1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምዕራብ ወለጋ፤ በፀጥታ ችግር የተዘጋዉ መንገድ ዳግም ሥራ ጀመረ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 13 2015

ለአራት ወራት ተቋርጦ የነበረው የካማሽ ዞንና ምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ መስመር የትራንስፖርት አገልግሎት ስራ መጀመሩ ተነገረ። መንገዱ በመዘጋቱ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ከ3 ወራት በኃላ ተሽከርካሪዎች ወደ ዞኑ መግባታቸውን እና የምርት ዋጋ ላይ አሁንም ጭማሪ መታየቱንም ተናግረዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4SpnH
 Kamashi town in Benishangul Gumuz region Ethiopia
ካማሺ ወረዳ ምስል Negassa Dessalegn/DW

ይሁንና መንገዱ ከስጋት ነጻ እስኪሆን ድረስ በእጀባ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተነግሯል

አራት ወራት ለሚሆን ጊዜ ተቋርጦ የነበረው የካማሽ ዞን እና ምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ  መስመር የትራንስፖርት አገልግሎት ስራ መጀመሩን የካማሺ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡ መንገዱ በመዘጋቱ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች  ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎ እንደነበር ገልጸዋል፡፡  ከ3 ወራት በኃላ ተሽከርካሪዎች ወደ ዞኑ መግባታቸውን  እና የምርት ዋጋ ላይ አሁንም ጭማሪ መታየቱንም ተናግረዋል፡፡ ከሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም አንስቶ የትንስፖርት አገልግሎት የተጀመረው በእጀባ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገልጸዋል፡፡ ሸቀጥ እና የተለያዩ ምርቶች መግባቱን የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ አረጋግጠዋል፡፡ ከምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደር በኩል ስለ መንገድ ትራንስፖርት እና ጸጥታ ሁኔታ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረኩት ጥረት ስልካቸው ባለማንሳታቸውን አልተሳካም፡፡

 Kamashi town in Benishangul Gumuz region Ethiopia
ካማሺ ወረዳ ምስል Negassa Dessalegn/DW

የምዕራብ ወለጋ ዞን እና ካማሺ ዞን የሚያገናኙ መንዶች በብልሽት እና ጸጥታ ችግር ምክንያት የመጓጓዣ አገልግሎት ከየካቲት ወር 2015 .ዓም ወዲህ መቋረጡን የካማሺ  ከተማ ነዋሪዎች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ይህም የሰዎችን እንቅቃሴን መገደብን ጨምሮ በመሰረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ ላይ አሉታዊ ተጽኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡ የካማሺ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አስካለች እመኑ ከባለፈው ሳምንት አርብ አንስቶ ተሽከርካሪዎች እና መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ወደ ዞኑ መግባት መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡ ሆኖም በጤፍ እና ልዩ ልዩ ምርቶች ዋጋ ላይ አሁንም የዋጋ ጭማሪ እንደሚስተዋል ገልጸው መንገድ ተዘግቶ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ የገቡ ምርቶች ለማህበረሰቡ በቂ አለመሆናቸውንና ዘላቂ መፍትሄ የዞኑ አስተዳደር እንዲያበጅም ጠይቀዋል፡፡

በካማሺ እና ነጆ ከተማ መስመር አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ከተወሰኑት ኪ.ሜትሮች በስተቀር የትራንስፖርት አገልገሎት በእጀባ እየተሰጠ እንደሚገኝ ሌላው ስመ አይጠቀስ ያሉ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ ከ3 ወራት በላይ ለሚሆን ጊዜ ተቋርጦ በነበረው የየብስ ትራንስፖርት አገልገሎት ምክንያት የምርት ዋጋ በእጥፍ ጨምሮ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በትናትናው ዕለትም ተሽከርካሪዎች ወደ አካባቢው መግባታቸውን አክለዋል፡፡ አሁንም አገልግሎቱ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴው እንዲመለስ የጸጥታ ችግሩ መቀረፍ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ 

 Kamashi town in Benishangul Gumuz region Ethiopia
ካማሺ ወረዳ ምስል Negassa Dessalegn/DW

የካማሺ ዞን የኮሙኒኬሽን መምሪያ ተወካይ የሆኑት አቶ ጀርሞሳ ተገኝ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ የተቋረጠው ከመጋቢት ወር ጀምሮ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመንገዱ መዘጋት ችግር ሳቢያ በምርት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቶ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ምርት እና የመጓጓዣ አገልግሎት በእጀባ መስጠት መጀመሩን አብራርተዋል፡፡ የገበያ ዋጋ ለማረጋጋትም መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች  ለተከታታይ ሶስት ቀናት በቦታው መድረሳቸውን ገልጸው መንገዱ ከስጋት ነጻ እስኪሆን ድረስ በእጀባ አገልግሎት እንደሚሰጥም አክለዋል፡፡

በከማሺ እና አካባቢው የነበረው የጸጥታ ችግር ከባለፈው ዓመት ግንቦት 2014 ዓ.ም ጀምሮ መሻሻሉንና በዞኑ የተለያዩ ተቋማት ወደ ስራ መግባታቸውን ሲዘገብ ቆይተዋል፡፡ በካማሺ እና ምዕራብ ወለጋ አዋሳኝ ቦታዎችና ሌሎች  ስፍራዎችን በልማት ለማስተሳሰር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ኦሮሚያ የሁለቱ ክልሎች  የሰላም እና ልማት የጋራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ተቋቁሙ በስራ ላይ ይገኛል፡፡   

 

ነጋሳ ደሳለኝ

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ