1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ያልተቋጨ ሥምምነት፣ የተቋረጠ የሰላም ንግግር፣ ያልተጀመረ ድርድር፤ ማይክ ሐመር ይሳካላቸዋል?

Eshete Bekele
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 1 2016

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሰው ግጭት በክረምት ቀዝቀዝ ብሎ የነበረ ቢሆንም ባለፉት ሦስት ወራት በኃይል ተባብሷል። ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ግጭቶቹ በድርድር እንዲቋጩ ግፊት ያደርጋሉ። ሐመር ያልተቋጨ ሥምምነት፣ የተቋረጠ የሰላም ንግግር፣ ያልተጀመረ ድርድር ይጠብቃቸዋል።

https://p.dw.com/p/4a2Zi
የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር የኢትዮጵያ መንግሥት እና ህወሓት የተፈራረሙትን ግጭት የማቆም ሥምምነት ተግባራዊ ማድረግ እንዲቀጥሉ ግፊት ለማድረግ ወደ አዲስ አበባ ይጓዛሉ። ሐመር አዲስ አበባ ሲደርሱ በአማራ እና በኦሮሚያ የበረታው ግጭት በድርድር እንዲፈታ ጭምር ግፊት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። ምስል Facebook

ያልተቋጨ ሥምምነት፣ የተቋረጠ የሰላም ንግግር ያልተጀመረ ድርድር፤ ማይክ ሐመር ይሳካላቸዋል?

በኢትዮጵያ ከሕዳር 15 እስከ 21 ቀን 2016 ባለው አንድ ሣምንት 31 የፖለቲካ ግጭት ኩነቶች እንደተመዘገቡ የኢትዮጵያ ፒስ ኦብሰርቫቶሪ መረጃ ያሳያል። በእነዚህ የፖለቲካ ግጭቶች 137 ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት ተደርጓል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተሰነዘሩ ጥቃቶች ምክንያት 59 ሰዎች ተገድለዋል። አብዛኞቹ ግጭቶች በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የተከሰቱ ናቸው።

ይኸ ፕሮጀክት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚከሰቱ የትጥቅ ግጭቶች ቦታ እና ጊዜ እየተከታተለ በሚሰንደው አክሌድ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የተቋቋመ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ውጊያ በገጠሙበት በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት ባለፈው ዓመት የመቀነስ አዝማሚያ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ባለፉት ወራት ተመልሶ መጨመሩን የአክሌድ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ብራደን ፉለር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ብራደን ፉለር “በተመዘገቡ አውደ ውጊያዎች፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች እና ባስከተሉት ሞት ብዛት በጥቅምት ወር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። በሕዳር በትንሹ ቢቀንስም በኦሮሚያ ብዙ ግጭት ከተመዘገበበት ከ2022 ጋር የሚነጻጸር እና ከፍተኛ የሚባል ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በመንግሥት እና ራሳቸውን ፋኖ ብለው በሚጠሩ ታጣቂዎች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ አምስት ወራት ተቆጥረዋል። በግጭቱ ምክንያት በአማራ ክልል ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል። “ለጥቂት ወራት ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም በሰኔ እና ሐምሌ ገደማ ቀንሷል” ያሉት ብራደን ፉለር በመስከረም፣ ጥቅምት እና ኅዳር ወራት ተመልሶ መጨመሩን አስረድተዋል።

የጥይት ቀልህ
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሰው ግጭት በመስከረም፣ ጥቅምት እና ሕዳር ወራት ጭማሪ እንዳሳየ አክሌድ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መረጃ ያሳያልምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

በቆዳ ስፋትም ይሁን በሕዝብ ብዛት ከኢትዮጵያ ቀዳሚ በሆኑት በሁለቱ ክልሎች የበረታውን ውጊያ ለማቆም ከመንግሥት በኩል የሚደረገው ጥረት ግን የተለያየ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሁለት ዙር ባደረጓቸው የሰላም ንግግሮች ግጭቱን ለማቆም ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ አቶ ሬድዋን ሑሴን እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ ድሪባ ኩምሳ የተሳተፉበት ሁለተኛው ዙር የሰላም ንግግር ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት ነበር። የሰላም ንግግሩ ከከሸፈ በኋላ ሁለቱም ወገኖች እርስ በርስ ሲካሰሱ በኦሮሚያ ያለው ግጭት ዳግም አገርሽቶ ወደ አሰቃቂነቱ ተመልሷል። 

በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ከተማ ከሁለት ሣምንታት በላይ የተደረገውን “የሰላም ንግግር” የታደሙት በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ማይክ ሐመር “በአጭር ጊዜ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል ብሎ መናገር ከባድ ነው” የሚል አቋም አላቸው።

ከአንድ ሣምንት ገደማ በፊት በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት ሐመር በታንዛኒያው የሰላም ንግግር መሻሻሎች መኖራቸውን ቢገልጹም “መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ወገኖች ለማመቻቸመች መዘጋጀት እና ግጭት መፍትሔ እንደማይሆን ለመወሰን ቁርጠኛ መሆን አለባቸው” ሲሉ ተደምጠዋል። ልዩ ልዑኩ ሁለቱ ወገኖች “ለራሳቸው እና ከፍ ሲልም ለሕዝባቸው ጥቅም የተወሰኑ ዓላማዎቻቸውን ወደሚያሳካ የፖለቲካ ንግግር መግባት ጠቃሚ ነው” ብለው ነበር።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ እና ምክትላቸውን እስከ ታንዛኒያ “መውሰድ ለጉብኝት አልነበረም” የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ሕዝቅኤል ገቢሳ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በዳሬ ሰላም በተደረገው ንግግር ወደ ሥምምነት ተቃርበው እንደነበር እምነት አላቸው።

“ድርድሩ በወታደሮቹ አልቆ ነበር። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተስማምተው ነበር” የሚሉት ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል “ነገር ግን እዚያ ከደረሱ በኋላ የሆነ ነገር አለ” ሲሉ ልዩነት ሳይፈጠር እንዳልቀረ ተናግረዋል። “ብዙ ሥምምነት ላይ የደረሱ ይመስለኛል” ያሉት ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ልዩነቶቻቸው ከ5 እስከ 10 በመቶ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደሚሆን አስረድተዋል።

የፋኖ አባላት በላሊበላ
በአማራ ክልል መንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ውጊያ ከገጠሙት የፋኖ ታጣቂዎች ጋር እስካሁን የሰላም ንግግርም ይሁን ድርድር አልተጀመረምምስል Mariel Müller/DW

እስካሁን በአማራ ክልል ከመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ውጊያ ከገጠሙ የፋኖ ታጣቂዎች ጋር በይፋ የተጀመረ የሰላም ንግግርም ይሁን ድርድር የለም። የአማራ ማህበር በአሜሪካ የአድቮኬሲ ዳይሬክተር ሆነ ማንደፍሮ አምባሳደር ማይክ ሐመር “ንግግር እንዲጀመር ግፊት እያደረጉ” መሆኑን እንደገለጹ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የአማራ ማህበር በአሜሪካ ከሌሎች የአማራ ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ከሚወተውቱ ግለሰቦች ጋር ከልዩ ልዑኩ በተገናኙበት ወቅት አምባሳደር ማይክ ሐመር “አዲስ አበባ በሚመላለሱበት ወቅት የመንግሥት ኃላፊዎችን በአማራ ክልል ያለው በጦርነት እንደማይፈታ እያስገነዘቧቸው” መሆኑን እንደገለጹላቸው አቶ ሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

አምባሳደር ማይክ ሐመር ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች “በአማራ ክልል የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያነሳ” መጠየቃቸውን በአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ተናግረዋል። መገናኛ ብዙኃን በክልሉ መንቀሳቀስ እንዲፈቀድላቸው እና  የተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ወደ ሥራ እንዲመለስ ጭምር ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለጹት ሐመር “ለአማራ ሕዝብ ፋይዳ ያላቸው እና ለውጊያ መነሾ የሆኑ በጣም ከባድ ታሪካዊ ጉዳዮችን በንግግር እና ሰላማዊ ውይይት መፍትሔ እንዲፈልግ አበረታተናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

አምባሳደር ማይክ ሐመር ወደ በዚህ ሣምንት ወደ አዲስ አበባ ሲያቀኑ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ግጭቶች በድርድር መፍትሔ እንዲበጅላቸው ጭምር ግፊት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል። ማይክ ሐመር እና ሀገራቸው አሜሪካ እንዲህ አይነት ግፊት ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው አይደለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት በደቡብ አፍሪካ የተፈራረሙትን ግጭት የማቆም ሥምምነት ተግባራዊ ማድረግ እንዲቀጥሉ ግፊት እንደሚያደርጉ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። የትግራይ ኃይሎች የታጠቋቸውን የጦር መሣሪያዎች ማስፈታት፣ ተዋጊዎችን በትኖ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ማድረግ፣ የሽግግር ፍትኅ እና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ በፕሪቶሪያው ሥምምነት መሠረት ያልተጠናቀቁ የቤት ሥራዎች ናቸው።

የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት ሲፈረም ሬድዋን ሑሴን እና ጌታቸው ረዳ ተጨባብጠው የኬንያው ኡኹሩ ኬንያታ ያያሉ
በፕሪቶሪያ በተፈረመው ግጭት የማቆም ሥምምነት መሠረት “የጦር ወንጀሎች፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና ብርቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የፈጸሙ ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ያሉት ማይክ ሐመር “ይኸን እንዲያደርጉ ግፊታችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ለበአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ገልጸዋል።  ምስል SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

“የጦር ወንጀሎች፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና ብርቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የፈጸሙ ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ለመተባበር ዝግጁ ነን። ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን መክሰስ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኤርትራ መንግሥት ኃላፊነት ነው” ያሉት ማይክ ሐመር “ይኸን እንዲያደርጉ ግፊታችንን እንቀጥላለን” ሲሉ ለበአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ገልጸዋል።  

አምባሳደር ማይክ ሐመር በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ሆነው የተሾሙት ግንቦት 24 ቀን 2014 ነበር። ከሐመር በፊት በልዩ ልዑክነት ተሹመው የነበሩት ጄፍሪ ፌልትማን እና ዴቪድ ሳተርፊልድ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማቆም አልተሳካላቸውም። ሐመርም ሹመቱን ከአምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድ ሲረከቡ አሰቃቂው «ጦርነት መቼም አይቆምም» ተብለው ነበር።

የአፍሪካ ኅብረት፣ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት እና የአውሮፓ ኅብረትን ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር ያደረጉት ጥረት ሰምሮ ቢያንስ እሳት የሚተፉ አፈሙዞችን ጸጥ ማሰኘት ችለዋል። ቀድሞም ጦርነቱን ለማቆም የተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያልሰመረው “ከማይክ ሐመር በፊት በነበሩት ልዩ መልዕክተኞች ድክመት እና የዲፕሎማሲ ችግር” እንዳልሆነ የሚናገሩት  የፖለቲካ ተንታኙ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ገቢሳ “በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ እና የተዋጊዎቹ ሥነ ልቦና ለድርድር አይፈቅድም ነበር” ሲሉ አስረድተዋል።

“ጅቡቲ ተገናኝተው ነበር፤ ሞሪሺየስ ላይ ተገናኝተው ነበር። ነገር ግን ሁለቱም ጦርነቱን እናሸንፋለን የሚሉበት ደረጃ ስለነበሩ አልተስማሙም” የሚሉት ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል “ፕሪቶሪያ ሲደርሱ ሁለቱም ደክመው ነበር” ሲሉ የጦርነቱ ብርታት ሁለቱንም ኃይሎች ወደ ድርድር እንደገፋ ያስረዳሉ።  

ዴቪድ ሳተርፊልድ
ማይክ ሐመር በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ሆነው የተሾሙት ዴቪድ ሳተርፊልድን በመተካት ነበርምስል picture alliance/AP Photo/B. Hussein

“በአማራ ክልልም በኦሮሚያም ያለው መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር ነው። ሁለቱም ተዋጊዎች ምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት? የሚለው ነው የሚወስነው” የሚሉት ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል የግጭቶቹ መደራረብ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በሀገሪቱ ምጣኔ ሐብት በተለይም በሕዝቡ ላይ ያሳደሩት ጫና ተፋላሚ ኃይሎችን ወደ ንግግር ሊመራ እንደሚችል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በአክሌድ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ብራደን ፉለር “በኦሮሚያ ለረዥም ጊዜ ግጭት ሲካሔድ በመቆየቱ ኹከት የሥርዓቱ አንድ አካል ሆኗል። መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተደጋጋሚ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ ተብለው ይከሰሳሉ። የክንዋኔያቸው አካል ነው። ገንዘብ የሚያገኙበት አንድ ስልት ነው። ስለዚህ እንዲያቆሙ የሚያደርጋቸው በቂ ማበረታቻ የለም የሚል ሥጋት አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል። “አንዳቸው ሌላቸውን በወታደራዊ ኃይል ማሸነፍ አልቻሉም። ሁሉም ሰልችቶታል። እርግጥ ነው ያ አንድ ማበረታቻ ነው” ያሉት ብራደን ፉለር“ እጅግ በጣም ፈታኝ” እንደሚሆን እምነታቸው ነው።

በአማራ ክልል ለተቀሰቀሰው ግጭት መነሾ የሆኑ ችግሮች «መሠረታዊ ሽግግር» የሚፈልጉ ናቸው የሚሉት አቶ ሆነ ማንደፍሮ በበኩላቸው የአሜሪካው ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር የኢትዮጵያ መንግሥት እና የፋኖ ታጣቂዎችን ወደ ድርድር መምራት ሊቸገሩ እንደሚችሉ ያምናሉ። “ችግሮቹ ሥር የሰደዱ ስለሆኑ እና ሕዝቡም የሚጠይቀው መሠረታዊ ለውጥ” መሆኑን የገለጹት አቶ ሆነ ጉዳዩ ከዚህ ቀደም ማይክ ሐመር ካመቻቿቸው ንግግሮች የተለየ እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ ሆነ በአማራ ክልል ያለው ቀውስ በድርድር እንዲፈታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ላይ “አሜሪካ ምን ያክል ጫና እያደረገች ነው?” የሚለው ጉዳይ “ትልቅ ለውጥ የሚፈጥር” እንደሆነ ያምናሉ። ይሁንና አሜሪካ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ባሉ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ መንግሥት ምጣኔ ሐብታዊ ድጋፍ ለማድረግ ያሳየችው ፈቃደኝነት አቶ ሆነን የሚያሳስብ ነው። ብራደን ፉለር ግን በሁለቱም ወገኖች በኩል የተሰነቀ «የማሸነፍ ተስፋ» ለሰላም ንግግርም ሆነ ለድርድር እንቅፋት እንደሚሆን ገልጸዋል። 

“በአማራ ክልል ለድርድር አንድ ማዕከላዊ ሰው የማግኘት የተወሰነ ፈተና አለ” የሚሉት የአክሌድ ከፍተኛ ተመራማሪ ብራደን ፉለር “ግጭቱ ረዥም ጊዜ አላስቆጠረም። ፋኖም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድር ከመዘጋጀታቸው በፊት የበለጠ አካባቢ ለመቆጣጠር ወይም አንዳቸው ሌላውን ለማሸነፍ ተስፋ ያደርጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ