ሜርክል በጀርመን ከፍተኛ የተባለዉን ሜዳልያ ተሸለሙ
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 10 2015የቀድሞዋ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በጀርመን ከፍተኛ የተባለዉን ሜዳልያ ተሸለሙ። ሜርክል ይህን ከፍተኛ ሜዳልያ ሲቀበሉ በጀርመን ታሪክ ሦስተኛዋ ዜጋ ሆነዋል። አንጌላ ሜርክል የጀርመን እጅግ ከፍተኛ የተባለዉን ሽልማት ያገኙት በ 16 ቱ ዓመት የመሪነት ዘመናቸዉ ላሳዩት ጠንካራ ፖለቲካዊ ርምጃ እና ዉሳኔዎቻቸዉ መሆኑ ተነግሯል። «ታላቁ መስቀል» የሚል ስያሜ ያለዉ ይህ የጀርመን ከፍተኛ ሽልማት ከጎርጎረሳዉያኑ 1951 ዓ.ም ጀምሮ በጀርመን "በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ ወይም በምሁራዊ መስክ ለተመዘገበ ስኬት ለጀርመናውያን ብሎም ለውጭ ዜጎች" የሚሰጥ ከፍተኛ ሽልማት ነው። ከሜርክል በፊት ይህን ሽልማት ያገኙት የመጀመርያዉ የጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ወይም የምዕራብ ጀርመን መራሄ መንግሥት ኮናርድ አደናውር ሲሆኑ ሁለተኛዉ ተሸላሚ ምስራቅ እና ምዕራብ ጀርመን ወደ አንድነት እንዲመጡ ፈር የቀደዱ እና ከጀርመን መገበያያ ገንዘብ ማርክ የአዉሮጳ መገበያያ ገንዘብ ይሮ እንዲመጣ ዉሳኔ ያሳለፉት መራሒ መንግሥት ሂልሞት ኮል ናቸዉ። ትናንት ሦስተኛዋ ተሸላሚ የሆኑት የቀድሞዋ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፤ በጦርነት የተፈናቀሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሶርያዉያን ወደ ጀርመን እንዲገቡ እና እንዲረዱ መፍቀዳቸዉ እንዲሁም በጃፓን የፊኩሺማ የአቶም ኃይል ማብላልያ ከፈነዳ በኋላ በጀርመን የአቶም ኃይል ማመንጫ ማዕከላትን እንዲዘጉ መወሰናቸዉ ከሰርዋቸዉ ዋንኛ ፖለቲካዊ ዉሳኔዎች መካከል ይጠቀሳሉ። ይሁንና ሩስያ ዩክሬንን መዉረርዋን ተከትሎ ጀርመን ዉስጥ የኃይል አአርቦት በመቀነሱ አልያም በመወደዱ፤ የአቶም ኃይል ምንች መዘጋቱን የሚቃወሙ ዜጎች በርካታ ሆነዋል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ