1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ማሊ ከምዕራባውያኑ ያላትን የሻከረ ግንኙነት

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 8 2014

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ባለፈው ረቡዕ የማሊ ወታደራዊ መሪዎች ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ከቀጠሉ የአውሮፓ አገራት ከማሊ ጋር እንደማይተባበሩ አስጠንቅቀዋል። አሜሪካ እና ፈረንሳይን የመሳሰሉ አገራት ሩሲያ ወደ ማሊ የምትልካቸው ወታደራዊ አሰልጣኞች ቫግነር የተባለው የግል የጸጥታ ጥበቃ ኩባንያ ተቀጣሪዎች ናቸው እያሉ ይከሳሉ

https://p.dw.com/p/4A1i9
Mali | Besuch Aussenministerin Annalena Baerbock
ምስል Florian Gaertner/photothek/picture alliance

ትኩረት በአፍሪካ 

በምዕራብ አፍሪካ አገራት ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ባለፈው ረቡዕ የማሊ ወታደራዊ መሪዎች ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ከቀጠሉ የአውሮፓ አገራት ከአገሪቱ ጋር እንደማይተባበሩ አስጠንቅቀዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በዋና ከተማዋ ባማኮ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የሩሲያ ኃይሎች በሶርያ እና በዩክሬን ፈጽመዋቸዋል የሚባሉ ብርቱ "የጦርነት ወንጀሎች" በማሊ ዜጎች ላይ ተፈጽመዋል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል። 

ሩሲያ ለማሊ ወታደራዊ አሰልጣኞችን ታቀርባለች። አሜሪካ እና ፈረንሳይን የመሳሰሉ አገራት በአንጻሩ ሩሲያ ወደ ማሊ የምትልካቸው ወታደራዊ አሰልጣኞች ቫግነር የተባለው የግል የጸጥታ ጥበቃ ኩባንያ ተቀጣሪዎች ናቸው እያሉ ይከሳሉ። ይኸ ኩባንያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ከሚመሩት የሩሲያ መንግሥት ጋር የጠበቀ ቁርኝት አለው የሚል ክስ ይቀርብበታል። 

Niger | Flüchtlingslager bei Ouallam | Besuch Annalena Baerbock
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በኒጀር የሚገኝ የግብርና ሥራ በጎበኙበት ወቅትምስል Richard Walker/DW

የቫግነር ኩባንያ በማሊ መገኘት እና የአገሪቱ ምርጫ መዘግየት ወታደራዊ መሪዎች የሚቆጣጠሩት የአገሪቱ መንግሥት ከምዕራባውያኑ አገራት ያለውን ግንኙነት አሻክሮታል። ባለፈው ሰኞ የአውሮፓ ኅብረት በዚሁ የሩሲያ ኩባንያ ምክንያት ለማሊ ይሰጥ የነበረውን ወታደራዊ ሥልጠና አቋርጧል። የጀርመኗ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ ታዲያ ማሊ ከሩሲያ ኃይሎች ጋር ባላት ግንኙነት ረገድ ግልጽ መስመር ካላበጀች "ትብብራችንን ልንቀጥል አንችልም" ብለዋል። የአውሮፓ ኅብረት ለማሊ በሚሰጠው ወታደራዊ ሥልጠና 300 ገደማ የጀርመን ወታደሮች ሲሳተፉ ቆይተዋል።

የጀርመኗ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአፍሪካ ጉዟቸው ኒጀርን ጭምር የጎበኙ ሲሆን ከአገሪቱ ፕሬዝደንት መሐመድ ባዞም እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐሶሚ ማሶውዶ ጋር ተገናኝይተው ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። 

የዛሬው የትኩረት በአፍሪካ መሰናዶ ማሊ ከምዕራባውያኑ ያላትን የሻከረ ግንኙነት እና በ10ኛው የአፍሪካ አገራት የምድር ጦር ጉባኤ ላይ ያተኩራል። 

እንዳልካቸው ፈቃደ 
እሸቴ በቀለ