1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሕደረ ዜና፣ የቻይናና የአሜሪካኖች ሽኩቻ

ሰኞ፣ ሰኔ 5 2015

ሁለቱ ልጣቸዉ የራሰ-ጉርጓዳቸዉ የተማሰ አዛዉንታት እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በምዕራባዉያኑ ይትበሐል የቫለንታይን (የፍቅር) ቀን በወርቅ፣ጎራዴና-ዊልቸር የስጦታ ልዉዉጥ ለበጎ ይሁን ለመጥፎ የመሰረቱት ወዳጅነት ከ75 ዘመን በላይ ንቅንቅ አላለም።

https://p.dw.com/p/4SUFz
Saudi Arabien | Antony Blinken in Riad
ምስል Ahmed Yosri/AP/picture alliance

የቻይናና የዩናይትድ ስቴትስ ሽሚያ በመካከለኛዉ ምስራቅ

የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ባለፈዉ ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ ያደረጉት ጉብኝት እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ «የተሳካ» ተብሎለታል።የሳዑዲ አረቢያ ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎች ግን፣ ከአሜሪካዉ ትልቅ ዲፕሎት ጉብኝትና ዉይይት ይልቅ ከፍተኛ ሽፋን የሰጡት አልጄሪያዊ-ፈረንሳዊዉ ዕዉቅ የእግር ኳስ ተጫዋች ከሪም ቤንዝማ ለሳዑዲ አረቢያዉ ኢትሐድ ክለብ ለመጫዎት ሳዑዲ አረቢያ ለመግባቱ ነበር።ብሊንከን ከሪያድ በወጡ በሳልስቱ የአሜሪካዋ የረጅም ጊዜ ጥብቅ ወዳጅ፣ ስልታዊ አጋር ሐገር ሳዑዲ አረቢያ የአረብ-ቻይናን የንግድ ስብሰባን አስተናገደች።በሪያድ የኢራን ኤምባሲ ዳግም የተከፈተዉ ብሊንከን ሪያድ ከመግባታቸዉ አንድ ቀን ቀድሞ ነበር።ኢራንና አሜሪካ ጠላቶች ናቸዉ።ኢራንና ሳዑዲ አረቢያን ያስታረቅች ቻይና ናት።ቻይና እስራልና ፍልስጤሞችን ለማስታረቅ አንድ ሁለት እያለች ነዉ።መካከለኛዉ ምስራቅ የዋሽግተን-ቤጂንጎች መሻሚያ ወይስ ቻይና ሲገሰግስ-አሜሪካ ይኮስስ እንበል ይሆን? ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

ፕሬዝደት ፍራንክሊን ዲ ሩዘቬልትም ሆኑ ንጉስ አብዱል አዚዝ ኢብን ሳዑድ እድሜያቸዉ ገፍቶ፣ጤናቸዉ ከፍቶ፣ ጉልበታቸዉ ከድቷቸዉ ነበር።ሁለቱ ልጣቸዉ የራሰ-ጉርጓዳቸዉ የተማሰ አዛዉንታት  እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) በምዕራባዉያኑ ይትበሐል የቫለንታይን (የፍቅር) ቀን በወርቅ፣ጎራዴና-ዊልቸር የስጦታ ልዉዉጥ ለበጎ ይሁን ለመጥፎ የመሰረቱት ወዳጅነት ከ75 ዘመን በላይ ንቅንቅ አላለም።

የቻይና-አረብ የንግድ ስብሰባ
የቻይና-አረብ የንግድ ስብሰባምስል Ahmed Yosri/REUTERS

የሩዘቬልት ብልሐት፣ የቢን ሳዑድ ትዕግስት ሰፊ፣ሐብታም፣የሙስሊሞች ቅዱስ ስፍራይቱን ሐገር ከአሜሪካኖች ዕቅፍ ሲዶል፣ ልዕለ ኃያልቱ ሐገር በፋንታዋ ለሪያድ ገዢዎች ሙሉ ከለላና ጥበቃ እየሰጡ የኮሚንስቶችን ግፊት፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ፈላጊዎችን ጥያቄ፤ የአዉሮጶችን ጉጉት ሳይቀር በየዘመኑ አክሽፈዉታል።

ባለፈዉ ሳምንት ሪያድን የጎበኙት የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከንና የሳዑዲ አረቢያ አቻቸዉ ልዑል  ፈይሰል ቢን ፈርሐን አል ሳዑድ ጋዜጠኞች ፊት የተለዋወጧቸዉ ቃላት ግን የሁለቱ ሐገራት የዘመናት ወዳጅነት ጥብቀት መላላቱን መስካሪ ነዉ።«ሳዑዲ አረቢያ ከዋሽግተንና ከቤጂንግ አንዱን እንድትመርጥ አትገደድም» አሉ ብሊንከን-እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ ለስለስ ብለዉ ።የሳዑዲ አረቢያዉ አቻቸዉ አፀፋ «ሳዑዲ አረቢያ ከዩናይትድ ስቴትስና ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት «የዜሮ-ድምር ዉጤት አይደለም» የሚል ነበር።

ባለፈዉ ግንቦት 7 የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የፀጥታ አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ሳዑዲ አረቢያን ጎብኝተዉ ነበር።ብሊንከን ሳዑዲ አረቢያን ሲጎበኙ ባንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ሁለተኛዉ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለስልጣን መሆናቸዉ ነዉ።

የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሪያድ የገቡት ከ2016 ጀምሮ አይና ናጫ የነበሩት ሪያድና ቴሕራን ከየመን እስከ ሶሪያ፣ ከሊባኖስ እስከ ፍልስጤም-እስራኤል፣ ከሊቢያ እስከ ኢራቅ መናጨት-መቧጨቃቸዉን አቁመዉ ወዳጅነታቸዉ በደመቀበት ወቅት፣ በሪያድ የኢራን ኤምባሲ ዳግም በተከፈተ ማግስት ነዉ።ብሊንከን ለሪያድ ጉብኝታቸዉ አንድም ጥሩ ቀን አልመረጡም ሁለትም የመንግስታቸዉን ንዴት፤ ቁጭት ምናልባት ቁጣን አልደበቁም።

«ዩናይትድ ስቴትስ እና ሳዑዲ አረቢያ ከባሕረ ሰላጤዉ ማሕበር (GCC) ጋር በመሆን ኢራን ለአሸባሪዎችና ለነዉጠኛ ሸማቂ ቡድናት የምትሰጠዉን ድጋፍ፣በዓለም አቀፍ ዉኃ ላይ የሚጓዙ ነዳጅ ማመለሻ መርከቦችን ማገትና የኑክሌር ሥጋት መፍጠሯን  ጨምሮ አካባቢዉን ማወኳን አተኩረዉበታል።ዩናይትድ ስቴትስ ይሕን አደገኛ ርምጃ ለመከላከል በኢኮኖሚያዊ ጫና፣ጥቃትን በመከላከልና ጠንካራ የመከላከያ ትብብርን በማዳበር የተደገፈ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል ብላ ታምናለች።»

የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከሳዑዲ አረቢያዉ አልጋወራሽ ጋር
የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ከሳዑዲ አረቢያዉ አልጋወራሽ ጋርምስል Saudi Royal Court/REUTERS

ዋሽግተኖች «የእስራኤል ቀንደኛ ጠላት፣የፍልስጤም፣ የሊባኖስ ደፈጣ ተዋጊዎች፣ የሁቲዎች አስታጣቂ፣የአሸባሪዎች ደጋፊ፣ የኑክሌር ቦምብ ለመስራት የምታደባ፣ የደማስቆ ተባባሪ፣ የሞስኮ ወዳጅ፣ የኢሺዓ ሐራጥቃ አዛማች» እያሉ የሚወነጅሉ፣የሚቀጡ-የሚቆነጥጧት ኢራን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር መወዳጀቷን አይፈቀዱትም።

የሁለቱ የመካከለኛዉ ምሥራቅ ሐብታም ኃያላን ጠብ የለዘበዉ በቻይኖች ሸምጋይነት መሆኑ ደግሞ ታዛቢዎች እንዳሉት ለዋሽግተኖች ሲበዛ አበሳጭ ነዉ።የሳዑዲ አረቢያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ልዑል ፈይሰል ፈርሐን አል ሳዑድ የዕግዳቸዉን ማስጠንቀቂያ ብጤ መልዕክት መሸንቆጫ ቃላት አላጡም

«(ነገሮችን) ማረጋጋት ለመካከለኛዉ ምሥራቅ ጠቃሚ ነዉ።ለሁሉም ብዙ ጥቅም አለዉ።ይሁንና ለፍልስጤም ሕዝብ ሰላም የሚወርድበት መንገድ ካልተቀየሰ፣ ይሕን ፈተና ካላስወገደ ማንኛዉም መረጋጋት የሚኖረዉ ፋይዳ በጣም ትንሽ ነዉ።እንደሚመስለኝ ለፍልስጤም ሕዝብ ክብርና ፍትሕ የሚያጎናፅፍ የሁለት-መንግስታት መፍትሔ ገቢር የሚሆንበት ስልት ሊኖረን ይገባል።እንደሚመስለኝ ዩናይትድ ስቴትስም ጥረቶቹ መቀጠል አለባቸዉ የሚለዉን ሐሳብ ሳትጋራ አትቀርም።»

ብሊንከን በሪያድ የሚያደርጉትን ጉብኝት ከማጠናቀቃቸዉ በፊት የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን በስልክ አነጋግረዋል።የሁለቱ ባለስልጣናት የስልክ ዉይይት የፍልስጤም እስራኤሎችን የዘመናት ዉዝግብ መንካቱ እንደማይቀር ብዙዎች ያምናሉ።ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ባለፈዉ ዕሁድ በሰጡት መገለጫ እንዳሉት ግን ዉይይቱ ያተኮረዉ በኢራን የኑክሌር መርሐ ግብር ላይ ነበር።

«ከኢራን ጋር ከዚሕ ቀደም ወደተደረገዉ የኑክሌር ስምምነት መመለስ የኢራንን የኑክሌር መርሐ ግብር እንደማያስቆም በአፅንኦት ተናግሬያለሁ።እንዲያዉም ኢራን መካከለኛዉ ምስራቅና እስራኤል ድንበር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ለአሸባሪ ድርጅቶች ገንዘብ በጣም ብዙ ገንዘብ እንዲትሰጥ ያደርጋታል።ከኢራን ጋር የሚደረግ ማንኛዉም ስምምነት እስራኤልን ተገዢ እንደማያደርጋት በአጽንኦት ተናግሬያለሁ።መንግስተ-እስራኤል ከጥቃት ለመከላከል አስፈላጊዉን ነገር ሁሉ ማድረጋችንን እንቀጥላለን።»

የኔታንያሁ መልዕክት ከ1979 ጀምሮ የቴል አቪቭ፣ ኋላ የእየሩሳሌም ወይም የዋሽግተን አብያተ መንግስታትን የተፈራረቁባቸዉ ፖለቲከኞች ካሉና ካደረጉት የተለየ አይደለም።የኢራንን የኑክሌር መርሐ ግብር ለማስቆም በ2015 የተደረገዉ ስምምነት እንዲፈርስ ከእስራኤል ቀጥሎ ዋሽግተኖች ላይ ከፍተኛዉን ግፊት ያደረገችዉ ሳዑዲ አረቢያ ነበረች።አሁን ግን ቢያንስ በይፋ ሳዑዲ አረቢያ እራስዋን አቅባለች።ሳዑዲ አረቢያ ከእስራኤል-አሜሪካኖች ጉያ ፈቀቅ በማለትዋ የተደሰቱት የኢራን የበላይ መሪ አያቶላሕ ዓሊ ኻሜኔይ ከእስራኤል ይልቅ በምዕራባዉያን ላይ ነዉ ያነጣጠሩት።

«የኑክሌር መርሐ ግብራችንን እስካሁን ማስቆም አልቻሉም።ወደፊትም አይችሉም።የኑክሌር ጦር መሳሪያ መስራት ብንፈልግ የሚያግደን የለም።ይህን እነሱም ያዉቁታል።ስለዚሕ ኢራን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ልትሰራ ነዉ የሚሉት ማማኻኛ ዉሸት ነዉ።»

የኢራኑ የበላይ መሪ ዓሊ ኻሜኔይ
የኢራኑ የበላይ መሪ ዓሊ ኻሜኔይ ምስል Tasnim

ለእስራኤል ዙሪያ መለስ ድጋፍ የምትሰጠዉ ዩናይትድ ስቴትስም በዶናልድ ትራም ያስተዳደር ዘመን ስምምነቱን አፍርሳለች።ይሁንና ዩናይትድ ስቴትስ በፍልስጤምና እስራኤል መካከል ሰላም ለማዉረድ  ከ1948 ጀምሮ አደረገች የሚባለዉ የሰላም ጥረት እስካሁን እንደመከነ ነዉ።

በሰላም ጥረቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ወገኖች እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ የሚቀርበዉን ጥያቄም ዋሽግተኖች አልተቀበሉትም።ዘመን-መጥቶ ዘመን በሔደ ቁጥር የዋሽግተኖችን እርጥባን አንጋጠዉ የሚጠብቁት የፍልስጤም መሪዎች ሞስኮን እንደሁለተኛ አማራጭ ማየቱም ምንም አልፈየዳቸዉም።

ዋሽግተኖችን ለመጋፋት ያሁኑ ዘመን የፈቀደላቸዉ ሐብቱም፣ጉልበቱም፣ ተደማጭነቱም ያላቸዉ ቤጂንጎች ናቸዉ።ባለፈዉ ሚያዚያ ሳዑዲ አረቢያንና ኢራንን ካስታረቁ ወዲሕ ደግሞ የቤጂንጎች የማሸማገል ትዕግስት፣ብልሐትና ዝና በሰፊዉ እየናኘ ነዉ።

ሳዑዲ አረቢያና ኢራን በየመንና በሶሪያ ጦርነት በቀጥታ ወይም ተቀናቃኝ ተፋላሚዎችን በማስታጠቅ ይካፈላሉ።ከሊባኖስ እስከ ኢራቅ፣ ከሊቢያ እስከ ፍልስጤም አንጃዎች ተቀናቃኞችን ይደግፋሉ።ሁለቱ የመካከለኛዉ ምስራቅ ሰፋፊ ሐገራት ጠባቸዉን ካረገቡ በኋላ የመኖች የሰላም ጭላንጭል እያማተሩ ነዉ።ሶሪያዎች ከመሰረቱት ሊግ ዳግም ተቀላቅለዉ የሰላምና የብልፅግና መንገድን እየተለሙ ነዉ።

ለሁለቱም መሰረቱ የቤጂንጎች ሽምግልና ነዉ።ታዲያ! ፍልስጤሞች ቢሞክሩትስ? ኔታንያሁ ለዘመናት እንደለመዱት ከእየሩሳሌም የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎችን ሲወንጅሉና ኢራን ላይ ሲዝቱ ትናንት  ዕሁድ የፍልስጤሙ ፕሬዝደንት ማሕሙድ አባስ ወደ ቤጂንግ ለመጓዝ ለረመላሕ ላይ ሰነድ-ጓዛቸዉን ይሸክፉ ነበር።

የቻይናዉ ፕሬዝደንት ሺ ቺ ፒንግ አባስን ለማስተናገድ ፍልስጤምና እስራኤልን ለመሸምገል ሙሉ ፈቃደኝነታቸዉን አስታዉቀዋል።አባስ ነገ ማክሰኞ ቤጂንግ ይገባሉ።ትናንት ሪያድ-ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ የተከፈተዉ የአረብ ቻይኖች የንግድ ትብብር ስብሰባ ደግሞ ከነገወዲያ ሮብ ያበቃል።ስብሰባዉ የአረብ-ቻይኖችን የንግድ ልዉዉጥ ያጠናከረ፣ በቢሊዮናት ዶላር የሚቆጠር ስምምነትን ያፈራረመም ነዉ።የሳዑዲ አረቢያዉ የኃይል ሚንስትር ልዑል አብዱል አዚዝ ቢን ሰልማን እንዳሉት አረቦች ከቻይና ዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን ከገበያዋም መጠቀም ይፈልጋሉ።

«ነዳጅ ዘይትን በተመለከተ የቻይና የነዳጅ ዘይት ፍላጎት እየጨመረ ነዉ።እና ከነዚያ ፍላጎቶች የተወሰነዉን መያዝ አለብሕ።የኬሚካሉንም ጭምር።ቻይና ዉስጥ መወረት እንፈልጋለን።ድፍድፉን ዘይት ወደ ኬሚካል የመቀየር አማላይ ዕቅድም አለን።»

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁምስል Ronen Zvulun/REUTERS

ዋሽግተኖች ምን ብለዉ ይሆን?ሳዑዲ አረቢያ ልክ እንደ ኢራን ሁሉ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ተቋም ለማስገንባት አቅዳለች።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፈይሰል ቢን ፈርሐን አል ሳዑድ ለአሜሪካዉ አቻቸዉ ለአንቶኒ ብሊከን እንደነገሩት ሳዑዲ አረቢያቸዉ ለግንባታዉ በስም ያልጠቀሷቸዉ መንግስታት ወይም ኩባንዮች እያጫረቱ ነዉ።አሜሪካም ከፈለገች «መጫረት ትችላለች።» ብለዋል ሚንስትሩ።

ዋሽግተን-ብራስልሶች አፍሪቃን በቻይና እየተቀሙ ነዉ።የአዉሮጳ-አሜሪካ ተሻራኪዎች ባለፉት ጥቂት አመታት ከቶኪዮ እስከ ካምቤራ፣ ከሞልዶቫ እስከ ሶል ያሉ ተከታዮቻቸዉን በሞስኮ፣ቤጂንግ ፣ፒዮንግ-ዮንግ ቴሕራኖች ላይ ለማሳመፅ ወይም ለኪየቭ ድጋፍ ለማሰባሰብ ሲባትሉ ቤጂንጎች መካከለኛዉ ምስራቅን ከአሜሪካኖች እቅፍ መንጭቀዉ ለመዉሰድ እየተፍረመረሙ ነዉ።እኒያ አዛዉንት መሪዎች ባለቀ እድሜያቸዉ ግን ለማያልቅ ሐገርና ትዉልዳቸዉ የመሰረቱት ወዳጅነት በነበር የሚዘከርበት ዘመን ተቃርቦ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ 

ታምራት ዲንሳ