1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት ጠላት ያላቸዉን ወገኖች „በኃይል“ ወይስ “በምክክር“ ?

ሰኞ፣ ግንቦት 7 2015

የፌደራል የመንግሥት ጽንፈኛ ያላቸው ሃይሎች ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። አንዳንድ ወገኞች እና ፖለቲከኞች እንደሚሉት ግን በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ኃይላት ወደ ምክክር የሚመጡበት መንገድ ላይ በትኩረት መሰራት አለበት።

https://p.dw.com/p/4RNCq
Äthiopien Addis Abeba | Sitz der Prosperity Party
ምስል Seyoum Getu/DW

«መንግስት የጸጥታ መዋቅሮችን በማጠናከር አንድ ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊትን በመገንባት በሐገሪቱ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ርብርብ እያደረኩ ነዉ ይላል»

የፌደራል የመንግሥት ጽንፈኛ ያላቸው ሃይሎች ላይ የሕግ ማስከበር እርምጃውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ መንግስት የጸጥታ መዋቅሮችን በማጠናከር አንድ ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊትን በመገንባት በሐገሪቱ ያሉ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ያለውን ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝ አትቷል።

አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ አንድ ፖለቲከኛ ግን በኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ኃይላት ወደ ምክክር የሚመጡበት መንገድ ላይ በትኩረት መሰራት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ስምምነት ከተቋጨ ቦኋላ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሌሎችም ክልሎች ከመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር ውግያ ሲገጥሙ የነበሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ጎዳና በመመለስ የተሐድሶ ፕሮግራም እየተካሄደ እንደሆነ በመግለጫው ያተተው የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን «የራስን እኩይ ፍላጎት በሌሎች ላይ በኃይል በመጫን የትኛውንም ዓይነት ፍላጎትም ሆነ ጥቅም ማረጋገጥ አይቻልም» ሲል በትናንቱ ሳምንታዊ መግለጫ አስጠንቋል።

መንግስት “ጽንፈኛ” ያላቸውን ሃይሎች ለሚወስዱት እርምጃ ያሳየውን ትዕግስት እንደፍርሃት በመቁጠር ዛሬም በጥፋታቸው ቀጥለውበታል ሲል ከሷልም፡፡ በመሆኑም የሕግ ማስከበር እርምጃው ይጠናከራል ብሏል መግለጫው፡፡

Äthiopien | Premierminister Abiy Ahmed Ali
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ሰብሳቢ ዶ/ር ራሔር ባፌ ይህንኑን አስመልክተው ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት መተማመን መሰረታዊ ችግሩ የሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተግባር ላይ ያተኮረ መተማመን በማስፈን እንደሚፈታ ነው የገለጹት፡፡ “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቁልፍ ችግር የአለመተማመን ችግር ሲሆን ይህም ቃልን በተግባር የአለመከወን የሚያመጣው ነው፡፡ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምታት እንደአገር በተለይም መንግስት እና ህዝብ መተማመን ላይ መድረስ የግድ ነው፡፡ ይህ ነው ጊዜ ሊሰጠው የማይገባው፡፡”

ኢትዮጵያ ሂደቱን ከዓመታት በፊት ጀምራ እስካሁን በተፈለገ ፍጥነት እየሄደ የማይመስለውን የብሔራዊ ንግግር እና መግባባት በተቻለ ፍጥነት ወደ ስራ በማስገባት መቀራረብን መፍጥር ዋነኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገነባው መሆኑን ነው ያስቀመጡት፡፡ “መንግስትም አስፈላጊነቱን አምኖ ያቋቋመው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ወደ ስራ እንዲገባ እና ተልእኮውን እንዲጀምር ነው እኛ እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ግፊት እያደረግን ያለነው፡፡ ከጦርነት ማትረፍም ሆነ በጦር እልባት ማግኘት እንደማይቻል ከኛ በላ ተገነዘመ ያለ አይመስልም፡፡ አሁንም ጦርነት በየትኛውም ወገን እልባት ስለማሆን የትኛም ወገን የሰላም አማራጮችን ነው እንደ መፍትሄ ለመውሰድ መጣር ያለበት፡፡”

የኢትዮጵያ መንግስት በትናንትናው መግለጨው ጽንፈኛ ያሏቸው ላይ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚወስድ ቢያስጠነቅቅም ጽንፈኛ የተባሉ ሐይሎች ማንነት በግልጽ አልተቀመጠም።

ከዚህ በፊት ግን መንግስት በተለይም በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል የህዝብ ሰላም ያውካላ ያሏቸውን ለማስታገስ የአገር መከላከያ ሰራዊትን አስፈላጊ ነው በተባሉ ስፍራዎች ሁሉ እንደሚያሰማራ ማስገንዘቡ አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ