀዳ ድምፅ በቱርክ ሹማምንት እጅ ሳይገኝ አልቀረም። መቀመጫውን በዋሽንግተን ያደረገው የአረብ ጥናት ማዕከል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኻህሊል ጃሻን "ጀማል እንደገባ ከቆንስላው ኃላፊ ጋር ተገናኝቶ ስለሚፈልገው ሰነድ ለጥቂት ደቂቃዎች ተወያይቷል። ወዲያውኑ እርሱን ለማስወገድ በተላኩ ሰዎች ጥቃት ተፈፅሞበታል። ድንገተኛ ሞት አይደለም። በቦክስ ግብግብ የተፈጠረም አይደለም" ሲሉ ግድያው ቀድሞ የተወጠነ እንደሆነ ዕምነታቸውን ገልጸዋል።
ሳዑዲ አረቢያ በበኩሏ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ጀማል በኢስታንቡል ከሚገኘው ቆንስላ ጉዳዩን ፈፅሞ ወጥቷል የሚል ማስተባበያ ብትሰጥም ማረጋገጫ ማቅረብ አልቻለም። የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው የዜና አውታሮች፤ ትዊተር እና ፌስቡክን በመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረ-ገፆች በኩል በጠላቶቹ የተጎነጎነ ሴራ እያለ ሊያጥል ሞክሯል። ትንታኔዎቹ ግን ከቱርክ እየተነሳ ሌላውን ዓለም ያዳረሰውን ዜና መገዳደር አልተቻላቸውም። ማስተባበያዎቹ እርስ በርስ የሚጋጩ ነበሩ። ይኸ የሆነው ግን እስከ ዕለተ-ቅዳሜ ማምሻ ብቻ ነበር። የሳዑዲ አረቢያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በአገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ ይፋ ባደረገው መግለጫ "የሳዑዲ አረቢያ ዜጋ በሆነው ጀማል ኻሾግጂ መጥፋት ላይ የተደረገው የመጀመሪያ ምርመራ በእርሱ እና በኢስታንቡል የሳዑዲ ቆንስላ ባገኛቸው ሰዎች መካከል ጭቅጭቅ እና ግጭት እንደነበር ያሳያል። ግጭቱ ሕይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል" ሲል ሞቱን አረጋገጠ።
ዓለም አቀፍ ጫናው ሲበረታ ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ረቸብ ጠይብ ኤርዶኻን ጋር መክረው መላ እንዲፈይዱ በንጉስ ሳልማን የተላኩት ልዑል ኻሊድ-አል ፋይሰል አገራቸው ውስብስብ ማጥ ውስጥ መግባቷን ተረድተው ነበር። ልዑሉ ከቱርክ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲመለሱ ለቅርብ ሰዎቻቸው "ከዚህ ውስጥ መውጣት እጅግ ከባድ ነው" ሲሉ መናገራቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር አደል አል-ጁበይር "ወደ ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ሲመጣ የሳዑዲ አረቢያ የጸጥታ ሰራተኞች አገኙት። የጸጥታ ሰራተኞቹ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲመለሱ ከቆንስላው መውጣቱን ሪፖርት አቀረቡ። የሁለቱ ቅዱሳን መስጊዶች የበላይ ጠባቂ ንጉስ ሰልማን አብዱልአዚዝ ጉዳዩን ከቱርክ ባለሥልጣናት ጋር ለመመርመር ልዑካን ልከው ነበር። ከቱርክ የደረሱን ሪፖርቶች የጸጥታ ሰራተኞቹ ከተመለሱ በኋላ ካቀረቡት ጋር የሚጣጣም አልነበረም። በዚህም ምክንያት ንጉሱ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርግ አዘዙ። ከዘጠኝ ቀናት በኋላ በተደረገው ምርመራ የጸጥታ ሰራተኞቹ ሪፖርት አሳማኝ እንዳልነበር ተደረሰበት። እንዴት እንደሆነ ለጊዜው ባናውቅም በቆንስላ ፅፈት ቤቱ ውስጥ መገደሉን ደርሰንበታል። አስከሬኑም የት እንዳለ አናውቅም" ሲሉ ጉዳዩን በዝርዝር በአሜሪካው የፎክስ ቴሌቭዥን በኩል አስረዱ።
ሳዑዲ አረቢያ ዜጎቿ አቅደው ፈፅመውታል ከሚባለው የመስከረም 11 የአሜሪካ ጥቃት በኋላ እንዲሕ አይነት ቀውስ ሲገጥማት የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም። ጫናው ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የመገናኛ ብዙኃን እና ፖለቲከኞች ቢበረታም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን በሳዑዲ አረቢያ ላይ አልጨከኑም። ለሳዑዲ አረቢያ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ለሸጥ የተዘጋጀችውን አሜሪካ የሚመሩት ትራምፕ በሰጧቸው ማብራሪያዎች ሁሉ ጉዳዩን አገራቸው ከምታገኘው ኤኮኖሚያዊ ጥቅም ጋር አገናኝተውታል። ሳዑዲ አረቢያ ማስተባበሏን አቁማ የጋዜጠኛውን ሞት ስታምን ፕሬዝዳንት ትራምፕ "የተሰጠው ምላሽ ለእኔ አመርቂ አይደለም። ቢሆንም ጥሩ የመጀመሪያ እርምጃ ነው። ነገር ግን ምላሹን ማግኘት እፈልጋለሁ" ሲሉ በጥቂቱም ቢሆን ጠንከር ያለ አስተያየት ሰነዘሩ።
የሳዑዲ አረቢያ ጠቅላይ አቃቤ-ሕግ በጀማል ኻሾግጂ ግድያ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 18 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል። የሳዑዲ መንግሥት የሰጠው ማብራሪያ የተጠርጣሪዎቹ መታሰር ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መልካም እርምጃ ቢሆንም ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ብሪታንያን የመሳሰሉ የአውሮጳ ልዕለ-ኃያላንን አላሳመነም። ሶስቱ አገሮች ለጀማል ኻሾግጂ ሞት ተጠያቂ የሆኑ እስኪለዩ እና የተፈጸሙ ወንጀሎች ለፍርድ እስኪቀርቡ ድረስ ጉዳዩ እንዲመረመር ጠይቀዋል። የጀርመኗ መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በተለይ ጉዳዩ ከኻሾግጂ ግድያ ባሻገር ከፍ ያለ ትርጉም እንዳለው ተናግረው የሳዑዲ አረቢያ ማብራሪያ መስጠት አለበት ብለዋል።
የሳዑዲ አረቢያ ዜግነቱን ሳይቀይር ኑሮውን በአሜሪካ አድርጎ የነበረው ጀማል ኻሾግጂ ከትውልድ አገሩ ከወጣ በኋላ የዓረቡ ዓለም የመናገር ነፃነቱን ተሸብቧል እያለ ይነቅፍ ነበር። በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ለመጨረሻ ጊዜ ለፃፈው የግል አስተያየት "በአሁኑ ወቅት የዓረቡ ዓለም እጅግ የሚያስፈልገው ነገር ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ነው" የሚል ርዕስ ሰጥቶታል። ጀማል ኻሾግጂ በግል አስተያየት አምድ ላይ በሰፈረው ጽሁፍ የፍሪደም ሐውስን አመታዊ ሪፖርት እየጠቀሰ ከቱኒዚያ በቀር የዓረቡ ዓለም ሐሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብቱ ታፍኗል ሲል ሞግቷል።
በአመታዊው ዘገባ እንደሰፈረው ጀማልም እንደጠቀሰው ዮርዳኖስ ፤ ኩዌት እና ሞሮኮ በከፊል ነፃ ሲባሉ ሌሎቹ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ከታፈነባቸው ጎራ ተመድበዋል። ካሾግጂ ታዲያ "በእነዚህ አገራት የሚኖሩ አረቦች መረጃ የላቸውም፤ አሊያም የተሳሳተ መረጃ ይዘዋል። በዚህም ምክንያት በለት ተለት ሕይወታቸውም ይሁን በአጠቃላይ በቀጣናው ተፅዕኖ በሚያሳድሩ ጉዳዮች ላይ መነጋገርም ሆነ መፍትሔ መፈለግ አይችሉም" ከሚል ድምዳሜ ደርሷል። ኻሾግጂ "ማሻሻያዎች ይደረጋሉ የሚል ወሬ አለ። ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ፅንፈኝነትን ከሳዑዲ አረቢያ ለማጥፋት ቃል ገብቷል። ያ ያስፈልገናል። ሙስናንም ለማጥፋት ቃል ገብቷል- ይኸም ያሻናል። ይሁን እና እነዚህን ሁሉ በጎ ነገሮች እያደረገ ያለው ሌሎች አስተያየቶችን በማፈን ነው" እያለ በተደጋጋሚ ወቅሷቸዋል።
የቱርክ መንግሥት ሹማምንት የኻሾግጂ ግድያ ያለ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን እውቅና አልተፈጸመም ሲሉ ይሞግታሉ። ሳባህ በተባለው የቱርክ ጋዜጣ ዘገባ መሠረት በሁለት አውሮፕላኖች ወደ ኢስታንቡል ከተማ ካቀኑ የጸጥታ ሰራተኞች መካከል የአልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማን የቅርብ ጠባቂ ይገኝበታል። አብዱልአዚዝ ሙተሪብ የተባለው ጠባቂያቸው ልዑሉ በተጓዙባቸው የውጭ አገራት አብሯቸው ታይቷል። ተንታኞች ይኸን ሁሉ እያጣቀሱ ያለ እርሳቸው እውቅና የኢስታንቡሉ ድርጊት ተፈፅሟል ለማለት ሲቸግራቸው ይስተዋላል። ውጭ ጉዳይ ምኒስትር አደል አል-ጁበይር ግን "ከእርሳቸው ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው እና በዚህ ጉዳይ የተሳተፉ ሰዎች የሉም። በተለያየ ጊዜ የእርሳቸው ጥበቃ የነበሩ የተወሰኑ ሰዎች ምስሎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን በጥበቃ ላይ የሚሰማሩ ሰራተኞች ወደ ተለያዩ ባለሥልጣናት ይዘዋወራሉ። ስለዚህ ምስል ስላለ ብቻ የተለየ ግንኙነት አላቸው ማለት አይደለም። አልጋ ወራሹ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። የሚያውቁት ነገር የለም። የደህንነት መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንኳ የሚያውቁት ነገር የለም። ይኸ ግለሰቦች የተሰጣቸውን ግዴታ እና ኃላፊነት ተላልፈው የፈጸሙት ነው። ጀማል ኻሾግጂን በቆንስላው ሲገድሉ ስህተት ፈፅመዋል። ይኸንንም ሊሸፋፍኑ ሞክረዋል" ሲሉ አስተባብለዋል።
ወደ ሥልጣን ሲመጡ ምዕራባውያኑ ተራማጅ እያሉ ያሸረገዱላቸው የ33 አመቱ የልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን አመራር አገሪቱን ወዴት እየመራት እንደሆነ እርግጠኝነት የጎደላቸው ብዙ ናቸው። እርሳቸው የአገሪቱን ቁልፍ የሥልጣን እርከኖች በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ለደኅንነቴ እሰጋለሁ ብሎ የተሰደደው ኻሾግጂ በተራማጅነታቸው ጥርጣሬ ባይገባውም ከጊዜ ወደ ጊዜ አምባገነን መሆናቸውን እየጠቀሰ በብርቱ ተችቷቸዋል። በተራማጅነታቸው ጥያቄ እንደሌለው የተናገረው ኻሾግጂ " ነገር ግን ሥልጣንን ሁሉ ጠቅልለው በእጃቸው እያስገቡ ነው። ለትችት መተንፈሻ ቦታ እንዲኖር የሳዑዲ ልሒቃን፣ የሳዑዲ ሚዲያ ክርክር እንዲያደርጉ ቢፈቅዱ ለእርሳቸውም ይበጃል። ይኸ አገሪቱ እያለፈችበት ለሚገኘው ለውጥ እጅግ አስፈላጊ ነው። ዛሬ እርሳቸው የሚያደርጉትን ቀድሜ በመጠየቄ አርታኢ ሖኜ እሰራበት ከበረው ጋዜጣ ተባርሪያለሁ። ሴቶች ማሽከርከር እንዲፈቀድላቸው፤ ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገባቸውን ቦታ እንዲያገኙ የሐይማኖት ልሒቃኑ ሥልጣን እንዲገደብ ጥሪ አቅርቢያለሁ። እርሳቸው እያደረጉ ያለው ያንን ነው። እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ይሁን እና የሁላችንንም አስተዋፆዖ የሚፈልግ እጅግ ጠቃሚ ለውጥ ነው። ማንም በዚህ ምክንያት ሊታሰር አይገባም" ሲል ተናግሮ ነበር።
የእስር ነገር ከተነሳ ልዑሉ ሥልጣን በተቆናጠጡ ማግሥት በሙስና ተጠርጥረው ከታሰሩ የሳዑዲ ልዑላን እና ከበርቴዎች መካከል ዛሬም ያልተፈቱ በርካታ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ሼክ መሐመድ አልአሙዲ ይገኙበታል። መልከ መልካሙ ልዑል በነዳጅ ዘይት ንግድ ላይ ጥገኛ ለሆነው ምጣኔ ሐብት አማራጭ ለመፈለግ በመነሳታቸው፤ በሴቶች ላይ ተጥለው የነበሩ ገደቦችን በማንሳታቸው እና የሐይማኖት ልሒቃንን ሚና በመገደባቸው ቢወደሱም የሚወቀሱባቸው በርካታ ናቸው። የሊባኖሱ ጠቅላይ ምኒስትር ሳድ ሐሪሪ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ባቀኑበት የስራ መልቀቂያ ማስገባታቸው በልዑሉ በመታገታቸው ነው የሚሉ ትንታኔዎች ዘግየት ብለው ይሰሙ ጀምረዋል። አገራቸው ከትንሺቱ ኳታር በገባችበት ቅራኔ ከክፍለ አኅጉሩ እንድትገለል በተደረገው ጫናም እጃቸው እንዳለበት ይነገራል። የከፋው ግን የየመን አበሳ ነው። ሳዑዲ አረቢያ በግንባር ቀደምትነት በምትመራው የየመን ጦርነት በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ ከ40 ሺህ በላይ ቆስለዋል። ቀድሞም ደሐ የነበረችው የመን እነ ሳዑዲ አረቢያ እና አጋሮቿ ከአሜሪካ፣ ጀርመን እና ብሪታኒያ በሚሸምቱት የጦር መሳሪያ በደረሰባት ውርጅብኝ ጭርሱን ደቃለች። መጣ ሔደት የሚለው የኮሌራ ወረርኝ ያምሳታል፤ 8.4 ሚሊዮን ዜጎቿ ከጠኔ አፋፍ ቆመዋል። ይኸ ሁሉ ሲሆን ዓለም አንዳች ነገር ማድረግ አልቻለም።
የ60 አመቱ ጀማል ኻሾግጂ ላለፉት አርባ ገደማ አመታት ጋዜጠኝነትን ሙያው አድርጎ ኖሯል። በ1990ዎቹ ከኦሳማ ቢን ላደን ጋር ግንኙነት ነበረው። ቢን ላደን የአል-ቃይዳ መሪ ከመሆኑ በፊትም ሆነ በኋላ ቃለ-መጠይቅ አድርጎለታል። አልዋታን እና አልአረብ ለተባሉ መገናኛ ብዙኃን በኃላፊነት ሰርቷል። በንጉሳዊው መንግሥት ውስጥ ቁልፍ ሥልጣን ላይ ለሚገኙ የአል-ሳዑድ ቤተሰቦች አማካሪነት ሆኖ ያውቃል። ከንጉሳዊው ሥርዓተ-መንግሥት አፈንግጦ ተቃዋሚ የመሆን ዕቅድ ግን አልነበረውም። ሥርዓቱ ራሱን ለማሻሻል የሚያደርጋቸውን አሊያም ጥረቶች ይደግፍ ነበር። ከትውልድ አገሩ የተሰደደው ከአንድ አመት ገደማ በፊት እስርን ፈርቶ እንደነበር በአደባባይ ተናግሯል። ዛሬ የጀማል ካሾግጂ እጮኛ፣ የሥራ ባልደረቦቹ እና በሞቱ ሳዑዲ አረቢያን የሚያብጠለጥሉ ምዕራባውያን አስከሬኑ ከወዴት እንዳለ ለማወቅ መወትወት ይዘዋል። ለጊዜው ከሞቱ ጀርባ ያለው ምስጢር ባይታወቅም ሳዑዲ አረቢያ ግን ትችት እየዘነበባት ነው።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ