1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሊ፦ ወታደራዊ ኹንታው ቀነ ገደቡ ሊያከትም ነው

ቅዳሜ፣ መስከረም 2 2013

ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ማሊ ውስጥ ባለፈው ወር ግድም ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አድርጎ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ኹንታ በአስቸኳይ ሥልጣኑን ለሲቪል መንግሥት እንዲያስረክብ ጫና በርትቶበታል። የአካባቢው ሃገራት ወታደራዊ ኹንታው የተባለውን እንዲፈጽም ቀነ-ገደብ አስቀምጠውለታል። 

https://p.dw.com/p/3iLqz
Mali Bamako | EUTM | Armee
ምስል picture-alliance/dpa/Maxppp/N. Remene

በተስፋ እና በቀውስ መሀል የምትዋትተው ማሊ

ማሊ የዛሬ ስምንት ዓመት ተዘፍቃበት ወደነበረው ቀውስ ዳግም እንዳትመለስ ዓለም ሰግቷል። ለዚህ ደግሞ ሰበቡ በሀገሪቱ መፈንቅለ መንግሥት ያከናወነው ወታደራዊ ኹንታ በሚመሠረተው የሽግግር መንግስት መሪው እኔው ነኝ መኾን ያለብኝ ሲል ሽንጡን ገትሮ መከራከሩ ነው። ተቃዋሚዎች እና የአካባቢው ሃገራት የምጣኔ ሐብት ትብብር ኢኮዋስ የሽግግር መንግሥቱ ቢያንስ ለአንድ ዓመት መመራት ያለበት ከሲቪል ማኅበረሰብ በተመረጠ ፕሬዚደንት እና ጠቅላይ ሚንሥትር ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ለዚያም ቀነ-ገደብ አኑረዋል። እናስ ወታደራዊ ኹንታው ማስጠንቀቂያውን ያከብር ይኾን?   

የማሊ መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ሥልጣኑን ለሲቪል ጊዜያዊ መንግሥት እንዲያስረክቡ የተጣቸው ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ይቀራሉ። ወታደራዊ ኹንታው የሽግግር መንግሥቱን ወታደራዊ መኮንን እንዲመራው ይሻል። ተቃዋሚዎች እና የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የምጣኔ ሐብታዊ ማኅበር (ECOWAS) በበኩላቸው የለም በሲቪል ነው መመራት ያለበት ሲሉ በአቋማቸው ጸንተዋል። 

ማሊ ባማኮ የኮሎኔል አሲሚ ጎይታ አንጋቾች
ማሊ ባማኮ የኮሎኔል አሲሚ ጎይታ አንጋቾችምስል Reuters/M. Keita

የኢኮዋስ አባል ሃገራት መሪዎች ማሊ ውስጥ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኹንታ ክፍል የኾነው የሕዝብ ታዳጊ ብሔራዊ ኮሚቴ(CNSP) የስልጣን ርክክብ እንዲፈጽም ቀነ-ገደብ ያስቀመጡት እስከ ማክሰኞ ድረስ ነው። አባል ሃገራቱ ባሳለፍነው ሰኞ ኒያሚ፤ ኒጀር ውስጥ ባካኼዱት ስብሰባም ነበር የኢብራሂም ቦባካር ኪይታ መንግሥትን ባስወገደው ወታደራዊ ኹንታ ላይ ቀነ ገደቡን ለመስከረም 5 ቀን፣ 2013 ዓ.ም በሚል በስተመጨረሻ የወሰኑት። የኢኮዋስን ውሳኔ የማሊ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ጥምረት (ADEPM) ፓርቲ ፕሬዚደንት አቦባካር ሲዲኪ ፎምባ ስህተት ብለውታል። 

«የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማኅበረሰብ ኢኮዋስ እንደ አንድ የፖለቲካ መዝባሪ ነው የሚንቀሳቀሰው። ኢኮዋስ በማሊ ጦርነት ኹሉን ልቆጣጠር ባይነቱን ካጣ በኋላ የሲቪል መንግሥት በማለቱ ብቻ ዳግም ነገሮችን ማካካስ የሚችል ይመስለዋል። ማሊያውያን የኢኮዋስን ምርጫ አይቀበሉትም። የምንፈልገው ሀገራችን መልሶ መገንባት ነው። ለሽግግር መንግሥቱ ሲቪል ያስፈልጋል ስንል የዛሬ ስምንት ዓመት እንደነበረው ወደኋላ መመለስ እንደማለትም ነው።»

ፖለቲከኛው ይኽን ሲሉ፦ ማሊ ውስጥ የዛሬ ስምንት ዓመት የ40 ዓመት ጎልማሳ በነበረው ወታደራዊ መኮንኑ አማዱ ሃያ ሳኖጎ መሪነት የተፈጸመውን ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥት እና እሱን የተከተለውን የማሊ ቀውስ መጥቀሳቸው ነው። ማሊ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2012 ተከስቶ ከነበረው ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ በተለይ ሰሜናዊ ግዛቷ የአክራሪዎች እና አሸባሪዎች መፈንጫ ኾኖ ቆይቷል። 

የማሊ ወታደራዊ ኹንታ ክፍል የኾነው የሕዝብ ታዳጊ ብሔራዊ ኮሚቴ (CNSP) ስብሰባ ላይ
የማሊ ወታደራዊ ኹንታ ክፍል የኾነው የሕዝብ ታዳጊ ብሔራዊ ኮሚቴ (CNSP) ስብሰባ ላይ ምስል Getty Images/AFP/M. Cattani

ቤንቤሬ የተሰኘው ጦማረ ድረ ገጽ መድረክ ላይ የሚጽፈው ጋዜጠኛ አብዶላዬ ጒዊንዶ የኢኮዋስ ቀነ ገደብ ብሔራዊ ኮሚቴው ስለ ሽግግር መንግሥት ምሥረታ ለመምከር ጊዜ እንዲገዛ ያደርገዋል ብሏል። ኢኮዋስ ቀነ ገደብ በማስቀመጡ ወታደራዊ ኹንታው ላይ ጫና ሊያሳድር ይችላል የሚልም እምነት አለው።

«የኢኮዋስ ውሳኔ በምክክር መድረኩ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ወታደራዊ ኹንታው ለሲቪል ስልጣኑን ካላስረከበ በመቀጠል ጠንከር ያለ ማዕቀብ ሊኖር ስለሚችል ማለት ነው። የኢኮዋስ ማዕቀብን በመፍራትም ምናልባት አንዳንድ ሰዎች ከጀመሩት ነገር ሊታቀቡ አለያም ቢያንስ በሽግግር መንግስቱ ኃላፊነት ማማ ላይ ሲቪል እንዲወጣ ሀሳብ ሊያቀርቡ ይችሉ ይኾናል።»

የኢኮዋስ ጫና በበረታበት ኹኔታ ወታደራዊ ኮሚቴው ሐሙስ ዕለት ባማኮ ከተማ ውስጥ ከመምከሩ ቀደም ብሎ የሲቪል ሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት የሚጠይቊ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። 

ልል በኾነ መልኩ የተለያዩ ተቃዋሚዎችን ያቀፈው ቅንጅት በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ (M5-RFP) የተሰኘው ንቅናቄ አባላትን ፖሊስ በአስለቃሽ ጢስ ለመበተን ሞክሯል። ቅንጅቱ ካለፈው ሰኔ ወር አንስቶ ጸረ መንግሥት መጠነ ሰፊ የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያደራጅ የቆየ ነው።  

የማሊ የቀድሞ ወታደሮች በተጠንቀቅ ቆመው
የማሊ የቀድሞ ወታደሮች በተጠንቀቅ ቆመውምስል picture-alliance/dpa/A.I. Bänsch

የኢኮዋስ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ዦን ክላውድ ብሮው ቀነ-ገደቡ ከመጠናቀቊ ቀደም ብሎ ወታደራዊ ኮሚቴው የሲቪል ሽግግር መንግስት ምስረታው ላይ ከልቡ እንዲያስብበት አሳስበዋል።  ዦን ክላውድ የሚመሩት ኢኮዋስ ቀደም ሲል ባከናወነው የመሪዎች ጉባኤው ላይ ይኽንኑ በጥብቅ አሳስቧል።

«ማሊ ውስጥ ያለውን ኹኔታ በተመለከተ በሲቪል ፕሬዚደንት እና ጠቅላይ ሚንስትር የሚመራ ለ12 ወራት የሚቆይ የፖለቲካ ሽግግር ተደርጎ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ በሀገሪቱ በአፋጣኝ መመለሱን ለማረጋገጥ ጉባኤው መቊረጡን በድጋሚ አጽንዖት ሰጥቶበታል። በነሐሴ 22 ቀን፣ 2012 ዓም በተከናወነው የመሪዎች ልዩ ጉባኤ ይኽን ውሳኔውን አሳልፏል። በማሊ ጉዳይ የሚያገባቸው አካላት በአጠቃላይ ወታደራዊ ኹንታው ማለትም የሕዝብ ታዳጊ ብሔራዊ ኮሚቴ ጨምሮ የሚያካኼዱትን ምክክር በአንክሮ ይከታተላል። የሲቪል መንግስቱ ጊዜያዊ ፕሬዚደንት እና ጠቅላይ ሚንስትር ዘገየ ቢባል በመስከረም 5 ቀን፣ 2013 ዓ.ም መሾም አለባቸው።»

የኢኮዋስ ማስጠንቀቂያ በበረታበት በአኹኑ ወቅት የማሊ የቀድሞ ፕሬዚደንትን በኃይል ያስወገደው ወታደራዊ ኹንታ ከተለያዩ የሀገሪቱ የፖለቲካ እና ሲቪል ማኅበረሰብ ጋር ምክክሩን ሐሙስ አመሻሹ ላይ ጀምሯል። የሲቪል መንግስት ማሊ ውስጥ እንዲመሠረት መንገድ ይጠርጋል ተብሎ የታሰበው ምክክር ለሦስት ቀናት ማለትም ከሐሙስ እስከ ቅዳሜ ድረስ የሚዘልቅ መኾኑም ስብሰባው በተጀመረበት ቀን ተገልጧል።  

የወታደራዊ ኹንታ ክፍል የኾነው የሕዝብ ታዳጊ ብሔራዊ ኮሚቴ (CNSP) መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ
የወታደራዊ ኹንታ ክፍል የኾነው የሕዝብ ታዳጊ ብሔራዊ ኮሚቴ (CNSP) መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታምስል Reuters/M. Kalapo

ማሊ ውስጥ የፕሬዚደንት ኢብራሒም ቦባካር ኪዬታ መንግሥትን አስወግዶ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኹንታ ክፍል የኾነው የሕዝብ ታዳጊ ብሔራዊ ኮሚቴ (CNSP) ኢኮዋስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ካለ 15 አባል ሃገራት ያሉት የምዕራብ አፍሪቃው ኢኮዋስ ርምጃ ይወስዳል ተብሎ ይጠበቃል። 

የማሊ ወታደራዊ ኹንታ ማክሰኞ፤ ነሐሴ 12 ቀን፤ 2012 ዓ.ም ነበር መፈንቅለ-መንግሥት ያከናወነው። መፈንቅለ መንግስቱ ይፋ በኾነ በጥቂት ሰዓታትም ነበር የሀገሪቱ ርእሰ-ብሔር ኢብራሒም ቦባካር ኪዬታ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸውን ይፋ ያደረጉት። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ላለፈው አንድ ወር ማሊ ወደ ቀደመ ቀውሷ እንዳትዘፈቅ በርካቶችን አስግቷል። ምናልባትም የሀገሪቱ እጣ-ፈንታ ከምንም በላይ በወታደራዊ ኹንታው ላይ ሳይወድቅ አልቀረም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ