የዶ/ር መርጋ ዮናስ፤ ከወለጋ ደምቢዶሎ እስከ ጀርመን ላይብሲሽ የትምህርት ጉዞ
ሐሙስ፣ ጥር 2 2016« የዶክትሬት ትምህርት ለመጀመር ስል አማካሪ አስተማሪዬ ፤ ዶክተር ከሆንክ በኋላ ምን ለማድረግ ነዉ የምትፈልገዉ ሲለኝ እኔ እዉቀት ቀስሜ እዉቀቴን ለሌሎች ማካፈል ነዉ ፍላጎቴ ስል እንደመለስኩለት ትዝ ይለኛል፤ አሁን ይህን አሳክቻለሁ። »
በቅርቡ በኮሚኒኬሽን ዘርፍ ከጀርመን ላይፕሲሽ ዩንቨርስቲ የዶክትሬት ማዕረጉን የተቀበለዉ ዶ/ር መርጋ ዮናስ ቡላ ነዉ። ዶ/ር መርጋ ዮናስ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን እስከ ዘጠነኛ ክፍል ድረስ በትዉልድ ቦታዉ ወለጋ ደምቢዶሎ ዉስጥ፤ ከተማረ በኋላ፤ በአንቦ ከተማ ትምህርቱን በመቀጠል፤ 12ኛ ክፍልን አጠናቋል። በ 12 ኛ ክፍል ማጠናቀቅያ ላይ ያገኘዉ ጥሩ ዉጤት ወጣቱን መርጋ ዮናስን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ሞያ የመጀመርያ ዲግሪዎዉ ለመቀበል አብቅቶታል። በአገር ቤት በተለይ አዲስ አበባ ዉስጥ ሆኖ፤ በአዲስ ፎርቹን እና ሬፖርተር ጋዜጣዎች ላይ በመስራት የጋዜጠኝነት ሞያን አሃዱ ብሎም ተቀላቅሏል። ዶ/ር መርጋ ዮናስ በጀርመን፤ ለሁለተኛ ዲግሪ ማለትም ለማስትሪት ከጀርመን ባገኘዉ የነጻ ትምህርት እድል ወደ ጀርመን አቅንቶ በዶቼ ቬለ እና በቦን ዩንቨርስቲ ፤ በጋዜጠኝነት እና ኮሚኒኬሽን ዘርፍ የማስትሪት ዲግሪዉን አጠናቋል። በጀርመን ሲኖር አስር ዓመታትን ያስቆጠረዉ ዶክተር መርጋ ዩናስ የማስትሪት ዲግሪዉን እንዳጠናቀቀ፤ የዶቸ ቬለ የአማርኛዉ ክፍል ባልደረባ ሆኖ በርካታ ዘገቦችን ጽፏል። በዶቼ ቬለዉ የእንጊሊዘኛ ክፍልም የተለያዩ ጽሑፎችን በማቅረቡ ይታወቃል። ከዝያም በመቀጠል እዚሁ በዶቼ ቬለ አካዳሚ ዉስጥ የአንድ ሚዲያ ፕሮጀክት፤ ስራ አስኪያጅ ሆኖ አገልግሏል። መርጋ ዮናስ በዶቼ ቬለ በጋዜጠኝነት ሞያ ባልደረባችን ሳለና በስራ ገበታችን ላይ ስንገናኝ፤ ኦቦ መርጋ ስንል ነበር የምንጠራዉ። በጣም ቁጥብ፤ አመለሸጋ፤ ሰዉ አክባሪ እና ትሁት ስብዕናም ያለዉ ሰዉ ነዉ። ኦቦ መርጋ ትምህርት ከጀመረ ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ፤ በማህበራዊ ሚዲያ አልያም በኢሜል መልክት ልዉዉጥ በስተቀር በስራና በትምህርት ዉጥረት ምክንያት ከአካባቢዉ ጠፍቶ ቆይቷል። ይሁንና የጎርጎረሳዉያኑ 2024 ዓመት መባቻ ላይ Transnational Communication and Identity Construction in Diaspora ማለትም ድንበር ተሻጋሪ ኮሚኒኬሽን/ተግባቦት እና የዲያስፖራዉ የማንነት ግንባታ የተሰኘዉ የዶክትሬት ምረቃ ጽሁፉን በመጽሐፍ መልክ አሳትሞ ለአዲስ ዓመት ስጦታዩ ሲል በማህበራዊ መገናኛ ለወዳጆቹ አጋርቷል። ይህን አይተን ኦቦ መርጋን እንኳን ደስ ያለህ ስንል፤ ዶ/ር መርጋ ዩናስ ስል ሃሎ አልነዉ!
« አመሰግናለሁ፤ በዴቼ ቬለ አገለግልበት በነበረበት ቦታ ተመልሼ ቃለ ምልልስ ለመስጠት እድል በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ። ከአሃገራችን ወጥተን ወደዚህ ስንመጣ ራሳችንን ለመለወጥ ፤ ከዝያም አልፎ ቤተሰቦቻችንን ለመለወጥ ነዉ። ስለዚህም እራሴን ለመለወጥ ባደረኩት ጥረት በጎርጎረሳዉያኑ 2018 መጨረሻ ላይ ፤ ወደ ዶቼ ቬለ አካዳሚ ከትምህርቴ ጋር ትንሽ የሚቀራረብ ሥራ ስሰራ ቆይቻለሁ። ሦስተኛ ዲግሪዬ በተለይ የሃገራት ድንበር ዘለል ኮሚኒኬሽን በሚል በጀርመንዋ ላይፕሲሽ ከተማ ዩንቨርስቲ እዛዉ ዶቼ ቬለ አካዳሚ እየሰራሁ ትምህርቴን ጀመርኩ። በዶቼ ቬለ ሦስት ሁለት ቀናት ብቻ ስሰራ ስለነበር ብዙ ጊዜ ስላለኝ ሦስተኛ ዲግሪዬን ብሰራ ይሻላል በሚል አስቤ ነዉ ትምህርት የጀመርኩት። 2020 ላይ ግን ትምህርቱ ብዙ ጊዜ እየወሰደብኝ ስለተቸገርኩ የዶቼ ቬለ አካዳሚ ስራዬን ለቅቄ ወጣሁ። ከዝያም ሙሉ በሙሉ ትኩረቴን ትምህርቴ ላይ አደረኩ»
ዶ/ር መርጋ ድንበር ተሻጋሪ ኮሚኒኬሽን እና የዲያስፖራዉ የማንነት ግንባት የሚለዉ የዶክትሪት መመርቅያ ጽሑፉ በተለይ በኢትዮጵያዊነት፤ በኦሮሞ ፤ በሶማሌ እንዲሁም በኤርትራ ማህበረሰቦች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነዉ። የዲያስፖራዉ ማህበረሰብ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ምን አይነት ርዕሶችን ያነሳል? ስለትዉልድ ሃገሩ በምን ጉዳይ ላይ ይግባባል? የድያስፖራዉ የግል እና የጋራ ማንነት ግንባታ እንዲሁም የማንነት ጥያቄ ቁርቁሶችንም ይዳስሳል።
ኦቦ መርጋ በእንጊሊዘኛ ያቀረበዉ የዶክትሬት የጥናት ጽሑፍ፤ በጀርመን ታዋቂ በሆነዉ አሳታሚ ድርጅት በመጽሐፍ መልክ ታትሞ ለአንባቢ ቀርቧል። በመጽሐፍ የታተመዉ 67 ይሮ ያወጣል፤ በኢንተርኔት ላይ ለማንበብ ወይም በሶፍት ኮፒ ደግሞ 85 ይሮ ይሸጣል። ዶ/ር መርጋ ዮናስ፤ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ በኢትዮጵያ በሱዳን ብሎም የአፍሪቃዉን ቀንድ በተመለከተ ታገስ ሽፒግል በተባለዉ የጀርመን እዉቅ ጋዜጣን ጨምሮ ለተለያዩ ጋዜጦች እና ለሚዲያ ተቋማት ይጽፋል። ዶ/ር መርጋ ዮናስ ባለትዳር እና ቢሊሌ የምትባል የሦስት ዓመት ልጅ አባትም ነዉ። ዶ/ር መርጋ ዮናስ የጋዜጠኝነት ሞያዉ በደሙ ዉስጥ እንዳለ ይናገራል፤ በአሁን ወቅት ጀርመን ዉስጥ በተለይ በአፍሪቃዉ ቀንድ አካባቢ ሃገራት የሚዲያ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ሆኖ እየሰራ ነዉ።
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ